ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሮም ሀገረ ስብከት የሮምን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እንዲተባበር ጠየቁ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሮም ሀገረ ስብከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጪው 2025 የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንን ለመቀበል ዝግጅት በማድረግ ላይ በሚገኝበት ወቅት በሀገረ ስብከቱ ውስጥ በሚገኙ ቁምስናዎች ውስጥ ለሚያገለግሉት ካኅናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ለድሆች እና ለችግረኞች አጋርነታቸውን በመግለጽ በበጎ አድራጎት ተግባራቸው ተጨባጭ ምልክት እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ተስፋን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፥ “ተስፋን የሚያመነጨው የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፣ ፍቅሩም የሚገለጸው በእኛ ፍቅር አማካይነት ነው” ብለው፥ የእግዚአብሔርን ፍቅር በተጨባጭ የበጎ አድራጎት ተግባራት በኩል በሰዎች ሕይወት ተስፋን ለመፍጠር በስውር ብዙ ለሚለፉ የሮም ሀገረ ስብከት በርካታ ቁምስናዎች፣ መንፈሳዊ ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ቤተሰቦች ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሮም ከተማ የሚታይ የመኖሪያ ቤት ችግር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ውስጥ የጋራ ጥቅም የሰው ልጅን ክብር የሚያረጋግጡ ማለትም መሬት፣ መኖሪያ ቤት እና ሥራ የማይጣሱ መብቶች የሚያካትት መሆኑን በማስታወስ፥ በተለይ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በጣሊያን መዲና ሮም ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩት ተስፋ እና ክብር የሚጎለብትበት ቁልፍ ጉዳ መሆኑን አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በኢዮቤልዩ ዓመት ወደ ሮም ለሚመጡ በርካታ ምዕመናን በሚደረግ ዝግጅት ላይ የሮም ቤተ ክርስቲያን ከሕዝብ ተቋማት እና ማኅበራት ጋር በመተባበር ይህን ማኅበራዊ ችግር እንድትፈታው አሳስበዋል።
ቤት ለሌላቸው የፍቅር ምልክት ማሳየት
በተለይም ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ማኅበራት ቤት የሌላቸውን ወይም በማደሪያ እጦት አደጋ ላይ ለሚገኘውን ማንኛውንም ሰው የአገልግሎት ንብረቶችን ወይም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ቤቶችን በማቅረብ ደፋር የፍቅር ምሳሌ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። መጠለያ የሌላቸው እነዚህ ሰዎች በተቋማት እና በማኅበራዊ አገልግሎቶች በኩል ድጋፍ እንደሚደረግላቸው፣ ማኅበራት እና ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች ደግሞ ወንድማማችነትን የተላበሱ ሌሎች የመስተንግዶ አገልግሎቶችን እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ በሮም ሀገረ ስብከት የሚገኙ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ምዕመናን ላደረጉት ልግስና እና የእግዚአብሔርን ፍቅር በሁሉም ሰው ሕይወት በማስተላለፍ በተለይም እጅግ ለተቸገሩት ተስፋን በመስጠት ለሚያደርጉት እገዛ በድጋሚ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።