ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የሁሉ ነገር ምንጭ ፍቅር ነው” በማለት አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞች እና እህቶች መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! በዛሬው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከማር 12፡28-34 ተወስዶ የተነበበው የወንጌል ክፍል ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ካደረጋቸው በርካታ ውይይቶች መካከል ስለ አንዱ ይነግረናል። ከጸሐፍት መካከል አንዱ ወደ እርሱ ቀርቦ፥ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። (ቁጥር 28) ኢየሱስም የሙሴን ሕግ ሁለት መሠረታዊ ቃላት አንድ ላይ በማጣመር እንዲህ ሲል መለሰ፡- ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ’ ሁለተኛውም ፥ ‘ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው ሲል መለሰ (ማር. 12: 30-31)።
ጸሐፊው ለኢየሱስ ካቀረበው ጥያቄ በመነሳት የትእዛዛቱ ሁሉ መጀመሪያ ማለትም ለትእዛዛት ሁሉ መሠረት የሆነውን ይፈልግ ነበር። አይሁዶች ብዙ ትእዛዛት ነበሯቸው፤ ከትእዛዛቶች ሁሉ መካከል መሠረት እና ዋና የሆነውን ይፈልጉ ነበር። መሠረታዊ በሆነው አንዱ ትእዛዝ ላይ ለመስማማት ይሞክሩ ነበር። እውነትን ለማግኘት የሚደረግ በመሆኑ መልካም ውይይት ነበር። ይህ ጥያቄ ለሕይወታችን እና ለእምነት ጉዞአችን አስፈላጊ ነው። በእርግጥ እኛም አንዳንድ ጊዜ በብዙ ነገሮች መካከል ስንሆን የጠፋን ይመስለንና እንዲህ በማለት እራሳችንን እንጠይቃለን፥ “ከሁሉ የሚበልጥ አስፈላጊው ነገር የቱ ነው? የሕይወቴን ወይም የእምነቴ ማዕከል የት ላገኝ እችላለሁ?” ብለን እራሳችንን ስንጠይቅ ኢየሱስ ሁለት ዋና ዋና ትእዛዛትን አንድ ላይ በማድረግ መልስ ይሰጠናል። መልሶቹም የእግዚአብሔር ፍቅር እና የጎረቤት ፍቅር ናቸው። የእምነታችን ልብም ይህ ነው።
ወደ ሕይወት እና ወደ እምነት ልብ መመለስ እንዳለብን ሁላችንም እናውቃለን። ምክንያቱም ‘ልብ የጥንካሬ እና የእምነት ዋና ምንጭ ነው’ (‘እርሱ ይወደናል’ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ቁ. 9)። ኢየሱስ የሁሉ ነገር ምንጭ ፍቅር እንደሆነ እና እግዚአብሔርን ከሰው መለየት በፍፁም እንደሌለብን ይነግረናል። እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ለደቀ መዝሙሩ እንዲህ ሲል ይናገራል። በሕይወት ጉዞ መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሚቃጠል መስዋዕት እና ሌሎች መስዋዕቶች የመሳሰሉ ውጫዊ ተግባራት አይደሉም (ማር 12:33)። ነገር ግን ራስን ለእግዚአብሔር እና ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን በፍቅር የምንገልጥበት የልብ ዝግጁነት ነው። ወንድሞቼ እና እህቶቼ እኛ ብዙ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። ነገር ግን ለራሳችን ብቻ የምናደርግ ከሆነ፣ ለሌሎችም ስናደርግ ያለ ፍቅር በተዘበራረቀ ወይም በተዘጋ ልብ ከሆነ ዋጋ የለውም። ሁሉም ነገር በፍቅር መደረግ አለበት።
እግዚአብሔር ተመልሶ በሚመጣበት ጊዜ መጀመሪያ የሚጠይቀን ስለ ፍቅር፥ ‘ሌሎችን እንዴት ወድዳችኋል?” የሚል ስለሆነ እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ትእዛዝ በልባችን ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ‘ይህ ትእዛዝ የቱ ነው?’ ብለን ስንጠይቅ፥ እግዚአብሔር አምላክህን ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ’ የሚል ነው። በየዕለቱ የህሊና ምርመራን በማድረግ እራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ ይገባል፥ ለእግዚአብሔር እና ለጎረቤት ያለኝ ፍቅር የሕይወቴ ማዕከል ነው? ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የማቀርበው ጸሎት ወደ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንድሄድ እና በነጻ እንድወዳቸው ያነሳሳኛል? በሌሎች ውስጥ እግዚአብሔር እንደሚገኝ ማወቅ እችላለሁ?
በንጹሕ ልቧ የእግዚአብሔርን ሕግ የተሸከመች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔርን፣ ወንድሞቻችንን እህቶቻችንን እንድንወድ ትርዳን።”