ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የአሦራውያን ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክን በቫቲካን ተቀብለው ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የአሦራውያን ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክን በቫቲካን ተቀብለው   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የመካከለኛው ምሥራቅ ክርስቲያኖች በጦርነት መካከል ምስክሮች እንዲሆኑ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምሥራቅ አሦራውያን ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማር አዋን ቅዳሜ ጥቅምት 30/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማር አዋን ወደ ቫቲካን የመጡት በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና በአሦር ፓትርያርክ በብጹዕ ወቅዱስ ማር ዲንካ 4ኛ መካከል የኢየሱስ ክርስቶስን አካላዊ ተፈጥሮ በማስመልከት የጋራ መግለጫ ያወጡበት ሰላሳኛ ዓመት የመታሰቢያ በዓል ለማክበር እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጋራ መግለጫው በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለ1500 ዓመታት የቆየውን የአስተምህሮ ውዝግብ ያስቆመ እንደሆነ ይታወቃል። የጋራ ስምምነቱ ወደ ሙሉ አንድነት ለመድረስ አብረው ለመሥራት ቃል የገቡበት እንደነበረ ሲታወስ፥ “እውነትን ለማግኘት የሚደረግ ውይይት ከበጎ አድራጎት እና ከሕይወት ውይይት ፈጽሞ መለየት የለበትም” የሚል እንደ ነበር ይታወሳል።

በብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማር አዋ የተመራው የልኡካን ቡድን ከቅዱስነታቸው ጋር ቫቲካን ውስጥ በተገናኙበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ከሁለቱም አብያት ክርስቲያናት የተወጣጡ የሥነ-መለኮታዊ ውይይት ኮሚሽን አባላት እንደ ነበሩ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በቫቲካን ለተቀበሏቸው እንግዶች ባሰሙት ንግግር፥ በመካከለኛው ምሥራቅ በጦርነት በሚሰቃዩ አገራት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያን ወንድሞች እና እህቶች ዛሬም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲመሰክሩ በማሳሰብ በጋራ እንጸልይ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀድሞው አባቶችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር ዲንካ 4ኛ ወደ ሙሉ አንድነት ለመድረስ በኅብረት መጓዝ እና አብሮ መሥራት በማስመልከት ያወጡትን የጋራ መግለጫ መመልከት እንደሚገባ አሳስበው፥ ይህ ሙሉ አንድነት በመንበረ ታቦት ላይ አብረን ለመጸለይ እና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ እና ደም በኅብረት የምንቀበልበት የተባረከ ቀን የመድረስ ተስፋ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሙሉ ኅብረት የሚያመራው መሠረታዊ እርምጃ ሠነድ የተፈረመበት ሰላሳኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር ወደ ሮም የመጡትን የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ማር ዋ 3ኛን በቫቲካን ተቀብለዋል። የብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር ዋ 3ኛ የቫቲካን ጉብኝት አሦራዊው ፓትርያርክ ከዚህ ቀደም ወደ ሮም ያደረጉትን 40ኛ ዓመት ለማክበር እንደ ሆነም ታውቋል። በዓሉ ላይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በምሥራቅ አሦራውያን ቤተ ክርስቲያን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው የጋራ ውይይት ኮሚሽን አባላትም መገኘታቸው ታውቋል።

የጋራ ውይይት ኮሚሽኑ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 1984 ሥራውን የጀመረው በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና በብጹዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ማር ዲንካ 4ኛ ተነሳሽነት እንደ ነበር ሲታወስ አሁን በሥርዓተ አምልኮ ላይ አዲስ የውይይት ምዕራፍ መጀመሩ ታውቋል።

ወደ ሙሉ አንድነት የሚደረግ ጉዞ
በኅዳር ወር ስልሳኛ ዓመቱን የሚያከብረውን የክርስቲያኖች አንድነት ስምምነት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የዘመናት ጌታ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በውስጣቸው ያለውን ልዩነት ተመልክተው ወደ ንስሐ እና ወደ አንድነት የሚያመጣቸውን ፍላጎት በብዛት ማፍሰስ መጀመሩን ገልጸው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን በጣሊያን የቤርጋሞን ከተማ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ እና መልካም የነገረ መለኮት ምሁር ዮሐንስ ዚዚዮላስን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሥነ-መለኮት የጋራ ውይይት ኮሚሽን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሥነ-መለኮት የጋራ ውይይት ኮሚሽን በቫቲካን በተቀበሏቸው ወቅት

ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ የዘለቀው የአስተምህሮ ውዝግቦች ፍጻሜ
ጉዞው አዝጋሚ ቢሆንም “ከመነሻው ጀምሮ ለክርስቲያኖች አንድነት የሚደረግ እንቅስቃሴን ያለማቋረጥ ልናዳብረው የሚገባን ጸጋ ነው” በማለት በድጋሚ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የጋራ የክርስትና መግለጫ ማዕከል ላይ ያለው ጥንታዊ እና አዲስ ፍላጎት እንደሆነ ገልጸው፥ የኤፌሶን ጉባኤን በተመለከተ ለ1500 ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን የአስተምህሮ ውዝግብ ፍጻሜ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።

በጠቅላላው የሰው ልጆች ውይይት ነው!
በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የጸደቀው መግለጫው ለሥነ-መለኮታዊ የጋራ ውይይት ኮሚሽን መቋቋም ምክንያት መሆኑ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የኮሚሽኑ ሥራ ውጤት አስደናቂ እንደ ነበር ገልጸው፥ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተፈረሙ አንዳንድ የአስተምህሮአዊ እና ሐዋርያዊ ስምምነቶችን በማስታወስ ኮሚሽኑን ላቋቋሙት የነገረ መለኮት ምሁራን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማር አዋን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማር አዋን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ

ቅዱስ ይስሐቅ ዘነነዌ በሮማዊያን ሰማዕታት ታሪክ ውስጥ
“በእምነት ውስጥ ያለው አንድነት በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን በኩል አስቀድሞ የተገኘ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ፥ ወደ ሙሉ አንድነት በሚወስደው መንገድ ላይ መልካም መሪዎቻችን ናቸው” በማለት አክለዋል።

በቅርቡ ለተካሄደው የሲኖዶሳዊነት ጉባኤ ብርታትን ከሰጡት የሶርያ ምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት አባቶች መካከል አንዱ የሆነው ታላቁ የነነዌ ቅዱስ ይስሐቅ በሮማውያን ሰማዕታት ታሪክ ውስጥ የባህል ሊቅ እና ቅዱስ በመባል እንደሚታወቅ ገልጸዋል።

በቅዱስ ቁርባን ላይ ያለ የአንድነት ተስፋ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የቅዱስ ይስሐቅ አማላጅነት እና በቤተ ክርስቲያናችን መካከል ያለው ወዳጅነት እስከ ቅዱስ ቁርባን ድረስ ማደግ እንዲቀጥል ጠይቀው፥ በኅብረት በመጓዝ አብሮ በመጸለይ እና በመሥራት ወደ ሙሉ አንድነት መድረስ እንደሚገባ አሳስበው፥ በመጨረሻም በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አንድ ላይ ሆነው በለመዱት መንገድ እና በቋንቋቸው እንዲጸልዩ በመጋበዝ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፓትርያርክ አቡነ ማር አዋ ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፓትርያርክ አቡነ ማር አዋ ከተመራው የልኡካን ቡድን ጋር

 

09 November 2024, 15:31