ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “መንፈሳዊ ተሰጥዎች የአንድነት እና የአገልግሎት መንፈስ ስጦታዎች ናቸው”
“ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችም አሉ፤ አሠራሮችም ልዩ ልዩ አሉ፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ ግን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ የመንፈስን መግለጥ የሚሰጠው ለጥቅም ነው። ይህን ሁሉ ግን አንዱና ያው መንፈስ ያደርጋል፤ እንደ ፈቃዱም ለእያንዳንዱ ሰው ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል” (1ኛ ቆሮ. 12:4-7 ፣ 11)
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በመጨረሻዎቹ ሦስት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዎች ውስጥ በቅዱሳት ምስጢራት፣ በጸሎት እና የእግዚአብሔር እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን በመከተል ውስት ያለውን የመንፈስ ቅዱስ የመቀደስ ሥራ ተመልክተናል። ነገር ግን ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ የተወሰደ አንድ ታዋቂ ጽሑፍ ምን እንደሚል እንመልከትር፡- ‘መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚቀድሰው፣ የሚመራው እና በበጎ ምግባራት የሚያበለጽገው በቅዱሳት ምስጢራት እና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቻ አይደለም። ስጦታውን እንደ ፈቀዱ ለእያንዳንዱ ሰው በማካፈል ነው’ (1ቆሮ. 12፡11) (‘የሕዝቦች ብርሃን’ ሐዋርያዊ ሠነድ ቁ. 12)
ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሠራበትን ሁለተኛውን መንገድ መመልከት እንችላለን። ይህም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ተግባር ነው። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ምን እንደሆነ ለማብራራት ሁለት ነገሮች አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። አንደኛው ‘ለጋራ ጥቅም’ የሚሰጥ ስጦታ ነው (1ቆሮ 12፡7)። በሌላ አነጋገር ይህ ስጦታ በዋናነት እና በተለምዶ አንድን ሰው ብቻ ለመቀደስ የታሰበ አይደለም። ነገር ግን ለማኅበረሰቡ ‘አገልግሎት’ ነው። በ1ጴጥ. 4፡10 እንዲህ ተጽፏልና፥ “የእግዚአብሔርን ልዩ ልዩ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል’። በሁለተኛ ደረጃ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለአንድ ሰው ወይም ለአንዳንድ ሰዎች በግል የሚሰጥ ስጦታ ነው። ለሁሉም ሰው በተመሳሳይ ሁኔታ የሚሰጥ አይደለም። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ከመቀደስ ጸጋ፣ ከሥነ-መለኮታዊ ምግባራት እና ከቅዱሳት ምሥጢራት የሚለየው ይህ ነው። እነዚህ ግን ለሁሉም ተመሳሳይ እና የተለመዱ ናቸው።
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ይህን በሚገባ እንዲህ ሲል ያብራራል፥ ‘መንፈስ ቅዱስ በእያንዳንዱ ደረጃ ለሚገኙ ምዕመናን ልዩ ጸጋዎችን ያከፋፍላል’። በእነዚህ ስጦታዎች በኩል እንደ ሐዋርያው ቃል፣ ለቤተ ክርስቲያን መታደስ እና ግንባታ የሚያበረክቱ የተለያዩ ሥራዎችን በብቃት ለመወጣት ብቁ እና ዝግጁ ያደርጋቸዋል። “የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለጋራ ጥቅም የሚሰጥ ስጦታ ነው’ (1ቆሮ 12፡7)።
መንፈሳዊ ተስጥዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ሙሽራ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ውብ ለማድረግ መንፈስ ቅዱስ ለሰዎች የሚያከፋፍላቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። ስለዚህ አንድ ሰው የጉባኤው ጽሑፍ በሚከተለው ማሳሰቢያ የሚደመደመው ለምን እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡- ‘እነዚህ መንፈሳዊ ተሰጥዎች ማራኪ፣ በጣም የጎሉ ወይም ቀላል ይሁኑ ለሰዎች በስፋት የሚዳረሱት ፍጹም ተስማሚ፣ ጠቃሚ እና ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች በመሆናቸው ከምስጋና እና መጽናናት ጋር መቀበል አለባቸው።’ (‘የሕዝቦች ብርሃን’ ሐዋርያዊ ሠነድ ቁ. 12)
የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ ሠነድ ውብ ጽሑፍ ብቻ ሆኖ አልቀረም። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ ራሱን በሥራ ለማረጋገጥ ስለወሰደ ነው። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2012 በጸሎተ ሐሙስ ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባደረጉት ንግግር፡- ‘ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ በኋላ ያለውን ታሪክ የተመለከተ ማንኛውም ሰው የእውነተኛ እድሳት ሂደትን ሊገነዘብ ይችላል። ይህም ብዙውን ጊዜ በሕያው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያልተጠበቁ ቅርጾችን በመውሰድ የማይጠፋውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያውነት፣ የመንፈስ ቅዱስ መገኘት እና ውጤታማነት ተጨባጭ ያደርገዋል።’
በተጨማሪም ተሰጥዎችን እንደገና ማወቅ ምእመናንን በተለይም የሴቶችን ዕድገት እንደ ተቋማዊ እና ማኅበረሰባዊ እውነታ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እና በመንፈሳዊው ገጽታም መረዳትን ያረጋግጣል። በእርግጥም ምእመናን የቤተ ክኅነት ውጫዊ ተባባሪዎች ወይም ረዳት ሠራዊት አይደሉም። ይልቁንም በራሳቸው ተሰጥዎ እና ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የሚሳተፉ ናቸው።
ሌላ ነገር እናክልበት፣ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ስናወራ አለመግባባትን ወዲያውኑ ማስወገድ አለብን። አስደናቂ ወይም ልዩ ከሆኑ ስጦታዎች እና ችሎታዎች እንለያቸው። ይልቁንም ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኙ ከሆነ እና በሕይወታችን ውስጥ በፍቅር ከያዝናቸው ልዩ ዋጋ የሚሰጣቸው ተራ ስጦታዎች ናቸው።
እንዲህ ዓይነቱ የመንፈሳዊ ስጦታዎች ትርጉም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ብዙ ክርስቲያኖች ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ሲነገር ሲሰሙ ሐዘን እና ብስጭት ያጋጥማቸዋል። ምንም እንደሌላቸው ስለሚያምኑ እና እንደተገለሉ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ቅዱስ አውግስጢኖስም በዘመኑ እጅግ አስደናቂ በሆነ ንጽጽር ለሕዝቡ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፡- ‘በፍቅር ከተያዛችሁ ምንም ነገር የለም ማለት አይደለም፤ አንድነትን ወይም አብሮነትን ብትወዱ በዚያ አንድነት ውስጥ ያለው ሁሉ ለእናንተም ነው። በሰውነት ውስጥ ዓይን ብቻውን ያያል፤ ዓይን የሚያየው ለራሱ ብቻ ነውን? ለሁለቱም ለእጅ እና ለእግር እንዲሁም ለሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሁሉ ይመለከታል።’
ይህም በጎነት ለምን በሐዋርያው እጅግ የላቀ መንገድ ተብሎ የተገለጸበትን ምስጢር ይገልጣል። ‘ነገር ግን የላቀውን የጸጋ ስጦታ በብርቱ ፈልጉ። ደግሞም ከሁሉ የሚበልጥ መንገድ አሳያችኋለሁ’ (1ኛ ቆሮ 12፣31)። መንፈሳዊ ተሰጥዎ ቤተ ክርስቲያንን ወይም የምኖርበትን ማኅበረሰብ እንድወድ ያደርገኛል። አንድነትን፣ አንዳንዶችን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ስጦታዎች እንድወድ ያደርገኛል። እንደራሴ ስጦታዎች አድርጌ እንድመለከታቸው ያደርገኛል። ምንም እንኳን ትንሽ መስለው ቢታዩም የሁሉ ሰው ስለሆኑ ሁሉንም ሰው የሚጠቅሙ ናቸው። በጎነት ብዙ መንፈሳዊ ተሰጥዎች አሉት፤ የአንድ ሰው መንፈሳዊ ስጦታን የሁሉ ሰው ያደርገዋል።"