ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቴህራን የሃይማኖት እና የባህል ውይይት ማዕከል ልኡካን ጋር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቴህራን የሃይማኖት እና የባህል ውይይት ማዕከል ልኡካን ጋር  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጦርነት ስጋት በሚገኝ ዓለማችን ውስጥ ለሰላም መሥራት እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ኅዳር 11/2017 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ቀደም ብለው በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ለአሥራ ሁለተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ከተገኙ የቴህራን የሃይማኖት እና የባህል ውይይት ማዕከል ልኡካን ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው “ለወጣቶች በሚሰጥ ትምህርት በተለይም በቤተሰብ ውስጥ የክርስቲያን እና የሙስሊም ማኅበረሰብ ተግዳሮቶች” በሚል ርዕሥ የቀረበውን ውይይት ለተካፈሉት ልኡካን ባደረጉት ንግግር፥ “ሁሉን ቻይ የእግዚአብሔር ፍቅር የሚያምኑ ሰዎችን በዓለም እና በአዲሱ ትውልድ ፊት ታማኞች እንድንሆን ያደርገናል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

“በሰላም አምላክ የምናምን፣ ሁሉን ቻይ በሆነው በእግዚአብሔር ፍቅር የምናምን እኛ ሁላችን በጋራ የምናደርገው ጥረት ሰላምን ለዓለም ማሳየት እንድንችል በተለይም በአዲሱ ትውልድ ፊት ታማኞች ሆነን እንድንገኝ ያደርገናል” ብለዋል። “በጥላቻ፣ በውጥረት፣ በጦርነት እና በኒውክሌር ግጭት ስጋት የተከፋፈለ ዓለም አሁን ያለው ሁኔታ ለጸሎት፣ ለውይይት፣ ለእርቅ፣ ለሰላም፣ ለደህንነት እና ለሁሉም የሰው ልጅ ጠቅላላ ልማት እንድንሠራ ይገፋፋናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንንችስኮስ ይህን የተናገሩት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ከማቅረባቸው በፊት ዛሬ ማለዳ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት ጽሕፈት ቤት ባዘጋጀው ውይይት ላይ ለተገኙት የቴህራን የሃይማኖት እና የባህል ውይይት ማዕከል ልኡካን ባስተላለፉት መልዕክት እንደ ነበር ታውቋል።

የአያቶች ትምህርታዊ አስተዋፅኦ የጋራችን ነው!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለልኡካኑ ባሰሙት ንግግር፥ “በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገው የረጅም ጊዜ ትብብር የውይይት ባሕልን የሚደግፍ እና ለእኔም ጭምር ውድ እና መሠረታዊ ነው” ሲሉ ገልጸው፥ “ለወጣቶች የሚሰጥ ትምህርት በተለይም በቤተሰብ ውስጥ የክርስቲያን እና የሙስሊም ማኅበረሰቦች ፈተና” የሚለው የጋራ ውይይት ርዕሥ መልካም እና ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸውላቸዋል። “ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች የሚወሰዱበት፣ አንድ ሰው ማዳመጥን የሚማርበት፣ ሰዎችን ለይቶ የሚያውቅበት፣ ማክበር፣ መርዳት እና ከእነሱ ጋር አብሮ መኖርን የሚማርበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው” ሲሉ ደጋግመው ተናግረዋል።

አረጋውያን ለወጣቶች በሚያበረክቱት ትምህርታዊ አስተዋፅዖ ከተለያዩ ሃይማኖታዊ ባህሎቻችን ውስጥ አንድ የተለመደ ነገር ይገኛል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ለልባቸው ቅርብ የሆነውን አንድ ነገር ሲናገሩ፥ አያቶች በጥበባቸው ለልጅ ልጆቻቸው ሃይማኖታዊ ትምህርትን ያረጋግጣሉ፣ በትውልዶች መካከል ባለው የቤተሰብ ግንኙነት ውስጥ አያቶችን ማክበር ወሳኝ እና በጣም አስፈላጊ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቴህራን ከመጡ የጋራ ውይይት ተሳታፊዎች ጋር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቴህራን ከመጡ የጋራ ውይይት ተሳታፊዎች ጋር

በአማኞች መካከል የሚደረግ ውይይት ለቤተሰብ ግንኙነት በር ይከፍታል
“በሕይወት ምስክርነት የሚተላለፍ ሃይማኖታዊነት ለወጣቶች እድገት ትልቅ ዋጋ እንዳለው ሊታሰብ ይገባል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ” በሚለው ሐዋርያዊ የድህረ ሲኖዶስ ማሳሰቢያቸው ውስጥ እንደገለጹትም፥ አዲስ እና ውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ በሚገኝ ማኅበረሰብ ውስጥ ድብልቅ ጋብቻ ለክርስቲያኖች እና ለሙስሊሞች የተደባለቀ የትምህርት ፈተና በመሆኑ፥ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ልዩ መብት እና ቦታ የሚሰጠው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል። 

በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ዘንድ ያለው የእምነት እና የሃይማኖታዊ ተግባራት መዳከም የተጎዳው ቤተሰብ ዛሬ ብዙ ተግዳሮቶችን እንዲጋፈጥ እና የትምህርት ተልዕኮውን በተሻለ ሁኔታ እንዲወጣው መጠራቱን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በምልዕክታቸው፣ ይህን ተግዳሮት ለማሸነፍ የመንግሥት፣ የትምህርት ተቋማት፣ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብን ጨምሮ የሁሉም ሰው ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ወንድማዊ ትብብር እና የእያንዳንዱ ሰው ክብር
የጋር ውይይት ፍሬያማ እንዲሆን ከተፈለገ፥ ቅን፣ የተከበረ፣ የወዳጃነት እና ተጨባጭ መሆን አለበት” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጋራ ውይይት በማኅበረሰቡ ዘንድ፣ በተወካዮቻቸው ፊት ለማኅበረሰባቸው ታማኝ መሆን እንዳለበት ተናግረው፥ ለምናስበው፣ ለምንናገረው ወይም ለምናደርገው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች እንደምንሆን መዘንጋት እንዳይገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም የወጣቶች ትምህርት “እግዚአብሔርን በመፈለግ በወንድማማችነት ትብብር የሚገኝ እንደሆነ አስረድተው፥ በዚህ ፍለጋ ውስጥ የእያንዳንዱን ሰው፣ የእያንዳንዱን ማኅበረሰብ እና የእያንዳንዱን ሕዝብ ክብር እና መብት ለማስከበር ከመናገር እና ከመሥራት ወደ ኋላ ማለት እንደማይገባ አሳስበው፥ የግለሰብን፣ የማኅበረሰብን እና የሕዝብን መብት ማስጠበቅ የህሊና እና የእምነት ነፃነት መብቶች ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ በመጥቀስ እንደተናገሩትም፥ “የሃይማኖት ነፃነት በአንድ ሰው የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ነገር ግን አንድ ሰው በእምነቱ እና በሃይማኖታዊ ልምምዱ ላይ ለመወሰን ሙሉ በሙሉ ነፃ እንዲሆን ይፈቅዳል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ  የቴህራን የሃይማኖት እና የባህል ውይይት ማዕከል ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቴህራን የሃይማኖት እና የባህል ውይይት ማዕከል ልኡካንን በቫቲካን ተቀብለው

በኢራን ውስጥ ለሚገኝ ጥቂት ካቶሊካዊ ምዕመና ቅርብ መሆን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው መጀመሪያ ላይ፥ ኅዳር 28/2017 ዓ. ም. በኢራን የቴህራን-ኢስፋሃን ሊቀ ጳጳስ ለሆኑት ለአቡነ ዶሚኒክ ዮሴፍ ማቲዩ የካርዲናልነት ማዕረግ እንደሚሰጡ አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም “ይህም ኢራን ውስጥ ለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ያለኝን ቅርበት እና አሳቢነት የሚገልጽበት መንገድ ነው” ብለው፥ ይህ በተጨማሪም መላውን አገር የሚያስታውሱበት መንገድ እንደሆነ ገልጸው፥ ኢራን ውስጥ ስለሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ዕጣ ፈንታን በተመለከተ፥ “ለመላው ኅብረተሰብ ጥቅም ሲባል ከሃይማኖት፣ ከጎሳ ወይም ከፖለቲካ ነፃ በሆነ መንገድ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመመስከር የበኩሉን አስተዋጾ ለማበርከት ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች እንደሚያውቁ አረጋግጠዋል።

 


 

20 November 2024, 17:03