ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከተቀበሏቸው የቤተሰብ አባላት ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ከተቀበሏቸው የቤተሰብ አባላት ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ቤተ ክርስቲያን የቤተሰብ እና የጋብቻ ትስስርን ለማጠናከር እንደምትጥር ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ሳይንስ ጳጳሳዊ የሥነ-መለኮት ተቋም መምህራን እና ሠራተኞች ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር የካቶሊክ ዩኒቨርስቲዎች የተለያዩ ባሕሎች ጋብቻን እንዴት እንደሚመለከቱ ማጥናት እንዳለባቸው አሳስበው ቤተ ክርስቲያን የቤተሰብ እና የጋብቻ ትስስርን በማጠናከር ወደ ቅድስና ጎዳና ለመምራት እንደምትፈል ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ኅዳር 16/2017 ዓ. ም. ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ሳይንስ ጳጳሳዊ የሥነ-መለኮታዊ ተቋም መምህራን እና ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር በቤተ ክርስቲያን ሕይወት የቤተሰብን ማዕከላዊነትን አረጋግጠዋል።

“ጋብቻ እና ቤተሰብ ለሕዝቦች ሕይወት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆኑ እናውቃለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ቤተ ክርስቲያን ጋብቻን እና ቤተሰብን ሁል ጊዜ ተንከባክባቸዋለች፣ ትደግፋቸዋለች እና ወንጌልን ታስተምራቸዋለች” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ የማይገሰስ መብት፣ ክብር እና ነፃነት እንዳለው የማያምኑ እና የማያከብሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ያሉባቸው አገሮች አሉ” ሲሉ በምሬት ተናግረው፥ ይህ አመለካከት ከባድ ገደቦችን በሴቶች ላይ በማስቀመጥ ብዙውን ጊዜ በዝቅተኛ ሚና ብቻ እንዲገደቡ ያደርጋል” ብለዋል።

በወንድ እና በሴት መካከል ያለውን ልዩነት ከማጥፋት ይልቅ፣ በምላሹ ሁሉም ሰው የኢየሱስ ክርስቶስ እና የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ አካል በመሆናቸው በሁለቱ መካከል አድልዎ ሊኖር እንደማይችል ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምር ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ካለፉት ቁስሎች ጋር የሚሰቃዩትን ማገዝ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፥ የቤተሰብ ወንጌል የተመሠረተው በምስጢረ ተክሊል ላይ ስለሆነ የሁሉም ባህል ሰዎች በቅድስና እንዲያድጉ መንገድ እንደሚሰጥ አስረድተው፥ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በእምነት ጉዟቸው ለሚታገሉት በሮቿን በሰፊው ከፍታ መሐሪ እና የሚያበረታታ ሐዋርያዊ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን በደስታ እንደምትቀበላቸው ገልጸዋል።

“ፍቅር በቤተስብ ውስጥ” የሚለውን ሐዋርያዊ ምክራቸውን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጋብቻ ቁርጠኝነታቸውን ላልተወሰነ ጊዜ በማራዘም አብረው የሚኖሩትን፣ የተፋቱትን እና እንደገና ያገቡትን ሐዋርያዊ አገልጋዮች እንዲያግዟቸው ጠይቀው፥ “ሕመምን የሚቀሰቅሱ ገጠመኞች ቢኖራቸውም እንኳን በቤተ ክርስቲያን መታቀፋቸው በእምነት ለመጽናት ያላቸውን ፍላጎት ይመሰክራል” ብለዋል። በማከልም ቤተ ክርስቲያን ማንንም ወደ ጎን እንደማትል እና ሳታቋርጥ የቤተሰብን ታላቅነት ከማስተዋወቅ ባለፈ የጋብቻ ትስስርን በፍቅር ለማጠናከር እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

ስለ ባሕል፣ ስለ ጋብቻ እና ስለ ቤተሰብ ግንዛቤ ማጥናት
“ባሕል ሰዎች ለጋብቻ እና ለቤተሰብ ካላቸው አመለካከት ጋር በቅርበት የተሳሰረ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወንጌል አሁንም ባሕልን እየሰበከ በሰዎች ባሕል ላይ መመሥረት አለበት ብለዋል።“እነዚህን ተግዳሮቶች የመፍታት ችሎታችን እያንዳንዱን ክርስቲያን የሚያሳትፍ የቤተ ክርስቲያንን የወንጌል ተልዕኮ ሙሉ በሙሉ መፈጸም በምንችልበት መጠን ይወሰናል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የጋብቻ እና የቤተሰብ ሳይንስ ጳጳሳዊ የሥነ-መለኮት ተቋም ለዚህ ተልዕኮው የተለያዩ ማኅበረሰቦች እና ባሕሎች ጋብቻን እና ቤተሰብን እንዴት መገንዘብ እንዳለባቸው በመርዳት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ተቋሙ ባለ ትዳሮችን እና ቤተሰቦችን የቤተ ክርስቲያን ህያው ድንጋዮች እንዲሆኑ፣ የታማኝነት፣ የአገልግሎት፣ ለሕይወት ግልጽ እና የእንግዳ ተቀባይነት ምስክሮች እንዲሆኑ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያደርጉት ተልዕኮ ድጋፍ እንዲሆን በማሳሰብ የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ በመከተል ወደ ፊት አብረን እንጓዝ” በማለት ለተቋሙ መምህራን ብራታትን ተመኝተውላቸዋል።
 

26 November 2024, 16:03