ፈልግ

ከኑባ ተራሮች የተውጣጡ ሱዳናውያን ክርስቲያኖች በካርቱም ለተቃውሞ ተሰብስበው ከኑባ ተራሮች የተውጣጡ ሱዳናውያን ክርስቲያኖች በካርቱም ለተቃውሞ ተሰብስበው  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የዓለም ሰላም እና ስደት የደረሰባቸውን ክርስቲያኖች በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በግጭት ቀጣናዎች ሰላም እንዲሰፍን ጸሎት አቅርበው በኅበረተሰቡ የተገለሉትን መርዳት እንደሚገባ እና በሰዎች ላይ በሚደርስ ኢ-ፍትሐዊነት እና በሚፈጸም ጥቃት ላንይ ተጨባጭ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 8/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማጠቃለያ ለምእመናን ባደረጉት ንግግር፥ በማኅበረሰቡ ለተገለሉት እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሳስበው፥ በጦርነት እና በፍትህ እጦት የሚሰቃዩትን በሙሉ በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም ዙሪያ ጦርነቶች በቀጠሉበት በዚህ ወቅት ለምዕመናን ባቀረቡት ጥሪ ዩክሬንን፣ ፍልስጤምን፣ እስራኤልን፣ ሊባኖስን እና ምያንማርን በጸሎት እንዲያስታውሷቸው በመጠየቅ፥ “ጦርነት ሰብዓዊነትን የሚያጎድፍ እና ተቀባይነት የሌላቸውን ወንጀሎች የሚያስከት መሆኑን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምእመናን አስረድተዋል።

ድሆችን ማስታወስ
እሑድ ኅዳር 8/2017 ዓ. ም. ወደ ተከበረው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ሃሳባቸውን የመለሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከመጽሐፈ ሲራክ በተወሰደው የዕለቱ ምንባብ ጭብጥ ላይ በማሰላሰል፥ “የድሆች ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ይደርሳል” ብለዋል። በድህነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን ችግር ለመቅረፍ አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚሰጥ ገልጸው፥ በየሀገረ ስብከት እና በቁምስናዎች የሚገኙ ምዕመናን ለድሆች ለሚያደርጉት ዕርዳታ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተገኙት ምዕመናን በሙሉ በሥነ-ምግባራቸው እና በድርጊታቸው ላይ እንዲያሰላስሉ ጠይቀው፥ እያንዳንዱ ምዕመን በልቡ “ድሆችን ለመርዳት ወደ ኋላ እላለሁ? ምጽዋት በምሰጥበት ጊዜ ድሆችን እመለከታለሁ? በማለት ራሱን እንዲጠይቅ አሳስበው፥ ጊዜን ሳያባክኑ ድሆችን መርዳት እንደሚገባ እና ዘወትር በልግስና እና በርህራሄ ሌሎችን በመርዳት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል

ሰማዕታትን ማክበር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብጽዕነታቸው የታወጀላቸውን ሦስት ሰማዕታት በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ በሃይማኖት ላይ ስደት በደረሰበት ወቅት እምነታቸውን በጽናት እና በድፍረት መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አልባኒያ ውስጥ በሽኮደር ግዛት ቤተ ክርስቲያንን በደረሳት ስደት የሕይወት መስዋዕትነትን የከፈሉትን እና ቅዳሜ ኅዳር 7/2017 ዓ. ም. ብጽዕናቸው የታወጀላቸውን ፍራንችስኮስዊ ካኅን አባ ሉዊጂ ፓሊች እና የሀገረ ስብከት ካኅን አባ ግዮን ጋዙሊን ጠቅሰዋል። ቅዱስነታቸው ቀጥለውም እሑድ ኅዳር 8/2017 ዓ. ም. ብጽዕናው የታወጀለትን እና በጀርመን የናዚን ጭቆና በመቃወም ለሰላም ምሥክር በመሆን ሕይወቱን የተሰዋውን አባ ማክስ ፍሬይበርግ ሜትዝገርን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ እነዚህን ሰማዕታት እንደ ብርታት ምንጭ እንዲመለቷቸው አሳስበው፥ በተለይም በእምነታቸው ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ አድልዎ የሚደረሰባቸውን ክርስቲያኖች የእነዚህ ሰማዕታት ምሳሌነት እንደሚያጽናናቸው አስረድተዋል።

ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸውን አስታውሰዋል
ሰኞ ኅዳር 9/2017 ዓ. ም. የሚከበረውን፣ በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ወሲባዊ ብዝበዛን ለመከላከል እና ሰለባዎችን ለመፈወስ በሚል ዓላማ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ቀንን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዕለቱን ለማክበር ከመላዋ ቤተ ክርስቲያን ጋር እንደሚተባበሩ አስታውቀዋል። እያንዳንዱ በደል “እምነትን እና ሕይወትን መካድ ነው” በማለት ገልጸው፥ የተበላሸውን እምነት ለመመለስ ጸሎት አስፈላጊ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዓሳ አጥማጆችን አስታውሰዋል
ሐሙስ ኅዳር 12/2017 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የዓሳ አጥማጆች ቀንን በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ዓሣ አጥማጆችን እና ቤተሰቦቻቸው በጸሎት አስታውሰው፥ዓሳ አጥማጆችን በሥራቸው ወቅት እንድትጠብቃቸው በማለት የባሕር ኮከብ ወደ ሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

በጉዞ ላይ አደጋ የደረሰባቸውን አስታውሰዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም በመንገድ አደጋ የተጎዱትንም በጸሎት አስታውሰው፥እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎችን ለማስወገድ የሚቻለውን ጥረት ከማድረግ በፊት በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡትን እና እንዲሁም ያሐዘኑ ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

 

18 November 2024, 16:18