ፈልግ

ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን መልዕክት ለጉባኤው በንባብ ሲያቀርቡ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን መልዕክት ለጉባኤው በንባብ ሲያቀርቡ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ረሃብን ለማጥፋት ፈጣን እና ወሳኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ትብብርን በማስመልከት በብራዚል ለተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው አስተናጋጅ አገር ፕሬዝደንት በላኩት መልዕክት ረሃብን እና ድህነትን ከዓለማችን ለማስወገድ ፈጣን እና የተባበረ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉባኤው በላኩት መልዕክት፥ ዛሬ በዓለማችን ለተከሰቱት ግጭቶች እና ለጦር መሣሪያ ግዥ የሚውለው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቂ እና የተመጣጠነ ምግብ የሌላቸውን ሦስት ቢሊዮን ሰዎች መመገብ ይችል ነበር ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለብራዚሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የላኩትን መልዕክት ለጉባኤው በንባብ ያሰሙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ናቸው።ብራዚል ከኅዳር 9-10/2017 ዓ. ም. የተካሄደውን የቡድን 20፣ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት መሪዎች የተገኙበትን የ2 ቀናት ጉባኤ በሪዮ ዲጄኔሮ ማስተናገዷ ታውቋል።

የተሻለ ዓለምን ለመገንባት አስተዋጽዖ ማድረግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችንስኮስ የቡድን 20 ሊቀ መንበር በመሆን ስብሰባው እንዲካሄድ ላመቻቹትለብራዚሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ መልካምን ተመኝተው፥ የጉባኤው ውጤት ለመጪው ትውልድ የበለፀገች እና የተሻለች ዓለምን ለመገንባት እውነተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ያላቸውን ተስፋ ገልጸው ለጉባኤው ተሳታፊዎች በሙሉ ሰላምታ አቅርበዋል።

የረሃብ ቅሌት በዓለማችን ይብቃ!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ እየተሰቃዩ እና እየሞቱ ባሉበት በዚህ ወቅት ከዓለማችን ላይ ረሃብን በማስወገድ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተው፥ በብዙ ቶን የሚቆጠር እህል እየባከነ መሆኑ እውነተኛ ቅሌት እንደሆነ ተናግረው፥ “ረሃብ ወንጀል መሆኑን እና በቂ ምግብ ማግኘት የሰው ልጅ የማይገረሰስ መብት ነው” የሚለውን “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በማለት ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ መልዕክት በመጥቀስ አበክረው ተናግረዋል።

ጦርነትን ቆሞ ዘላቂ ሰላም መፍጠር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት፣ በግጭት እና በፍትህ መጓደል ምክንያት የተከሰቱ በርካታ ችግሮች መኖራቸው አምነው፥ በእነዚህ ማኅበራዊ ችግሮች ለተጎዱት ሰዎች ክብራቸውን ለመመለስ በማሰብ በሁሉም አካባቢዎች የተረጋጋና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አዳዲስ መንገዶችን መፈለግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። በነዚህ ጦርነቶች እየደረሰ ያለው ሞትና ውድመትም ለረሃብና ለድህነት መባባስ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፣ ከግጭቶቹ ርቀው የሚገኙ ቦታዎችን ጨምሮ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና ለጦር መሣሪያ ትጥቅ የሚውለው ከፍተኛ ገንዘብ ጉዳቱን የከፋ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የረሃብን አሳዛኝ ሁኔታ ለሌሎች ማሳወቅ
“ዛሬ በጣም የሚያሳስበን ጉዳይ ዓለም ዛሬም ቢሆን የረሃብን አሳዛኝ ሁኔታ መቋቋም የሚቻልባቸውን መንገዶች አለማወቁ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ይህ ዝምታ ተቀባይነት የሌለው አሳፋሪ ግፍ እና ከባድ በደል ነው” ሲሉ ገልጸውታል። “በተለይ በስግብግብነት የወንድሞቻቸውን እና የእህቶቻቸውን ሕይወት በረሃብ ማሰቃየት ነፍስ ማጥፋት ነው” ብለው፥ በመሆኑም “ሕዝቡን ከድህነት እና ከረሃብ ለማውጣት የሚያግዝ ምንም ዓይነት ጥረት እና ዘዴ ወደ ኋላ ሊባል አይገባም” ሲሉ አሳስበዋል።

ድህነት የረሃብ ቀውስን ያስከትላል
ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኢፍትሃዊነት የረሃብን እውነታ እንደሚያባባስ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ ድህነት "በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ውስጥ የተንሰራፋውን የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እኩልነት ዑደት ሊያደናቅፍ እንደሚችል አስረድተዋል። “በመሆኑም የረሃብና የድህነት መቅሰፍት ለማስወገድ ፈጣን እና ወሳኝ እርምጃን በመወሰድ፣ በመሰል ርምጃዎች መላውን ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በማሳተፍ በጋራ እና በመተባበር መከናወን አለባቸው” ብለዋል።

ውጤታማ እርምጃዎችን ለመውሰድ የመንግሥታት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ባጠቃላይ የኅብረተሰቡ ተጨባጭ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው ሲገልጹ፥ ይህም ለኑሮ መሠረታዊ የሆኑ ሸቀጦችን ማግኘት፣ እግዚአብሔር የሰጠውን የእያንዳንዱን ሰው ክብር የሚያስጠብቅ የአስፈላጊ ሃብቶች ፍትሐዊ ስርጭትን የሚያጠቃልል መሆኑን አስረድተዋል።

የምግብ መባከንን መቋቋም
የምግብ መባከን ችግርን ለመፍታት የጋራ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ቅዱስነታቸው ጠቁመዋል፣ ዛሬም ቢሆን ለሁሉም ሰው የሚሆን በቂ ምግብ ቢኖርም ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች በእኩል ደረጃ አለመሰራጨቱን በመናገር እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የሚደረገው ጥረት የረዥም ጊዜ ራዕይ እና ስትራቴጂን ይጠይቃል ብለዋል።

ለዚህም ረሃብን እና ድህነት ከዓለማችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ግሎባል አሊያንስ ርሃብን እና ድህነትን በመቅረፍ ረገድ ቁልፍ ሚናን መጫወት እንዲችል፣ የቅድስት መንበር የረዥም ጊዜ ዕቅድ ተግባራዊ በማድረግም፣ በአሁኑ ወቅት ለጦር መሣሪያዎች እና ለሌሎች ወታደራዊ ወጭዎች የተመደበው ገንዘብ ረሃብን ለመቅረፍ እና እጅግ ድሃ በሆኑ አገሮች ውስጥ ልማትን ለማስፋፋት የተነደፈ ዓለም አቀፍ ፈንድ ወጪ እንዲመለስ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።

“የርዕዮተ ዓለም ቅኝ አገዛዝን” ማስወገድ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የውጭ አገራት ጫና የሌለባቸው የልማት ውጥኖች አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት ለሕዝቡ እና ለማኅበረሰባቸው ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት የታቀዱ የልማት ውጥኖች ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ቅድስት መንበር የሰውን ልጅ ክብር ለማስተዋወቅ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ተቋማትን ልምድ በማካፈል የራሷን አስተዋጽዖ ለማበርከት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል በማረጋገጥ፥ “በዓለማችን ውስጥ በእግዚአብሔር የተወደደ እያንዳንዱ ሰው የዕለት እንጀራውን መነፈግ የለበትም” ብለዋል።

ለጉባኤው ተሳታፊዎች በላኩት ማበረታቻም፥ “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ለመላው የሰው ልጅ እውነተኛ ዕድገት ለማምጣት የሚያደርጓቸውን ሥራዎች እና ጥረቶች አብዝቶ ይባርክ!” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

19 November 2024, 16:42