ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ሕጻናትን በመስጠት ተዓምራትን ለሚያደርግ እግዚአብሔር ምስጋናን እናቅርብ!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ታኅሳስ 13/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች፥ በዕለቱ ምንባብ ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ከቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሰሙት ስብከት፥ “ሕጻናትን በመስጠት ተአምር ለሚያደርግ እግዚአብሔር ምስጋናችንን እናቅርብ” ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን የቅዱስነታቸውን ስብከት ሙሉ ትርጉም ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞች እና እህቶች እንደምን አረፈዳችሁ! ከሉቃ. 1፡39-35 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ወንጌል፥ ከመልአኩ ገብርኤል ብስራት በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያም በዕድሜ ታላቋን እና ነፍሰ ጡር የነበረችው ዘመድዋን ኤልሳቤጥን እንደጎበኘቻት ይናገራል። ግንኝነታቸው የእናትነት ልዩ ስጦታን የተቀበሉት ሁለት ሴቶች የሚደሰቱበት ግንኝነት ነው። ድንግል ማርያም የዓለም አዳኝ የሆነው ኢየሱስን ጸንሳለች (ሉቃ. 1፡31-35)። ኤልሳቤጥ ምንም እንኳን እርጅና ቢኖራትም ለመሲሑ የመምጫ መንገድ የሚያዘጋጅ መጥምቁ ዮሐንስን በሆዷ ተሸክማለች (ሉቃስ 1፡13-17)።

ሁለቱም አብረው የሚደሰቱባቸው ብዙ ነገሮች አሏቸው። ምናልባት በሕይወታችን ውስጥ የማናገኛቸው የታላላቅ ተአምራት ዕድለኞች እንደሆኑ ይሰማን ይሆናል። ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ከብርሃነ ልደቱ በዓል ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሊሰጠን የሚፈልገው የተለየ መልዕክት ይህ ነው። በእውነቱ የእግዚአብሔርን የማዳን ተግባር ተአምራዊ ምልክቶችን ማሰላሰላችን ለእርሱ ቅርብ መሆናችን እንዲሰማን ሊያደርገን ይገባል። ይልቁንም እርሱ ከእኛ ጋር መሆኑን እና ለእኛ ያለውን ፍቅር መገንዘብ እንድንችል ያግዘናል። እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ሕይወት፣ በእያንዳንዱ ሕጻን ወይም እናት በኩል የሕይወት ስጦታው እንዲገለጽ ያደርጋል። ማንኛውም ሕጻን ከእግዚአብሔር የተገኘ የሕይወት ስጦታ እንጂ በስሕተት የተገኘ አይደለም።

ዛሬም ቢሆን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ እናቶች ከልጆቻቸው ጋር መጥተዋል። ምናልባትም አንዳንዶቹ ነፍሰ ጡር ናቸው። እባካችሁ ለነፍሰ ጡሮች ግድየለሾች አንሁን። ውበታቸውን ማድነቅ እንማር። ውበታቸው ልክ እንደ ኤልሳቤጥ እና ማርያም የወደፊት እናትነት ውበት ነው። እናቶችን እንባርክ! ስለ ሕይወት ተአምር እግዚአብሔርን እናመስግን! ነፍሰ ጡሮችን ማየት እወድ ነበር። በሌላ ሀገረ ስብከት በመንገደኞች ማመላለሻ አውቶቡስ ተሳፍሬ ስሄድ ነፍሰ ጡር እናት አውቶብስ ውስጥ ስትገባ የተቀመጥኩበትን ወንበር ወዲያውኑ እሰጣት ነበር። ይህም የተስፋ እና የአክብሮት ምልክት ነው!

ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! በእነዚህ ቀናት ውስጥ ብርሃነ ልደቱን ልዩ ልዩ ቀለማት ያሏቸውን መብራቶች በማብራት፣ ጌጣጌጦችን በመሰብሰብ እና ዝማሬዎችን በማቅረብ የበዓል ድባብ መፍጠር እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ልጅን በእቅፏ ወይም በማኅፀንዋ ውስጥ የተሸከመች አንዲት እናት ስናገኝ በውስጣችን ያለውን የደስታ ስሜት መግለጽ እንደሚገባ እናስታውስ። ይህ ስጦታ እኛ ላይ ሲደርስ ደግሞ እንደ ኤልሳቤጥ በልባችን እንጸልይ። 'አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው!' እንበል (ሉቃስ 1:42)። እናትነት ሁሉ የተባረከ ይሆን ዘንድ እንደ ማርያም “ነፍሴ የጌታን ታላቅነት ትናገራለች” (ሉቃስ 1፡46) ብለን እንዘምር። በዓለማችን የሚገኙ ወንዶች እና ሴቶች ልጆችን እንዲወልዱ ስልጣን የሰጣቸው እግዚአብሔር የተመሰገነ እና የተከበረ ይሁን!

ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ይዛችኋቸው የመጣችሁትን የሕጻኑ ኢየሱስ ምስሎች እንባርካለን። እኔም ከዚህ በፊት ከአንድ ጳጳስ በስጦታነት የተሰጠኝን የሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል አምጥቼአለሁ። ምስሉ የተሠራውም በኤኳዶር ነው። ራሳችንን እንዲህ በማለት ልንጠይቅ እንችላለን። ከኃጢአት በቀር በሕይወታችን ሁሉ ተካፋይ ለመሆን ራሱን እንደ እኛ ሰው ያደረገውን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁን? ስለተወለዱት ሕጻናት በሙሉ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፣ እባርከዋለሁ? ነፍሰ ጡር እናት ስታጋጥመኝ ደግ ነኝ? ገና ያልተወለዱ እና በእናቶች ማኅፀን ውስጥ ያለው ነፍስ ከተጸነሰበት ጊዜ ጀምሮ ቅዱስ መሆኑን አምናለሁ?”

ገና ሕፃን ከመወለዱ በፊት የሕይወትን ምሥጢር እንድንረዳ፥ እግዚአብሔር ለሚሰጠን የሕይወት ተአምራት ምስጋናን ማቅረብን እንድንለማመድ፥ ከሴቶች መካከል የተባረከች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትርዳን!
 

23 December 2024, 16:57