ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ሰላምን መፈለግ የሁሉ ሰው ኃላፊነት ነው” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 22/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረሱ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ “የመጣው የሰላም ጭላንጭል በሁሉም የጦር ግንባሮች ተኩስ ቆሞ ወደ ሰላም እንደሚያመራ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው፥ በሊባኖስ ውስጥ በሚገኝ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች እና በእስራኤል መካከል ለ13 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ጠቅሰዋል።
ይህን ዕድል በመጠቀም የሊባኖስ ሕዝብ ቶሎ ብሎ ፕሬዝዳንቱን እንዲመርጥ በማሳሰብ “በተቻለ ፍጥነት ተቋማቱ ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ፣ አስፈላጊውን ማሻሻያዎች እንዲያደርጉ እና አገሪቱ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች በሰላም አብረው የሚኖሩባት ምሳሌ ሆና እንድትቀጥል” በማለት አበረታትተዋል።
ሆኖም የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ ቀን በኋላ የእስራኤል አየር ኃይል በሂዝቦላህ ተቋም ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምር የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሷል ሲሉ እስራኤል እና ሂዝቦላ አንዱ ሌላውን ከሰዋል።
'ጦርነት እግዚአብሔርን የሚያስቆጣ ተግባር ነው'
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋዛን፣ ሶርያን እና ዩክሬንን ጨምሮ በግጭት ውስጥ በሚገኙ ሌሎች አካባቢዎችም ስጋት እንዳላቸው መግለጽን ቀጥለው፥ ጋዛ ውስጥ የሚገኙ እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲፈቱ እንዲሁም በጦርነት ከፍተኛ የሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም ለደረሰበት የፍልስጤም ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሰው በማለት በድጋሚ ተማጽነዋል።
በአውሮፓ ውስጥ የክረምት ወቅት መቃረቡን የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያህል በዘለቀው ጦርነት ዩክሬንን ከባድ መከራ የደረሳባት መሆኑን አስታውሰዋል። ጦርነት ከኃይለኛ ቅዝቃዜ ጋር ተዳምሮ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ተፈናቃይ ሰዎች ሕይወት አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ጦርነቱ ቆሞ ውይይትን፣ ወንድማማችነትን እና እርቅን ለማስፋፋት የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።
ሰላም የጥቂት ሰዎች ኃላፊነት ብቻ አይደለም!
የብርሃነ ልደቱን ሰሞን መጀመሪያ እና በዓሉንም በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲናገሩ፥ በጦርነት በወደቁ አገራት ውስጥ ለሚሰቃዩት ሰዎች ዕርዳታን እና ተስፋን ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶች ይበልጥ እንዲጠነክሩ ጠይቀው፥ “ሰላምን መፈለግ የጥቂቶች ሳይሆን የሁሉም ሰው ኃላፊነት ነው” ሲል ተናግረዋል።
በደቡብ አሜሪካ ውስጥ የታየ ወሳኝ ክስተት
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ኅዳር 29/1984 በአርጀንቲና እና በቺሊ መካከል የተፈረመውን የሰላም እና የወዳጅነት ስምምነት 40ኛ ዓመት መታሰቢያን ያከበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ቅድስት መንበር ባደረጉት ሽምግልና በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የግዛት ይገባኛል ውዝግብ እንዲቀንስ መደረጉ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ይህንን እንደ ምሳሌ በመጠቀም፥ “የጦር መሣሪያን አስቀምጠን ወደ ውይይት የምንገባ ከሆነ በትክክለኛው መንገድ መጓዝ እንችላለን” ብለዋል።