ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የሶርያ ሕዝብ አደራን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሰጡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በሶርያ እየተባባሰ የመጣውን ብጥብጥ እና የአሳድ መንግሥት ውድቀት ተከትሎ በሀገሪቱ ውስጥ በየቀኑ እየተፈጠረ ያለውን ቀውስ በቅርብ እንደሚከታተሉ የተናገሩት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በሳምንታዊው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ለታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር፥ አገሪቱ በታሪኳ አሳስቢ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደምትገኝ በመግለጽ ለሕዝቡ ደኅንነት እና ሰላም ጸልየዋል።
የሰላም ጸሎት
“በውጭ አገራት የሚኖሩ በርካታ ሶርያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ ተጨማሪ ግጭት እና መከፋፈል ሳይከሰት፥ በአገሪቱ ውስጥ መረጋጋትን እና አንድነትን የሚያጎለብት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲገኝ” በማለት ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓመታዊው የጉዋዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓል የዋዜማ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባቀረቡት ጸሎት፥ የሶርያ ሕዝብን ለእመቤታችን ድንግል ማርያም በአደራ ሰጥተው፥ “በእርሷ አማላጅነት ዜጎች በሚወዷት አገራቸው ውስጥ ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሰላም እንዲኖሩ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። በሶርያ የሚኖሩት ልዩ ልዩ የሃይማኖት ቡድኖች፥ ከእነዚህም መካከል 70% የሱኒ ሙስሊም ማኅበረሰብ፣ 13% የሺዓ ሙስሊም ማኅበረሰብ እና 2% የሚሆን ክርስቲያን ማኅበረሰብ ለአራቸው ጥቅም ሲሉ በመዋደድ እና እርስ በርስ በመከባበር አብረው እንዲኖሩ” የእመቤታችንን አማላጅነት ጠይቀዋል።
አዲስ ሽግግር
በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የሶርያ ዋና አማፂ ቡድን ሀያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) ዋና ዋና ከተሞችን እና መዲናዋ ደማስቆን ተቆጣጥሮ የሽግግር መንግሥቱን የሚመራ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾሙ ታውቋል። በዚህም አገሪቱን ለ13 ዓመታት የመራው የበሽር አል-አሳድ አገዛዝ እና የአምስት አሥርት ዓመታት የአሳድ ቤተሰብ ሥርወ መንግሥትም ማብቃቱ ታውቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ለ48 ሰዓታት በሶርያ ላይ በፈጸመው ጥቃት፥ ስልታዊ የጦር መሣሪያ ማከማቻ ያሏቸውን ሥፍራዎች ያነጣጠሩ ከ350 በላይ የአየር ጥቃቶች መፈጸሙን አስታውቋል።
በጦርነት ውስጥ የሚገኙትን በጸሎት ማስታወስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጦርነት የተመሰቃቀሉትን፥ ዩክሬንን፣ ፍልስጤምን፣ እስራኤልን እና ምያንማርን በጸሎታቸው አስታውሰው፥ ሁሉም ሰው ለዓለም ሰላም እንዲጸልይ በድጋሚ አደራ በማለት፥ ዓለማችን ከጦርነት ወጥቶ ወደ ሰላም የሚመለስበትን መንገድ እንዲያገኝ እንጸልይ” በማለት አሳስበዋል።