ር.ሊ.ጳ ፍራንችስኮስ 'ከእንግዲህ በጦር መሣሪያ ሰዎችን በቅኝ ግዛት መገዛት አይቻልም!' አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
"ለሁላችሁምን እንኳን ለገና በዓል አደረሳችሁ። በእነዚህ ቀናት ብዙ መልዕክቶች እና የመቀራረብ ምልክቶች ደርሰውኛል አመሰግናለሁ። ሁሉንም ሰው፣ እያንዳንዱን ቤተሰብ፣ አጥቢያ እና ማኅበራትን ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ። ሁላችሁንም አመሰግናለሁ!" ብለዋል ቅዱስነታቸው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በገና ማግስት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምእመናን በዚህ በታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም የቅዱስ እስጢፋኖስ በዓል፣ የመጀመሪያው ክርስቲያን ሰማዕት፣ እየተከበረ መሆኑን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በአለም ዙሪያ በጦርነት ለሚሰቃዩ፣ ለሚሰደዱ እና ለሚገደሉ ክርስቲያኖች ቅዱስ እስጢፋኖች አማላጃቸው እንዲሆን ቅዱስነታቸው ተማጽነዋል።
ኢየሱስን ለመገናኘት ኢዮቤልዩ
በመቀጠልም ከኢጣሊያ እና ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ ምዕመናን ሰላምታ አቅርበው "ብዙዎቻችሁ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ቅዱስ በር በመግባት የኢዮቤልዩ ጉዞ እንዳደረጋችሁ አስባለሁ" በማለት ተናግሯል።
“የሕይወታችንን ትርጉም የሚገልጽ፣ የሚወደንን ኢየሱስን ለመገናኘት መሄድ” እና “ወደ ፍቅር፣ ደስታ እና ሰላም መንግሥት እንድንገባ የሚፈቅድልን ይህ ምልክት ነው” በማለት ሐሳብ አቅርቧል።
በዚህ ጊዜ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከጥቂት ሰአታት በፊት በሮማ ሬቢቢያ እስር ቤት ቅዱስ በር እንደከፈቱ አስታውሰዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የቅዱስ በር ከተከፈተ በኋላ በታህሳስ 15/2017 ዓ.ም የኢዮቤልዩ አመት በይፋ ሲከፈት መፈጸሙን በማስታወስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ በእስር ቤት ያሳለፉትን ጊዜ “በህመም እና በተስፋ ካቴድራል” ውስጥ እንዳሉ እንደ ተሰማቸው ተናግረዋል ።
"ዕዳ ወደ ተስፋ መለወጥ"
ኢዮቤልዩ ከሚገለጽባቸው ተግባራት ውስጥ አንዱ የዕዳ ስርየት መሆኑን ያስታወሱት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ “በመሆኑም ካሪታስ ኢንተርናሽናልሊስ “ዕዳን ወደ ተስፋ መለወጥ” በሚል ርዕስ የጀመረውን ዘመቻ ሁሉም ሰው እንዲደግፈው እና በከፍተኛ ዕዳ የተጨቆኑ አገሮችን ዕዳ ለማቃለል እና ልማትን እንዲያበረታታ አበረታታለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።
የዕዳ ጉዳይ በጥቅሉ ከሰላም እና ከ“ጥቁር ገበያ” የጦር መሣሪያ ጋር የተያያዘ መሆኑን በመግለጽ “ሕዝብን በጦር መሣሪያ ቅኝ መገዛት ይቁም!” ሲሉ ተማጽነዋል።
ለአለም ሁሉ ሰላም ጸሎት
"ትጥቅ ለማስፈታት እንስራ፣ ረሃብን ለመከላከል፣ በበሽታዎች ላይ፣ በህፃናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ እንስራ" እንዲሁም "በመላው አለም በተለይም በጦርነት በተመሰቃቀለው ዩክሬን፣ ጋዛ፣ እስራኤል፣ ምያንማር፣ ሰሜን ኪቩ እና በጦርነት ውስጥ ያሉ ሌሎች በርካታ አገሮች ቅዱስነታቸው በጸሎታቸው አስታውሰዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምእመናን በሙሉ በዚህ ሁለተኛ የገና ቀን መልካም በዓል ከተመኙ በኋላ እና ለእርሳቸው እንዲጸልዩላቸው ካሳሰቡ በኋላ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።