ፈልግ

ቤተልሔም ቤተልሔም  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በቤተልሔም የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ወድ የእምነት ስጦታውን እንዲጠብቅ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ለቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በላኩት የገና ሰሞን መልዕክት፥ ተማሪዎቹ ሁሉን ነገር ለኢየሱስ ክርስቶስ አደራ እንዲሰጡ እና ውድ የእምነትን ስጦታቸውን ጠብቀው እንዲያቆዩ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአውሮፓውያኑ የገና በዓል ቀደም ብሎ ታኅሳስ 11/2017 ዓ. ም. ለቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በላኩት መልዕክት፥ ተማሪዎቹ የእምነት ስጦታን እንዲጠብቁ እና በጸሎት ሁሉንም ነገር ለኢየሱስ ክርስቶስ አደራ እንዲሰጡ በማለት ሁለት ምክሮችን ለግሠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ቻንስለር ለሆኑት ወንድም ሄክቶር ሄርናን ሳንቶስ ጎንዛሌዝ በላኩት ልባዊ ሰላምታቸው ለዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች እና ተማሪዎች ያላቸውን መንፈሳዊ ቅርበት ገልጸዋል።

“መላዋ ቤተ ክርስቲያን የኢዮቤልዩ ዓመት መጀመሪያ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለማክበር በምትዘጋጅበት ወቅት” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “አዲስ ሕይወትን፣ ተስፋን እና ዕርቅን የሚያመለክቱ እነዚህ አጋጣሚዎች፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ደስተኛ ደቀ መዛሙርት እንድትሆኑ በቀረበላችሁ ጥሪ ውስጥ መንፈሳዊ ለውጥን እና ጽናትን ለማበረታታት ዕድሎችን እንዲሰጡአችሁ እጸልያለሁ” ብለዋል።

“ውድ የሆነውን የእምነት ስጦታችሁን ጠብቁ!”
ቅዱስነታቸው በዩኒቨርሲቲው ለሚገኙ ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “በተለይም ዘወትር ውድ የሆነውን የእምነት ስጦታችሁን ተንከባክባችሁ በማቆየት ሳትደብቁት ከሌሎች ጋር ለጋራ መጠቀሚያ አውሉት” ብለዋል።

“ምንም እንኳን በወጣትነት ዕድሜያችሁ አንዳንድ ጊዜ ድካም፣ ግራ መጋባት ወይም ተስፋ መቁረጥ ሊሰማችሁ ቢችልም ሁሉንም ነገር የዘላለም ተስፋ ምንጭ ለሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎት አደራ ስጡ” ብለው፥ ከዚህም በላይ ሕይወትን አትረፍርፎ የሚስጥ እርሱ ወጣትነታችሁን ጠቃሚ እንድታደርጉ ይረዳችኋል” ሲሉ አረጋግጠዋል።

“በጭራሽ ብቻችሁን አትጓዙ!”
ቅዱስነታቸው ከዚሁም ጋር ወጣቶቹ ፈጽሞ ብቻቸውን እንዳይጓዙ፥ ይልቁንም ትምህርታዊ እና ማኅበራዊ የወዳጅነት ትስስር እንዲፈጥሩ አሳስበው፥ “በእርግጥ ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በአመጽ ሁኔታ እየተጎዱ ባሉበት በዚህ ጊዜ ሰብዓዊ ቤተሰባችን በተስፋ የተሞላ አብሮነትን ይፈልጋል” ብለዋል።

በዚህ ረገድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘመናት የቆዩትን የወንጌል እሴቶችን፥ የተለያየ እምነትና ወግ ላላቸው የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች ምሳሌ ሆነው እንዲያገለግላቸው በጋለ ስሜት እንዲመሰክሩላቸው ተማሪዎችን አበረትተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ደስታ እና ሰላም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፥ ተማሪዎቹ በዚህ መልኩ ዘላቂ ውይይትን፣ የጋራ መግባባትን እና በወንድማማችነት አብሮ በሰላም የመኖር ባህልን መገንባት እንደሚችሉ ገልጸው፥ “በዚህ ስሜት የቤተልሔም ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችን እና ተማሪዎችን የቤተ ክርስቲያን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም እንድትጠብቃት ተማጽነው፥ “ቃል ሥጋ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደስታን እና ሰላምን እመኝላችኋለሁ” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

28 December 2024, 13:36