ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሜቶዲስት እምነት ተከታዮች፥ እርቅ ‘የልብ ሥራ ነው” ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ ታኅሳስ 7/2017 ዓ. ም. ወደ ቫቲካን ከመጡት በርካታ የዓለም የ ሜቶዲስት ቤተ እምነት ምክር ቤት አባላት ጋር ተገናኝተዋል። ቤተ እምነቱ ባሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ ወደ 80 የሚጠጉ ቤተ ክርስቲያናት ያሉት እና ወደ 80 ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናንን የሚወክል እንደሆነ ይታወቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለልኡካን ቡድኑ ንግግር ባደረጉ ጊዜ እግዚአብሔርን አመስግነው፥ ካቶሊኮች እና ሜቶዲስቶች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በማሸነፍ ላለፉት 60 ዓመታት እርስ በርስ ዕውቀቶችን፣ መግባባትን እና ፍቅርን ለመለዋወጥ ጥረት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
“ራሳችንን ክፍት ማድረጋችን ይበልጥ እንድንቀራረብ በማድረግ እና እርቅም የልብ ሥራ መሆኑን እንድንገነዘብ አድርጎናል” ብለው “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ልባችንን ሲነካ ይለውጠናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሜቶዲስቶች እና ካቶሊኮች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተለያዩ አእምሮአቸውን እና ፈቃዶቻቸውን አንድ ለማድረግ እንዲመኙ ጋብዘዋል።
“ይህ ጉዞ ጊዜን የሚወስድ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ነገር ግን ምንም ቢሆን ሁልጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ላይ በማተኮር፣ እርስ በርሳችን በጥሩ መንገድ የምንተሳሰበው እና የእግዚአብሔርን መንግሥት ማገልገል የምንማረው ከዚህ ስለሆነ በዚህ መንገድ መቀጠል አለብን” በማለት ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ክርስቲያኖችን በኒቂያ ጸሎተ ሃይማኖት ዙሪያ ያሰባሰበ የመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ 1,700ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት መሆኑን አስታውሰዋል።
ሜቶዲስቶች እና ካቶሊኮች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ተመሳሳይ እምነት እንዳላቸው በመግለጽ “እግዚአብሔር ወደ ዓለም መምጣቱን የሚመሠክሩ የተስፋ ምልክቶችን የማቅረብ ኃላፊነት አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማጠቃለያቸው፥ በዓለም ዓቀፍ የሜቶዲስት ቤተ እምነት ምክር ቤት እና በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው ዓለም አቀፍ የጋራ የውይይት ኮሚሽን ውስጥ ያገለገሉትን የነገረ መለኮት ሊቃውንት እና መጋቢዎችን አመስግነዋል።
የልኡካን ቡድኑን “ውድ እህቶቼ እና ወንድሞቼ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እንግዶቹ ወደ ቫቲካን መጥተው ስላደርጉት ጉብኝት ልባዊ ምስጋናቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ “በጸሎት እንተባበር” በማለት መልካም የብርሃነ ልደቱ በዓልን ተመኝተውላቸዋል።