ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኢዮቤልዩ ዓመት ሁሉም የጦር ግንባሮች ተኩስ የሚያቆሙበት እንዲሆን ተመኝተዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጽሐፉ መግቢያ እንዲሆን ባበረከቱት ጽሑፋቸው፥ ቅዱስ ዓመት ሰላም የሰፈነበት ዓለምን እንደሚያሳይ ተስፋ በማድረግ የጦር መሣሪያዎች ድምጽ ጸጥ የሚልበት፣ የጦር መሣሪያውን የሚያመርቱትም ከሰዎች ሞት የሚያገኙት ትርፍ እንዲቆም፣ የሞት ቅጣት ተወግዶ እስረኞች ምህረት ተደርጎላቸው ነጻ እንዲወጡ የሚሉት በመቅድም ጽሑፋቸው ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የኢዮቤልዩ በዓልን በሙላት ማክበር
“መጪው የኢዮቤልዩ ዓመት ጦርነት በሚካሄድባቸው አገሮች ሁሉ ተኩስ ለማቆም ዕድል እንደሚሰጥ ተስፋ አደርጋለሁ!” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህን ጥሪ በአብዛኛው ንግግራቸው ግልጽ እንዳደረጉት አጽንዖት ሰጥተዋል። “ከጦርነት እና ከግጭት የሚያተርፍ ማንም የለም! ሁሉም ወገን ተሸናፊ ነው!”፣ “ተስፋ አያሳዝንም” በማለት ቅዱስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ይፋ ያደረጉትን መልዕክት በማስታወስ አበክረው ገልጸዋል።
“ተስፋ አጠራጣሪ ወይም ስለ ወደፊቱ ግልጽ ያልሆነ አዎንታዊ ስሜት የሚታይበት ሳይሆን ከዚህ የተለየ ነው” በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው በመቀጥልም፥ ተስፋ ምናባዊ ወይም ስሜታዊ ሳይሆን ነገር ግን ተጨባጭ በጎነት እና የሕይወት መንገድ፣ ተጨባጭ ምርጫዎችን የሚያካትት፣ በእያንዳንዱ ሰው መልካም ቁርጠኝነት የሚያድግ፣ በማኅበራዊ፣ ምሁራዊ፣ መንፈሳዊ፣ ኪነ ጥበባዊ እና ፖለቲካዊ ተግባር ውስጥ ከፍተኛ ትርጉም እና ጠቀሜታ ያለው ነው” ሲሉ አስረድተው፥ የአንድ ሰው አቅም እና ሃብት ለጋራ ጥቅም እንዲውል የሚያደርግ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ተስፋ የጸጋ መሣሪያ ነው!
ይህ ማለት “የተስፋ ጉዞ” እየተባለ የሚጠራው እና ስደተኞችን ከሚያጋጥማቸው አስጨናቂ ጉዞ ጋር በተገናኘ በጋራ ጥቅም ላይ የሚያተኮር እና ብዙውን ጊዜ እውነተኛ ተስፋ መቁረጥ የሚታይበት እና “ታላቅ መቃብር” በመባል ወደሚታወቅ የሜዲትራኒያን የባሕር ላይ ጉዞ እንደሚቀየር የሚገልጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በእስር የሚማቅቁት ነጻ እንዲወጡ ካላቸው ምኞት እና የሞት ቅጣትን ከማስወገድ ጎን ለጎን “እነዚህ በሙሉ የሰውን ልጅ የማይጣስ ክብር የሚጋፏ በመሆናቸው ተቀባይነት የላቸውም” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመጽሐፉ እንደ መግቢያነት ባበረከቱት ጽሑፋቸው፥ “የተሳፋ ኢዮቤልዩ” በቀን መቁጠሪያነት ብቻ የተደነገገ ክስተት ሳይሆን ነገር ግን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1300 ጀምሮ በነበሩት ዓመታት ውስጥ ጊዜው በሚጠይቀው መንገድ ቤተ ክርስቲያንን የመራት እውነተኛ ሐዋርያዊ መሣሪያ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
ዳግም የሚወለዱበት ጊዜ
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጭው 2025 ቅዱስ ዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናን በቫቲካን የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በር እና በሮም ውስጥ በሚገኙ ሌሎች ሦስት ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች በር የሚያቋርጡበት ዓመት ይሆናል። በዚህም መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመላው ዓለም ም ዕመናን ወደ ሮም የሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ እንደ ኦሎምፒክ ውድድር የአንድ ግብ ስኬት ወይም ለአገር ጉብኝት የሚደረግ ጉዞ እንደማይሆን ተስፋ እድርገዋል። ቅዱስነታቸው በጽሑፋቸው “በእርግጥ የመለወጥ አጋጣሚ፣ ሕይወትን ከወንጌል አኳያ የምንመለከትበት እና ይህ መንፈሳዊ ጉዞ ዘወትር በሚስጥር በሚደረግ የበጎ አድራጎት ተግባር የታጀበ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
መጽሐፉ በተጨማሪም በኢዮቤልዩ ዓመት ቅድስናቸው የሚታወጅላቸውን ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲ እና ካርሎ አኩቲስ የተባሉትን ሁለት ወጣቶችን አስታውሷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእነዚህ የሁለት ወጣቶችን ምሳሌ እና ቃላት በተደላደለ ሕይወት ተታልለን ሳናባክን ነገር ግን ኢየሱስ በልባችን ውስጥ ወደ አገልግሎት የሚለወጠውን የፍቅር ውበትን እንድንይዝ አሳስበዋል።