በደላችንን ይቅር በለን: ሰላምህን ስጠን
I. ለአደጋ የተጋለጠ የሰው ልጅ ልመና ማዳመጥ
1. በሰማያዊው አባታችን በተሰጠን በዚህ አዲስ አመት መግቢያ (የአውሮፓዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ማለት ነው)፣ የኢዮቤልዩ ዓመት በተስፋ መንፈስ፣ ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት ልባዊ መልካም የሰላም ምኞት አቀርባለሁ። በተለይ የተጨቆኑትን፣ በቀደሙት ስህተቶቻቸው የተነሳ ሸክም የበዛባቸውን፣ በሌሎች ፍርድ የተነሣ የተጨቆኑትን እና ለራሳቸው ህይወት የተስፋ ጭላንጭል እንኳን ማየት የማይችሉትን ሰዎች አስባለሁ። ለሁሉም ተስፋ እና ሰላም እለምናለሁ፣ ይህ ከአዳኙ ልብ የተወለደ የጸጋ ዓመት ነውና!
2. በዚህ አመት ውስጥ ሁሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢዮቤልዩ ታከብራለች፣ ይህም ልቦችንን በተስፋ የሚሞላ ክስተት ነው። “ኢዮቤልዩ” በየአርባ ዘጠነኛው ዓመት የአውራ በግ ቀንድ በመጠቀም (በዕብራይስጥ ቋንቋ 'ጆቤል') ለመላው ሕዝብ የይቅርታና የነፃነት ዓመት የሚታወጅበትን የጥንት የአይሁድ ልማድ ያስታውሳል (ዘሌ. 25፡10)። ይህ የተከበረ አዋጅ በምድሪቱ ላይ ለማስተጋባት የታሰበ ነበር (ዘሌ. 25፡9) እናም የእግዚአብሔርን ፍትህ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ላይ መልሶ ለማስፈን፣ በመሬት አጠቃቀም፣ በንብረት ይዞታ እና ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ከሁሉም በላይ ድሆች እና ርዕስታቸውን የተነጠቁትን ለመካስ የሚደረግ ነው። የመለከት ድምጽ በሚሰማበት ወቅት መላውን ሕዝብ፣ ባለጠጋም ሆነ ድሀ፣ ማንም ወደዚህ ዓለም ለጭቆና እንዳልመጣ አስታውሷል፡ ሁላችንም ወንድማማቾችና እህቶች፣ የአንድ አባት ወንድና ሴት ልጆች ነን፣ ከጌታ ፈቃድ ጋር በነጻነት እንድንኖር የተወለድን ነን (ዘሌ. 25፡17፣ 25፣ 43፣ 46፣ 55)።
3. በእኛም ዘመን፣ ኢዮቤልዩ በዓለማችን ላይ የእግዚአብሔርን ነጻ አውጭ ፍትህ ለመመስረት እንድንፈልግ የሚያነሳሳ ክስተት ነው። በበጉ ቀንድ ምትክ፣ በዚህ የጸጋ ዓመት መጀመሪያ ላይ “የእርዳታ ልመናን” እንደ አቤል ደም ጩኸት (ዘፍ. 4፡10) እንደሚነሳ መስማት እንፈልጋለን። ከብዙ የአለማችን ክፍሎች የሚመጡ - ለእግዚአብሔር መስማት የማይሳነው ልመና። እኛ በበኩላችን ምድር የተበዘበዘችበትን እና ጎረቤቶቻችን የተጨቆኑባቸውን በርካታ ሁኔታዎች በጩኸት መግለጽ እና ማውገዝ እንዳለብን ይሰማናል። እነዚህ ኢፍትሐዊ ድርጊቶች አንዳንድ ጊዜ ሊታዩ የሚችሉት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብለው እንደ ነበረ “የኃጢአት መዋቅር” ብሎ በጠሩት መልክ ሲሆን በአንዳንዶች ላይ ከሚደርሰው ግፍ ብቻ ሳይሆን በተባባሪነት መረብ የተጠናከረ እና የሚጠበቅ ነው።
4. በተዘዋዋሪም ቢሆን በአሁኑ ጊዜ ሰብዓዊ ቤተሰባችንን እያስጨነቁ ያሉትን ግጭቶች እንዲባባሱ ከሚያደርጉ ድርጊቶች ጀምሮ፣ የጋራ መኖሪያችን የሆነችው ምድር ለደረሰባት ውድመት እያንዳንዳችን በሆነ መንገድ ተጠያቂነት ሊሰማን ይገባል። የስርአት ተግዳሮቶች ፣የተለያዩ ግን እርስ በርስ የተሳሰሩ ፣ስለዚህ የተፈጠሩ እና አንድ ላይ ሆነው በዓለማችን ላይ ውድመት ያስከትላሉ። በተለይ ከሁሉም ልዩነቶች፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት፣ የአካባቢ ብክለት፣ በሐሰት መረጃ ሆን ተብሎ የተፈጠረው ግራ መጋባት፣ በማንኛውም ዓይነት ውይይት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆን እና ለጦር ኢንዱስትሪው የሚውለው ከፍተኛ ሀብት እነዚህ ጉዳዮች በተለይ እኔን ያሳስቡኛል። እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ተሰባስበው በአጠቃላይ የሰው ልጅ ህልውና ላይ ስጋት ይፈጥራሉ። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ በአንድነትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ፣ የፍትሕ መጓደልን ለማፍረስና የአምላክን ፍትሕ ለመስበክ በሥቃይ ላይ የሚገኙትን የሰው ልጆች ልመና ለመቀበል እንፈልጋለን። አልፎ አልፎ የሚደረጉ የበጎ አድራጎት ተግባራት በቂ አይደሉም። ዘላቂ ለውጥ እንዲመጣ የባህልና መዋቅራዊ ለውጦች አስፈላጊ ናቸው።
II. የባህል ለውጥ፡ ሁላችንም ባለዕዳዎች ነን
5. የኢዮቤልዩ አከባበር የምድራችን ሐብት ለጥቂቶች ብቻ የታለመ ሳይሆን ለሁሉም ሰው መሆኑን በማሳሰብ አሁን ያለውን ኢፍትሃዊነት እና አለኩልነት ወይም መበላለጥ ለመጋፈጥ በርካታ ለውጦችን እንድናደርግ ያነሳሳናል። የቂሳርያው ቅዱስ ባስልዮስ፡- “ንገረኝ፣ የአንተ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው? የሕይወትህ አካል እንዲሆኑ ከየት አገኘኋቸው? … ከእናትህ ማኅፀን ራቁትህን አልወጣህምን? ራቁትህን ወደ መሬት አትመለስምን? ንብረትህ ከየት መጣ? በተፈጥሮ ወደ አንተ በዕድል ይመጣል ብትል ፈጣሪን ባለማወቅ እና ሰጪውን ባለማመስገን እግዚአብሔርን ትክዳለህ" ይል ነበር። ያለ ምስጋና፣ የእግዚአብሔርን ስጦታዎች ለይተን ማወቅ አንችልም። ሆኖም ጌታ ማለቂያ በሌለው ምህረቱ ኃጢአተኛ የሰው ልጅን አይጥልም፣ ይልቁንም የሕይወት ስጦታውን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሁሉም በተሰጠ የማዳን ይቅርታ ያረጋግጣል። ለዚያም ነው፣ “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ሲያስተምረን፣ “በደላችንን ይቅር በለን” (ማቴ 6፡12) ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን።
6. ከአብ ጋር ያለንን ዝምድና ካጣን በኋላ፣ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ትክክል በሚሆንበት በብዝበዛ እና በጭቆና አመክንዮ ሊመራ ይችላል የሚለውን ቅዠት መንከባከብ እንጀምራለን። በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ሊቃውንት ከድሆች ስቃይ እንደተጠቀሙ ሁሉ፣ ዛሬም እርስ በርስ በተገናኘው ዓለም አቀፋዊ መንደራችን ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት በአብሮነት እና በመደጋገፍ መንፈስ ካልተነሳሳ በስተቀር በሙስና እየተባባሰ ለኢፍትሃዊነት መፈጠር መንስኤ ይሆናል፣ ይህም ድሆች አገሮች ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል። ባለዕዳዎችን የሚበዘብዝ አስተሳሰብ አሁን ላለው “የዕዳ ቀውስ” አጭር መግለጫ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፣ ይህም በብዙ አገሮች ላይ በተለይም በዓለም አቀፉ ደቡብ ክፍል ውስጥ።
7. አንዳንድ የበለፀጉ ሀገራት መንግስታት እና የግል የፋይናንስ ተቋማት የድሃ ሀገራትን የሰው እና የተፈጥሮ ሃብት ያለ አግባብ በመበዝበዝ የራሳቸውን የገበያ ፍላጎት ለማርካት ሲሉ የውጭ ብድር የቁጥጥር ዘዴ እየሆነ መምጣቱን ደጋግሜ ገልጫለሁ። በተጨማሪም፣ ቀድሞውንም የዓለም አቀፍ ዕዳ የተሸከሙ የተለያዩ ህዝቦች፣ በበለጸጉት አገሮች የሚደርስባቸውን “የሥነ-ምህዳር ዕዳ” ሸክም ለመሸከም ተገደዋል። የውጭ ብድር እና የስነ-ምህዳር ዕዳ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፣ እነሱም የብዝበዛ አስተሳሰብ ወደ ዕዳ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። በዚህ የኢዮቤልዩ አመት መንፈስ፣ በዚህ አለም በሰሜን እና በደቡብ መካከል ያለውን የስነ-ምህዳር ዕዳ በመገንዘብ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የውጭ ዕዳን ይቅር ለማለት እንዲሰራ አሳስባለሁ። ይህ ለአብሮነት የቀረበ የይግባኝ ጥሪ ነው፣ ከሁሉም በላይ ግን ለፍትህ አስፈላጊ ነው።
8. ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስፈልገው የባህልና መዋቅራዊ ለውጥ የሚመጣው ሁላችንም የአንድ አባት ወንድ እና ሴት ልጆች መሆናችንን፣ ሁላችንም የእሱ ዕዳ እንዳለብን፣ ነገር ግን እርስ በርሳችን አንዱ ለአንዱ እንደምያስፈልግ ስንገነዘብ፣ በጋራ መንፈስ እና በተለያየ ኃላፊነት ሁላችንም የድርሻችንን ስንወጣ ነው። “እርስ በርሳችን የሚያስፈልገንን አንድ ጊዜ እንደገና ማግኘት” እና አንዳችን ለሌላው ባለውለታ መሆን እንችላለን።
III. የተስፋ ጉዞ፡- ሶስት ሐሳቦች
9. እነዚህን በጣም የሚፈለጉ ለውጦችን ልብ ብለን ከወሰድን፣ የኢዮቤልዩ የጸጋ ዓመት እያንዳንዳችንን ወደ አዲስ የተስፋ ጉዞ እንድናቀና ሊያደርገን ይችላል፥ ይህም ከማይገደበው ከእግዚአብሔር ምሕረት ልምድ የተወለድን እንድንሆን ያደረገናል።
እግዚአብሔር ለማንም ምንም ዕዳ የለበትም፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ጸጋውን እና ምሕረቱን ለሁሉም ይሰጣል። የነነዌው ይስሐቅ፣ የሰባተኛው መቶ ዘመን የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን አባት፣ በአንድ ጸሎቱ ላይ እንዳስቀመጠው:- “ጌታ ሆይ፣ ፍቅርህ ከበደሌ ይበልጣል። ከኃጢአቴ ብዛት አንጻር የባሕር ማዕበል ምንም አይደለም፥ ነገር ግን በሚዛን ላይ ተቀምጦ በፍቅርህ የተመዘኑ፥ እንደ ትቢያ ቅንጣት በነዋል" ይል ነበር። እግዚአብሔር የምንሠራውን ክፉ ነገር አይመዝንም፤ ይልቁንም እርሱ “በምሕረቱ እጅግ ባለ ጠጋ ነው፤ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ” (ኤፌ 2፡4)። ነገር ግን የድሆችን ልመናና የምድርን ጩኸት ይሰማል። ልባችንን በተስፋና በሰላም እንዲሞላ፣ ኃጢአታችንን ያለማቋረጥ ይቅር የሚለን፣ ዕዳችንንም ይቅር የሚለን ምሕረትን ልናስብ፣ በተለይም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ለአፍታ ቆም ብለን ብናስብ መልካም ነው።
10. “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት እንድንጸልይ ሲያስተምረን ኢየሱስ አብ በደላችንን ይቅር እንዲሊልን በመጠየቅ ይጀምራል፣ ነገር ግን ወዲያውኑ ወደ ተፈታታኝ ቃላቶች ያልፋል፡- “የበደሉንን ይቅር እንደምንል” (ማቴ 6፡12) ወደ ተሰኘው ሐርግ ማለት ነው። የሌሎችን በደላቸውን ይቅር ለማለት እና ለእነሱ ተስፋ ለመስጠት፣ ህይወታችን በዚያው ተስፋ እንዲሞላ፣ በእግዚአብሔር የምሕረት ልምድ ፍሬ እንዲሞላ ያስፈልገናል። በልግስና ውስጥ ተስፋ ሞልቷል፣ ከስሌት የጸዳ ነው፥ ምንም የተሰወረ ነገርን አያደርግም፥ ለጥቅም አይጨነቅም፥ ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ ነው የሚፈልገው፥ የወደቁትን ለማንሣት፥ የተሰበረውን ልብ ለመፈወስ፥ ከባርነትም ሁሉ ነጻ ያወጣናል።
11.ስለዚህ በዚህ የጸጋ አመት መጀመሪያ ላይ የመላው ህዝቦች ህይወት ወደነበረበት እንዲመለስ እና በተስፋ ጉዞ ላይ በአዲስ መልክ እንዲረማመዱ የሚያስችሏቸውን ሶስት ሀሳቦችን ማቅረብ እፈልጋለሁ። በዚህ መንገድ የዕዳ ቀውስን ማሸነፍ ይቻላል እና ሁላችንም ዕዳችን ይቅር የተባለልን ባለዕዳዎች መሆናችንን በድጋሚ እንገነዘባለን።
በመጀመሪያ፣ በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ የ2000 ዓ.ም ታላቁ ኢዮቤልዩ በዓል ላይ “የብዙ አገሮችን የወደፊት ዕጣ በእጅጉ የሚያሰጋውን ዓለም አቀፋዊ ዕዳ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ካልሆነም እንዲሻር” ያቀረቡትን ጥሪ በድጋሚ ለማንሳት እፈልጋለሁ። ለሥነ-ምህዳር ዕዳቸው እውቅና ለመስጠት፣ የበለጸጉ አገሮች የተበደሩትን መጠን ለመክፈል ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የሌላቸውን የእነዚያን አገሮች ዕዳ ይቅር ለማለት የተቻለውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ ሊደረግላቸው ይገባል። በተፈጥሮ፣ ይህ የተናጠል የበጎ አድራጎት ተግባር ብቻ እንዳይሆን፣ በቀላሉ የፋይናንስ እና የብድር አዙሪት እንደገና እንዳይጀምር፣ አዲስ የፋይናንስ ማዕቀፍ ተነድፎ በህዝቦች መካከል አብሮነትና ስምምነት ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት መፈጠር አለበት።
እንዲሁም እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሕይወት እንዲንከባከብ እና ሁሉም ለራሳቸው እና ለእነርሱ ብልጽግና እና ደስታን ለማግኘት ተስፋ እንዲያደርጉ ለሰው ልጅ ሕይወት ክብር ከጽንሰ-ሀሳብ እስከ ተፈጥሮአዊ ሞት ለማክበር ቁርጠኝነት እጠይቃለሁ። ለወደፊት ያለ ተስፋ፣ ለወጣቶች አዲስ ህይወት ወደ አለም ለማምጣት በጉጉት መጠባበቅ ከባድ ይሆናል። እዚህ አንድ ጊዜ የህይወት ባህልን ለማዳበር የሚረዳ ተጨባጭ ምልክት ሀሳብ ማቅረብ እፈልጋለሁ፣ ይህም በሁሉም ሀገራት ውስጥ የሞት ቅጣትን ማስወገድ ነው። ይህ ቅጣት የህይወትን የማይገረሰስ መብት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ የይቅርታ እና የመልሶ ማቋቋም ተስፋን ያስወግዳል።
በተጨማሪም፣ የቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እና የቤኔዲክት 16ኛን ፈለግ በመከተል፣ ለቀጣዩ ትውልዶች ስል ሌላ አቤቱታ ለማቅረብ አላቅማም። በዚህ በጦርነቶች በሚታወቅበት ጊዜ፣ ለጦር መሣሪያ ከተመደበው ገንዘብ ቢያንስ የተወሰነውን በመቶኛ በመጠቀም ረሃብን ለማጥፋት እና በድሃ አገሮች ውስጥ ዘላቂ ልማትን ለማስፋፋት እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት የታለሙ የትምህርት እንቅስቃሴዎችን ለማመቻቸት ዓለም አቀፍ ፈንድ ለማቋቋም እንጠቀም። ወጣቶች የወደፊት ሕይወታቸውን እንደ ተስፋ ቢስ አድርገው እንዲቆጥሩ ወይም የሚወዷቸውን ሰዎች ደም ለመበቀል ባለው ጥማት የበላይ እንዲሆኑ የሚያበረታታውን ማንኛውንም ሰበብ ለማስወገድ መሥራት አለብን። መጪው ጊዜ ካለፉት ውድቀቶች አልፈን አዲስ የሰላም መንገዶችን ለመዘርጋት የሚያስችል ስጦታ ነው።
IV. የሰላም ግብ
12. እነዚህን ሃሳቦች አንስተው ወደ ተስፋው ጉዞ የተጓዙት በጣም የሚፈለገውን የሰላም ግብ ጎህ ሲቀድ ያያሉ። መዝሙራዊው “ፍቅርና ታማኝነት ይገናኛሉ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ” (መዝ 85፡10)። የብድር መሳሪያውን ራሴን ነጥቄ ለወንድሞቼ ወይም ለእህቶቼ የተስፋ መንገድን ስመልስ፣ በዚህ ምድር ላይ የእግዚአብሔር ፍትህ እንዲታደስ አስተዋፅዖ አደርጋለሁ፣ እናም ከዚያ ሰው ጋር ወደ ሰላም ግብ እሄዳለሁ። በቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ እንደተመለከተው፣ እውነተኛ ሰላም ሊወለድ የሚችለው ከጭንቀትና ከጦርነት ፍርሃት ብቻ ሳይሆን “ትጥቅ ከፈታው” ልብ ብቻ ነው።
13. እ.አ.አ 2025 ዓ.ም ሰላም የሚያብብበት ዓመት ይሁን! በስምምነት ዝርዝሮች እና በሰዎች ስምምነት ላይ ከመንቀጥቀጥ የዘለለ እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም። ለታጠቁ ልቦች ከእግዚአብሔር የተሰጠን እውነተኛውን ሰላም እንፈልግ፡ ልቦች የእኔና የእናንተ የሆነውን ለማስላት ያላሰቡ ልቦች። ራስ ወዳድነትን ወደ ሌሎች ለመድረስ ዝግጁነት የሚቀይሩ ልቦች፣ ለእግዚአብሔር ባለውለታ እንደሆኑ አድርገው የሚቆጥሩ እና ሌሎችን የሚጨቁኑ ዕዳዎችን ይቅር ለማለት የተዘጋጁ ልቦች፥ እያንዳንዱ ግለሰብ ለተሻለ ዓለም ግንባታ ግብአት ሊሆን ይችላል በሚል የወደፊት ጭንቀትን የሚተኩ ልቦች።
14. ልብን ትጥቅ ማስፈታት ለታላቅም ለታናሽም፣ ለሀብታምም ለድሆችም ለሁሉም ሰው የሚሆን ሥራ ነው። አንዳንድ ጊዜ በጣም ቀላል የሆነ ነገር ለምሳሌ "ፈገግታ፣ ትንሽ የጓደኝነት ስሜት፣ ደግ መልክ፣ ዝግጁ ጆሮ፣ ጥሩ ተግባር" ይሠራል። እንደዚህ ባሉ ምልክቶች፣ ወደ ሰላም ግብ እንሄዳለን። ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በምናደርገው ጉዞ መጀመሪያ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እንደተለወጥን ካወቅን ቶሎ እንደርሳለን። ሰላም የሚመጣው ከጦርነቶች ማብቂያ ጋር ብቻ ሳይሆን አዲስ ዓለም ሲገባ ነው፣ ይህም ዓለም እኛ ከምንጊዜውም በላይ የምንቀራረብበት እና የበለጠ ወንድማማች መሆናችንን የምንገነዘብበት ዓለም ነው።
15. አቤቱ ሰላምህን ስጠን! ለአዲሱ ዓመት ለመንግሥታት እና ለአገር መሪዎች፣ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች፣ ለተለያዩ ሃይማኖቶች መሪዎች እና መልካም ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ሁሉ መልካም ምኞቴን እያቀረብኩ ይህ ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎቴ ነው።
አቤቱ ጌታ ሆይ የበደሉንን ይቅር እንደምንል
በደላችንን ይቅር በለን
በዚህ የይቅርታ ሂደት ውስጥ ሰላምህን ስጠን።
የወንድሞቻቸውንና የእህቶቻቸውን ዕዳ ይቅር ለማለት በተስፋ ለሚመርጡ፣
ዕዳቸውን መናዘዝ ለማይፈሩ፣
ለድሆችም ጩኸት ጆሮአቸውን ለማይዘጉ።
ልባቸውን ትጥቅ ማስፈታት ለሚፈቅዱ ሁሉ
አንተ ብቻ የምትሰጠው ሰላም ስጠን
ከቫቲካን፣ ታህሳስ 8፣ 2024
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን