ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. የምሕረት ኢዮቤልዩ ዓመትን ሲያስጀምሩ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. የምሕረት ኢዮቤልዩ ዓመትን ሲያስጀምሩ  

የኢዮቤልዩ በዓላት በግል ሕይወት ላይ በማሰላሰል ውሳኔ የሚደረግባቸው ጊዜያት እንደሆኑ ተነገረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ተስፋ” በሚለው መሪ ቃል ላይ በማሰላሰል መጭውን የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት (2025) ዓ. ም. በማስመልከት “@Pontifex” በሚለው መለያ “X” ገጻቸው በኩል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዋዜማ ማለትም ታኅሳስ 15/2017 ዓ. ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር በመክፈት የኢዮቤልዩ በዓል ቅዱስ ዓመትን በይፋ እንደሚያስጀምሩ ታውቋል። ቀጥለውም ታኅሳስ 17/2017 ዓ. ም. ሮም ውስጥ የሚገኘውን የሬቢቢያ ማረሚያ ቤትን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።

ከዚያም በሮም ውስጥ የሚገኙ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎችን፥ የቅዱስ ዮሐንስ ዘ ላቴራን ባዚሊካን፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ጳጳሳዊ ባዚሊካን እና የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካን ጎብኝተው ቅዱሳት በሮቻቸውንም እንደሚከፍቷቸው ይጠበቃል። በእነዚህ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢዮቤልዩ በዓላት እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ሕይወታችንን የምንመረምርባቸው፣ መንፈስ ቅዱስ የሚነግረንን ለማዳመጥ እና ለማሰላሰል ዕድሎችን የሚሰጡ የተከበሩ ጊዜያት ናቸው” (ራዕ 2.7) ፣ #ኢዮቤልዩ2025። “ተስፋም ቅር አያሰኘንም” (ሮሜ 5:5) በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ላይ እንደተገለጸው፥ በጦርነት፣ በመከፋፈል፣ በድህነት፣ በአየር ንብረት ቀውሶች፣ ጭንቀት እና መከራ ብቻ ያለበት በሚመስለው ዓለም ውስጥ ተስፋ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በዘጠኝ የተለያዩ ቋንቋዎች በጻፉት መልዕክት፥ መላውን ዓለም እና የሁሉንም ሰው ሕይወት ሊወክል በሚችል መልኩ ተናግረዋል። የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት መንፈስ ቅዱስ የሚናገረውን ለማዳመጥ እና ለማሰላሰል ዕድልን የሚሰጥ ውድ ጊዜ መሆኑን ያሰመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ቀደም ሲል በቅርብ ወራት ውስጥ እንደገለጹትም፥ “የኢዮቤልዩ በዓል መንፈሳዊነት ይበልጥ የሚያድግበት፣ ዳግም የሚወለዱበት፥ ይቅር የሚባባሉበት እና ማኅበራዊ ነጻነት የሚገኝበት ጊዜ ሊሆን ይችላል” ማለታቸው ይታወሳል።

በኢዮቤልዩ ዓመት የሚከበሩ በርካታ በዓላት አሉ
ከአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ በዓል ዋዜማ እና የቅዱሱ በር መክፈቻ መርሃ ግብር ከሚፈጸምበት ከታህሳስ 15/2017 ዓ. ም. ጀምሮ የኢዮቤልዩ ዓመት እስከሚገባደድበት ታኅሳስ 28/2017 ዓ. ም. ድረስ ሊከበሩ የታቀዱ በዓላት እንዳሉ ታውቋል። በኢዮቤልዩ ዓመት ውስጥ በሚከበሩ በዓላት ላይ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚሳተፉ ሲነገር፥ ከመገናኛው ዓለም እስከ አርቲስቶች፣ ከጦር ሠራዊት አባላት እስከ በጎ ፈቃደኞች፣ ከሕሙማን እና ጤና ባለሞያዎች እስከ ገዳማውያን፣ ገዳማውያት እና ዲያቆናት፣ ከሠራተኛ እስከ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ከአገር መሪዎች እስከ ወጣቶች ድረስ እንደሚሳተፉበት ይጠበቃል። በተለይም የካርሎ አኩቲስ የቅድስና አዋጅ በተመለከተ ከሚያዝያ 17-19/2017 ዓ. ም. ድረስ ሊከበር በታቀደው በዓል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣት እና ጎልማሳ ምዕመናን እንዲሁም እንግዶች ወደ ሮም እንደሚመጡ ይጠበቃል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በር የመክፈት ሥነ-ሥርዓት
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓውያኑን የብርሃነ ልደቱ በዓል ምክንያት በማድረግ በዋዜማው ዕለት ማለትም ታኅሳስ 15/2017 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እንደሚፈጸም እና ቀጥሎም የባዚሊካው ቅዱስ በር መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት እንደሚካሄድ ታውቋል። ሥነ-ሥርዓቱን ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ምእመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተገኝተው በሰፋፊ ስክሪኖች በኩል ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ የሚያስጀምሩት የኢዮቤልዩ ዓመት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የኢዮቤልዩ ዓመትን በይፋ ካስጀመሩ ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ እና ልዩ የምሕረት ኢዮቤልዩ በዓል ከተከበር ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ እንደሆነ ታውቋል።

በዓሉን ለማክበር የሁሉም አህጉራት ምዕመናን ወደ ሮም ይመጣሉ
በዚህ ቅዱስ የኢዮቤልዩ ዓመት ከዓለም ዙሪያ ምዕመናን ወደ ሮም እንደሚመጡ ሲጠበቅ በመጀመሪያ ደረጃ ከተለያዩ አገራት ማለት ከኦስትሪያ ፣ ከደቡብ ኮሪያ ፣ ከግብፅ ፣ ከፊሊፒንስ ፣ ከህንድ ፣ ከሜክሲኮ ፣ ከናይጄሪያ ፣ ከሳሞአ ፣ ከስሎቫኪያ እና ከቬንዙዌላ የተውጣጡ አሥር ሕፃናት ለር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አበባን የሚያቀርቡበት መርሃ ግብር መካከቱ ታውቋል። ከአምስት አህጉራት የተወጣጡ ሃምሳ አራት ምእመናን የኢዮቤልዩ ዓመትን ምሕረት ለመጠየቅ እና እምነታቸውን ለመመስከር በቅዱስነታቸው የተከፈተውን ቅዱስ በር በመሻገር የመጀመሪያዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ምዕመናኑ ከሚመጡባቸው አገራት መካከል ቻይና፣ ኮንጎ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ኢራን፣ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፣ ሳሞአ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ቬትናም እንደሚገኙበት ታውቋል።

የኢዮቤልዩ በዓል ለረቢቢያ ታራሚዎች የተስፋ ምልክት ነው!
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ተስፋም ቅር አያሰኘንም” (ሮሜ 5:5) በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ እንደጻፉት፥ የኢዮቤልዩ ዓመት ምልክት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በኅብረተሰቡ ውስጥ ተጋላጭ ለሆኑት ሰዎች እንክብካቤ የሚደረግበት እና በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙትም ምሕረትን የሚያገኙበት ቅዱስ ዓመት ይሆናል በማለት ገልጸው እንደ ነበር ይታወሳል።

በመቀጠልም የኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት አስተባባሪ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ቅዱስነታቸው እንዲጎበኙት የተመረጠው ማረሚያ ቤት ሮም ውስጥ የሚገኝ የረቢቢያ ማረሚያ ቤት መሆኑን ገልጸው፥ ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት በ2007 ዓ. ም. ጎብኝተውት እንደ ነበር አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ቅዱስነታቸው ለታራሚዎቹ በጻፉት መልዕክት ተጨባጭ የመቀራረብ ምልክትን ማቅረብ መፈለጋቸውን ገልጸው በተጨማሪም የወደፊት ሕይወትን በተስፋ እና በአዲስ የሕይወት ቁርጠኝነት እንድንመለከተው የሚጋብዝ ምልክት ሊሆን እንደሚችል መናገራቸውን አስታውሰዋል።

ሮም ውስጥ በሚገኙ ባዚሊካዎች ውስጥ የሚፈጸም ሥነ-ሥርዓት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ፍራንችስኮስ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር እና የረቢቢያ ማረሚያ ቤት በር ከከፈቱ በኋላ ሮም ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሦስቱ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች እነርሱም የቅዱስ ዮሐንስ ዘ ላቴራን ባዚሊካ በር ታኅሳስ 20 ቀን፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ በር ታኅሳስ 23 ቀን፣ እና የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ በር ታኅሳስ 27/2017 ዓ. ም. እንደሚከፍቱት ይጠበቃል።

ከዓለም ዙሪያ ለሚመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሁሉም የባዚሊካዎቹ በሮች ዓመቱን በሙሉ ተከፍተው እንደሚቆዩ ታውቋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ካቴድራሎች እስከ እሑድ ታኅሳስ 19/2018 ዓ. ም. ድረስ እንደ መደበኛው ጊዜ ተዘግተው ቢቆዩም የኢዮቤልዩ ዓመት የመክፈቻ በዓል ምክንያት በማድረግ ጳጳሳት በሁሉም ካቴድራሎች እና አጋር ካቴድራሎች ውስጥ እሑድ ታኅሳስ 20/2017 ዓ. ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015-16 የምሕረት ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ የካቴድራሎች ዋና መግቢያ በሮች ወይም የልዩ አምልኮ ቦታዎች ቅዱስ በሮች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሮም መጓዝ ለማይችሉት ምዕመናን ክፍት ሆነው እንዲቆዩ በማለት የዓለም ጳጳሳትን ማሳሰባቸው ይታወሳል።

 

24 December 2024, 15:39