ፈልግ

በአውሎ ነፋስ አደጋ የተጎዳች የማዮት ደሴት በአውሎ ነፋስ አደጋ የተጎዳች የማዮት ደሴት  (REUTERS)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በአውሎ ነፋስ አደጋ የተጎዱትን የማዮት ደሴት ሰዎች በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ታኅሳስ 9/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው፥ በአውሎ ነፋስ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን የማዮት ደሴት ነዋሪዎችን በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ከፖላንድ የመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን በአውሮፓውያኑ የብርሃነ ልደቱ ሰሞን የዩክሬይን ስደተኞችን እንዲያስታውሷቸው አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው ላይ ለተገኙት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታ አቅርበው፥ በአውሎ ነፋስ አደጋ የተጎዱ የማዮት ነዋሪዎችን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ግዛት በሆነች ማዮቴት ደሴት ውስጥ ታኅሳስ 5/2017 ዓ. ም. የተነሳው አውሎ ነፋስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ እና በንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት ሳይደርስ እንዳልቀረ ተነግሯል። በፈረንሳይ የሚገኝ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት “ካሪታስ” ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ተወካይ አቶ ማርክ ቡልቴው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ በደሴቲቱ ያለውን ሁኔታ እጅግ አስደንጋጭ ነው” ሲል ገልጾታል።

ጠቅላላ ሕዝቧ ወደ 300,000 ያህል እንደሚሆን የሚነገርላት ማዮቴ ደሴት በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ እጅግ ድሃ እንደሆነች እና ከነዋሪዎቿ መካከል አንድ ሦስተኛው በተጎሳቆሉ መንደሮች ውስጥ እንደሚኖር፥ አሁን በደረሰው አደጋ አብዛኛዎቹ መንደሮች መውደማቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሳምንታዊው የረቡዕ አስተምህሮአቸው ላይ ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ዕረፍትን፣ ችግር ውስጥ ለወደቁት አስፈላጊው ዕርዳታ እንዲደርሳቸው እና በአደጋው ለተጎዱት ቤተሰቦች እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጣቸው ጸሎት አድርሰዋል።

ለፍልስጤም፣ ለእስራኤል፣ ለዩክሬን እና ለምያንማር ሕዝብ ሰላም ጸልየዋል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየሳምንቱ በሚያቀርቧቸው የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው እንደሚያደርጉት ሁሉ፥ ከጣሊያን ልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶች ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ባቀረቡት ሰላምታም ጦርነት ባሉባቸው ቀጣናዎች ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

“ስለ ሰላም እንጸልይ!” በማለት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጦርነት የሚሰቃዩ የፍልስጤም፣ የእስራኤል፣ የዩክሬይን እና የምያንማር ሕዝቦችን ማስታወስ እንደሚገባ አሳስበው፥ “የሰላሙ ንጉሥ በዓለማችን ውስጥ የሰላም ጸጋን እንዲሰጠን እንለምነው” ካሉ በኋላ ጦርነት ሁሌም ሽንፈት ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

ከፖላንድ ለመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያን በድጋሚ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ ፖላንድ ውስጥ በስደት የሚኖሩ ዩክሬይናውያንን መንከባከብ እንደሚገባ ለነጋዲያኑ አደራ ብለዋል። “በብርሃነ ልደቱ ዋዜማ ላይ የምትቆርሱት የገና ዳቦ የበጎነት፣ የሰላም እና የይቅርታ ምልክት በመሆኑ በመንገድ ዳር ለምታገኟቸው ችግረኞች ልባችሁ ክፍት ይሁን!” ካሉ በኋላ፥ ከሁሉም በላይ ድሆችን፣ ብቸኝነት ያጠቃቸውን፣ የጎርፍ አደጋ ሰለባዎችን እና እህት እና ወንድም የሆነውን የዩክሬይን ሕዝብን ማስታወስ ቀጥሉ” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

19 December 2024, 13:37