ፈልግ

በቅድስት ሉሲ በዓል ዕለት የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት  በቅድስት ሉሲ በዓል ዕለት የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የቅድስት ሉሲ በጎነት ፍትሃዊ ማኅበረሰብን መገንባት እንደሚያስተምር ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ጣሊያን ሲሲሊ ውስጥ ለሚገኝ የሲራኩሳ ሀገረ ስብከት መልዕክት ልከዋል። ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ለሀገረ ስብከቱ የላኩት በደቡብ ጣሊያን ሲሲሊ የሚገኘው የሲራኩስ ሀገረ ስብከት የከተማው ባልደረባ የሆነች የቅድስት ሉሲ በዓል የሚከበርበት ልዩ ዓመት ባወጀበት ዓርብ ታኅሳስ 4/2017 ዓ. ም. እንደሆነ ታውቋል። በመልዕክታቸውም፥ “የቅድስት ሉሲ ሰማዕትነት የበለጠ ፍትሃዊ ማኅበረሰብን ለመገንባት አስፈላጊ የሆኑ ርህራሄ እና ክርስቲያናዊ በጎነቶችን ያስተምረናል” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት ሉሲ ሲሲሊ ውስጥ በሰራኩሳ ሀገረ ስብከት የተወለደች ስትሆን፥ በዲዮቅልጥያኖስ ዘመን ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ304 ክርስቲያኖችን በደረሰ ስደት ዓይኖቿ ተነቅለው በሰማዕትነት ያረፈች ሲሆን፥ ከብዙ መቶ ዘመናት ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ተወዳጅነት እንዳላት ታውቋል።

የሲራኩሳ ምዕመናን በየዓመቱ በታኅሣሥ ወር የባልደረባቸውን ዓመታዊ በዓል በደማቅ ሁኔታ እንደሚያከብሩ ይታወቃል። ሉሲ የሚለው ስሟ በላቲን “ብርሃን” ወይም “ሉክስ” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፥ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ እንደ የዕይታ ጠባቂ በመሆን እንደሚከበር እና ታኅሳስ 4 ቀን ሰማዕትነት የተቀበለችበት እንደሆነ ይታወቃል።

በየዓመቱ ታኅሳስ 4 ቀን የቅዱሷ ሐውልት እና ቅዱስ አጽም መካነ መቃብሯ ወደሚገኝበት ቅድስት ሉሲ ካቴድራል በኡደት እንደሚወሰድ ይታወቃል። ዘንድሮም የቅድስት ሉሲ ዓመት መባቻን ምክንያት በማድረግ በዓሉ የሚከበረው ላለፉት ስምንት መቶ ዓመታት የቅድስት ሉሲ ቅዱስ አጽም ተጠብቆ ወደቆየበት ወደ ቬኒስ የቅድስት ሉቺያ ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ጉዞ እንደሚደረግ ታውቋል። በዕለቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሲራኩሳ ሰማዕት ውርስ ለዛሬው ዓለማችን በሚሰጠው ምክር ላይ በማሰላሰል ለሲራኩሳ-ሎማንቶ ሀገረ ስብከት ምዕመናን ማኅበረሰብ መልዕክት አስተላልፈዋል።

እግዚአብሔር ብርሃንን ያወጣል
“ለቅድስት ሉሲ ያላችሁት ፍቅር ወደ አንድ ጥንታዊ የክርስትና እምነት መልሷችኋል” ያሉት ርዕሠ ጳጳሳር ፍራንችስኮስ፥ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ የለም” በሚለው የድነት ቃላት ላይ የሲራኩሳ ምዕመናን እንዲያሰላስሉ አሳስበዋል። ይህ የድነት ቃልም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጭው 2025 በሚከበረው የኢዮቤልዩ ዓመት እንደ ተስፋ ነጋዲያን ሆነው ለመጓዝ ሲዘጋጁ ከቤተሰባቸው፣ ከቤተ ክርስቲያን እና ከማኅበረሰባቸው ጋር ያላቸውን ትስስር ለማደስ የሚያገለግል መሆኑን አስረድተዋል።

የቅዱስነታቸው መልዕክት በማከልም የቅድስት ሉሲ ቅዱስ አጽም ከቬኒስ ወደ ሲራኩሳ በሚያደርገው መንፈሳዊ ንግደት የእግዚአብሔርን ምስጢር ማየት እንደሚቻል ለምእመናኑ ተናግረው፥ መለያየትን አስወግደው ደግነትን የሚያስፋፉ የመጀመሪያ ምሳሌዎች በመሆን ይህን መለኮታዊ ምሳሌ እንዲከተሉ አሳስበዋል። “ቅድስት ሉሲ ወደ እናንተ ዘንድ ስትመጣ እናንተም ደግሞ በተራችሁ የመጀመሪያ እርምጃን በማድረግ ወደ እርሱ የምትቀርቡ የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ” በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ በጊዜያዊነት ወደ ሲራኩሳ ሀገረ ስብከት የመጣው የቅድስት ሉሲ ንዋያተ ቅድሳት በቬኒስ እና ሲራኩስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው የኅብረት መንፈስ ውስጥ ስጦታን የሚለዋወጡበት ብርሃን እንዳለ በማስረዳት፥ ይህም ዛሬ በዓለማችን ወንድማማችነትን ለማፍረስ እና ፍጥረታትን ለማውደም የተስፋፋ ሐሰተኛነት የሚያስወግድ መሆኑን ያሳያል” ብለዋል። 

"ቅድስት ሉሲ ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ምስክር ነች" 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን በመቀጠልም የቅድስት ሉሲ ምስክርነት ሴቶች ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረከቱትን ልዩ አስተዋፅዖ የሚያሳይ ሲሆን፥ ይህም ከክርስትና ጅማሬ ጀምሮ በዘመናት ሁሉ ሴቶች በአስተዋይነታቸው፣ በፍቅራቸው እና ወንጌልን በማስፋፋት የማይተካ ሚና ተጫውተው እንደ ነበር ያሳያል” ሲሉ ተናግረዋል።

“የሴቶች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እና ድምጽ በባሕሎች እና በኅብረተሰብ ውስጥ እርሾ እና ብርሃን እንዲሆን እንፈልጋለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ይህም በሜዲትራኒያን ባሕር መሃል፣ የስልጣኔ እና የሰብዓዊነት መገኛ መሆናቸው በይበልጥ ወሳኝ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ በስደት ሰቆቃዎች ጎልቶ የሚታየው የግፍ እና የሚዛን መዛባት ማዕከል ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል።

ክርስቲያናዊ የፖለቲካ ርህራሄ እና የገርነት ባህሪያት
“የቅድስት ሉሲ ሰማዕትነት እንድናለቅስ፣ እንድንራራ እና ርኅራኄን እንድንቀበል ያስተምረናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ክርስቲያናዊ “ነገር ግን ጥልቅ ፖለቲካዊ” በጎ ምግባር ለበለጠ ፍትሐዊ ማህበረሰቦች ግንባታ አስፈላጊ እንደሆኑ ተናግረዋል።

“እንደ ስራኩሳ ሀገረ ስብከት ምዕመናን በቅድስት ሉሲ ዙሪያ እጅግ ብዙ ሕዝብ በአንድነት መሰብሰብ ማለት ሕይወት ሲገለጥ ማየት እና ብርሃንን መምረጥ፣ ከሌሎች ጋር በምናደርገው ግንኙነት ግልጽ እና ቅን መሆን ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ልብን ማዳመጥ መማር
በዚህ ረገድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እኛ ራሳችን በተለይም ወጣቱን ትውልድ ልብን ማዳመጥ፣ ምስክርነቶችን መገንዘብ፣ ወሳኝ አስተሳሰብን ማዳበር እና ለሕሊና መታዘዝን በመማር ቅዱሳንን በመምሰል፣ ውስብስብ ነገሮችን እንድንጋፈጥ የሚያነሳሱ ትምህርቶችን ማስተማር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የሚሰቃዩትን ድሆች፣ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ማስታወስ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ የሲራኩሳ ማኅበረሰብ የሚሰቃዩትን ማለትም ስደተኞችን፣ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ድሆችን በበዓላቸው ውስጥ እንዲያካትቱ በማሳሰብ ለስራኩሳ ሕዝብ የቅድስት ሉሲን እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት ተማጽነዋል።

 

14 December 2024, 16:35