ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የ “ሰብዓዊ ኢኮኖሚ ፎረም” አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የ “ሰብዓዊ ኢኮኖሚ ፎረም” አባላትን በቫቲካን ተቀብለዋል  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ዘላቂ ልማትን ለማምጣት ሰብዓዊ ክብርን ማስቀደም እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ከታኅሳስ 1-2/2017 ዓ. ም. በሮም የተሰበሰቡ የ “ሰብዓዊ ኢኮኖሚ ፎረም” አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሰብዓዊ ክብርን፣ ዓለም አቀፋዊ ትብብርን እና ሁሉ አቀፍ የጋራ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ቀጣይነት ባለው ልማት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።


የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተካሄደው የ “ሰብዓዊ ኢኮኖሚ ፎረም” አባላት ጋር ታኅሳስ 2/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል። “ስብሰባው አስፈላጊ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን እንደሚመለከት እና በሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወት መሪ ሃሳብ ላይ ያተኮረ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

"ሁሉን አቀፍ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና ለማስተዋወቅ፣ ዘላቂ እና ጠቅላላ የሰው ልጅ ልማትን መፈለግ ወሳኝ ነው" ብለው፥ በዚህም ምክንያት በችግሮቻችን እና ተግባሮቻችን መካከል የሰውን ልጅ ማስቀደም እና ዋና ማዕከል ማድረግ አስፈላጊ ነው” ብለዋል። ድህነትን ለመዋጋት፣ በማኅበረሰቡ የተገለሉ ሰዎች ክብርን ለመመለስ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመንከባከብ ከሚደረገው ጥረት ጋር ለሰብዓዊ ክብርና ሁለንተናዊ ዕድገት ትኩረት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሰብዓዊ ዕድገትን የሚያበረታቱ ፕሮጀክቶች ውጤታማ የሚሆኑት ራስን በራስ መደገፍ በሚያስችሉ እና ዘላቂ በሆኑ የኢኮኖሚ ሥርዓቶች የተደገፉ እንደሆነ ነው” በማለት አስገንዝበዋል።

የ “ሰብዓዊ ኢኮኖሚ ፎረም” በወቅታዊው ጉዳዮች ላይ ትንተናን በመስጠት ዓለም አቀፋዊ ራዕይን መውሰዱ የሚያስመሰግን መሆኑን ከተለያዩ ባሕሎች እና ሃይማኖት ተቋማት ለተወጣጡ የስብሰባው ተናጋሪዎች ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ በቫቲካን የተገኙት የስብሰባው ተሳታፊዎች የሰው ሕይወት ቅድስናን ተቀብለው የተሻለ ዓለምን ለመገንባት ባላቸው ቁርጠኝነት እንዲቀጥሉ አበረታተው፥ አባላቱ በቫቲካን ላደረጉት ጉብኝት በማመስገን፣ ሥራዎቻቸውንም በመባረክ ሸኝተዋቸዋል።


 

12 December 2024, 13:36