ፈልግ

cardinale Peter Kodwo Appiah Turkson cardinale Peter Kodwo Appiah Turkson 

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶችን የመፈወስ አቅም መገደብ እንዲያበቃ አሳሰቡ።

በየዓመቱ በህዳር ወር ውስጥ የሚከበረው የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች አጠቃቀም ሳምንት፣ በየዓመቱ እያደገ የመጣውንና በሰዎች ጤና ላይም ጉዳት እያስከተለ ያለው የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች የመፈወስ ሃይልን ሰውነት እየተቋቋመ መምጣቱ አሳሳቢ ደርጃ ላይ ደርሷል ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶች የማዳን አቅምን መገደብ እንዲቆም አሳስበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ይህን የገለጹት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የአንቲባዮቲክ መድሐኒት አጠቃቀም ሳምንት ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በንግግራቸው፣ ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት የቆመ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ እንደመሆኔ ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ጋር መተባበር ይኖርብኛል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረው የአንቲባዮቲክ መድሐኒት አጠቃቀም ሳምንት በዋናነት የተመለከተው የአንቲባዮቲክ መድሃኒቶች የማዳን አቅምን መገደብ በአስቸኳይ ለማስቆም ጥረት ማድረግን የሚጠይቅና ይህን ለማድረግም ጉዳዩ የሚመለከታቸው በሙሉ በሕብረት እንዲቆሙ የሚያሳስብ እንደሆነ ታውቋል። በየዓመቱ በሕዳር ወር ውስጥ የሚከበረው የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች አጠቃቀም ሳምንት፣ በየዓመቱ እያደገ የመጣውንና በሰዎች ጤና ላይም ጉዳት እያስከተለ ያለው የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች የመፈወስ ሃይልን ሰውነት እየተቋቋመ መምጣቱ አሳሳቢ ደርጃ ላይ ደርሷል ተብሏል። በመሆኑም አሉ ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በመሆኑም በሕብረተሰቡ ወይም በተጠቃሚው መካከል፣ በጤና ባለሞያዎች፣ በመንግሥት በሚመሩ የፖለቲካ ተቋማት መካከል ግንዛቤን በመስጠት የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን የመቋቋም አቅም እንዳይከሰት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአንቲባዮቲክ መድኃኒቶች ላይ የሚድረግ ጥንቃቄ፣

የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች በምርምር ከታውቁበት ጊዜ አንስቶ በሰው ልጅ ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን ስቃዮች በማስወገድ፣ በርካታ ሕይወትንም ከሞት ማትረፉ የሚታወቅ ሲሆን፣ ነገር ግን መጠናቸውንና ዓይነታቸውን በአግባቡ ካለመለየት የተነሳ እንደ ባክቴሪያ ያሉ ረቂቅ ተህዋሲያን መድሐኒቱን መቋቋም በሚችሉበት ጊዜ ሰዎችንና እንስሳትን ለሞት አደጋ እያጋለጡ መሆናቸው ተረጋግጧል ተብሏል። በተጨማሪም ጥራታቸውን ያልጠበቁ የአንቲባዮቲክ መድሐኒቶች ገበያ ላይ መበራከት፣ ይህንን የሚከታተል ክፍል ጥቂት ከመሆኑ የተነሳ፣ በእንስሳት ምግብ፣ በእርሻ ምርቶች፣ በጤና አገልግሎት አቅርቦት፣ በላቦራቶሪ ምርመራዎች፣ በውሃና በአፈርም ብክለት እያስከተለ መሆኑን በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን ገልጸዋል።

አንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን መቋቋም የሚያስከትለው ችግር፣

የአንቲባዮቲክ መድኃኒቶችን የመፈወስ ብቃት የመቋቋም ሃይል እየጨመረ መምጣት በዓለም ሕዝብ ጤና ላይ ችግር እያስከተለ መምጣቱን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ እንደ ባክቴሪያ ያሉ ረቂቅ ተህዋሲያን ለምሳሌ ቫይረሶችና ፈንገስ መድሐኒቱን የመቋቋም ሃይል የሚያገኙ ከሆነ የዘመናዊ መድሐኒቶችን የመፈወስ አቅም አደጋ ላይ በመጣል፣ የሰዎችን ጤና እና የአገሮችን እድገት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን አስረድተዋል። ይህ ከሆነ በተለይም በወላድ እናቶች እንዲሁም አዲስ በሚወለዱ ሕጻናት ጤና፣ አንዳንድ ከባድ ህመም ያለባቸው ታካሚዎች፣ ኬሞቴራፒ ወይም ቀዶ ጥገና ለሚደረግባቸው ሕሙማን፣ የጤና እንክብካቤን የማያገኙ እና በብዙ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ጤና ላይ አደጋን እንደሚያስከትል አስረድተዋል።  

ተነሳሽነቶችን ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፣

ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በንግግራቸው መደምደሚያ፣ አንቲባዮቲክ መድሐኒቶችን በሚጠቀሙ ሕሙማን መካከል አስፈላጊውን የባህሪ ለውጦች ማምጣት፣ የተዛማች በሽታዎች ቁጥጥርን ማሳደግ፣ የአንቲባዮቲክ መድሓኒቶችን በትክክል እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ግንዛቤን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን በተጨማሪም በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሕክምና ትምህርት ቤቶችና እና የጤና እንክብካቤ ተቋማት መኖራቸውን አስታውሰው እነዚህ ተቋማት ከሌሎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመተባበር ለሕክምና ሰጭ ተቋማት የማያቋርጥ ድጋፍን መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 November 2018, 15:33