የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ክፍል ሁለት
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በሚል አርእስት ስለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ለዚህ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሰረት የጣሉ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎችን፣ አንቀጸ እምነቶችን፣ አስተምህሮዎችን፣ እንዲሁም ይህንን የቤተ ክርስቲያኒቷን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የጻፏዋቸውን ሐዋርያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖችን በመዳሰስ፣ ነባራዊ የሆነውን የዓለማችንን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን እና የሀገራችንን ሁኔታ በዳሰሰ እና ከግምት ባስገባ መልኩ ወደ እናንተ በማቅረብ ላይ እንደ ምንገኝ ይታወቃል።
በክፍል አንድ ዝግጅታችን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ጠቅላላ ይዘቱን እና ፅንሰ-ሐሳቡን መመልከት መጀመራችን ይታወሳል። በክፍል አንድ ዝግጅታችን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ ጠቅላላ ይዘቱን እና ፅንሰ-ሐሳቡን በቀጣይነት በተከታታይ ለምናደርገው አስተምህሮ የመሰረት ድንጋይ የሚጥል በመሆኑ የተነሳ አንድ በአንድ መመልከት መጀመራችን የሚታወስ ሲሆን በዛሬው በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መሰረታዊ የሆኑ ጽንሰ-ሐሳቦችን በጥልቀት እንዳስሳለን።
ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትሳተፍላች
ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ከተመሰረተችበት ቀን አንስቶ እስከ ዛሬ ቀን ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ በመሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ በሕዝቦች ላይ የሚደረሰውን ማኅበራዊ ጫናና በደል በመቃወም ለዓለም ድምጽዋን ስታሰማ መቆየቷን፣ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ ሰላማዊ በሆነ መልኩ የመሳተፍ መብት እንዲኖራት ሕጋዊ እና ስነ-ምግባራዊ በሆነ መልኩ እንድትሳተፍ መብት የሚሰጣትን ዋና ዋና መሰረታዊ የሆኑ ሐሳቦችን በክፍል አንድ ዝግጅታችን ጠቅሰን መዳሰሳችን ይታወሳል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ትሳተፋለች ሲባል “በአንድ ሀገር ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ትገባለች” ማለት እንዳልሆነ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱትን በደሎች፣ ኢፍታዊ ተግባሮችን፣ በተለይም ደግሞ ዝቅተኛ እና ድሃ በሚባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ የምደርሰውን በደል በመቃወም ለዓለም ድምጹዋን ታሰማለች ማለት እንደ ሆነ ልብ ልባል ይገባል።
ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው መላእክትን ለመጠበቅ አይደለም
በእዚህ ረገድ የቤተክርስቲያናችን ተልዕኮ አንድ እና አንድ ብቻ ነው፣ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችው መልኣክትን ለመጠበቅ ሳይሆን ሳይሆን የሰው ልጆችን አቅፋ ደግፋ፣ በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ/እንዲያድጉ በማድረግ፣ “የሕዝቡ ደስታ ደስታዬ፣ የሕዝቡ ለቅሶ ደግሞ ለቅሶዬ ወይም ሐዘኔ ነው” (ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ) በማለት ሕዝቡ በሰላም እና በደስታ እግዚኣብሔር የሰጣቸውን በረከት እየታቋዳሱ እንዲኖሩ ለማድረግ፣ በመጨረሻም የሰው ልጆችን ለእግዚኣብሔር መንግሥት የማብቃት መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ የሆነ ተልዕኮ እንደ ተሰጣት ይታወቃል።
በመጽሐፍ ቅዱሳችንም ውስጥ ይህ ጽንሰ-ሐስብ በብዙ ስፍራዎች ተጠቅሶ ይገኛል። ለምሳሌ “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እርሱ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩት መፈታትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቈኑትን ነጻ እንዳወጣ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እንዳውጅ ልኮኛል” (ሉቃስ 4፡18) በማለት ኢየሱስ እዚህ ምድር የመጣበትን ዋነኛ ዓላማ ሲገልጽ እንሰማለን።
በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው እና “የድኾች አባት” በማባል የሚታወቀው የፈረንሳይ ሀገር ተወላጅ የነበረው ቅዱስ ቪንሰንት ዲ ፖል ይህንን የእየሱስን ዓላማ የግሉ መፈክር አድርጎ በመያዝ በወቅቱ በፈረንሳይ አገር ለነበሩ የድሃ ማህበረሰቦች አልኝታነቱን በመግለጽ ሐብታሞችን ከድኾች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን ማኅበራዊ ፍትህ ይሰፍን ዘንድ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋጾ አድርጎ ማለፉን፣ በተመሳሳይ መልኩም በጣም ብዙ የሚባሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁዱሳን ለድኾች ያላቸውን አለኝታ በመግልጽ ጭቆና እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች እንዲወገዱ የበኩላቸውን ሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገው አልፈዋል። ቤተክርስቲያናችንም የክርስቶስን እና የእነዚህ ቅዱሳንን ፈለግ በመከተል በሕዝቦች ላይ የሚፈጸሙትን በደሎች ሁሉ “በዛሬ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ደስታና ተስፋ፣ ሐዘን እና መከራ ከሁሉም በላይ ደግሞ ድሆች እና መከራ የሚደርስባቸው ሰዎች ሁሉ፣ ደስታቸው እና ተስፋቸው፣ ሐዘናቸው እና መከራቸው ሁሉ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የሚጋሩት እና በማንኛውም እውነተኛ በሆነ ሰው ልብ ውስጥ የሚያስተጋቡ ነገሮች ናቸው” (Gaudium et Spece no. 1) በማለት ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን በደል እንደ ራሷ በደል አድርጋ በመቁጠር ለቅሶዋቸው ለቅሶዋ፣ ሐዘናቸው ሐዘኔ ነው በማለት አሁንም የሰላም እና የፍትህ ጥሪዋን ታሰማለች።
ቤተ ክርስቲያን ይህንን የምታድርግበት ምክንያት ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደ ሞከርኩት “የሰው ልጆችን ማዕከል” ባደርገ መልኩ ነው። የሰው ልጆች ባሉበት እመንት አለ፣ እምነት ባለበት ቤተክርስትያን አለች፣ ቤተክርስቲያን ባለችበት ማኅበረሰብ አለ፣ ማኅበርሰብ ባለበት ደግሞ መልካም እና ክፉ የሆኑ ነገሮች ይንጸባረቃሉ፣ ቤተክርስቲያን ስነ-ምግባራዊ የሆኑ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ፣ ሰዎች በስላም እና በመከባበር እንዲኖሩ መልካም የሆኑ ነገሮችን በማበረታታት በተቃራኒው ደግሞ የማኅበርሰቡን ሰላም የሚነሳውን ክፉ ነገሮችን በብርቱ በመቃወም፣ እንዳይስፋፉም በወንጌል እና በስበኣዊነት ላይ የተመሰረቱ አስተምህሮችን ትሰጣለች። ምክንያቱም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች እና ኢፍታዊ ድርጊቶች ምክንያት የሚጎዳው ያው የሰው ልጅ በመሆኑ ነው፣ በተለይም አቅም ደካማ የሆነ እና ድሃ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በመሆኑ የተነሳ ማኅበራዊ አስተምህሮ አስፈላጊ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ታምንበታለች።
አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን