ፈልግ

በአፍሪቃ ውስጥ አመጽ እና ጦርነት ያስከተለው የስደት ቀውስ፣ በአፍሪቃ ውስጥ አመጽ እና ጦርነት ያስከተለው የስደት ቀውስ፣ 

“በችግር ምክንያት ከማኅበረሰቡ መካከል የተፈናቀሉትን መርሳት የለብንም”።

በአመጽ፣ በጦርነት እና በሌሎች ልዩ ልዩ አደጋዎች ምክንያት በአገር ውስጥ የሚፈናቀሉትን ለመርዳት እና መልሶ ለማቋቋም የአብያተ ክርስቲያናት እና የመንግሥት ተቋማት እገዛ ማስፈለጉን ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አስታውቀው፣ በማከልም በችግር ምክንያት ከማኅበረሰቡ መካከል የተገለሉትን ወይም የተፈናቀሉትን መርሳት የለብንም” ማለታቸው ታውቋል።

የቫቲካን ዜና

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እንደሚያሳስቡት መላዋ ቤተክርስቲያን ዕርዳታዋን ወደ ተቸገሩት በመመለስ በተለይም ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ለበርካታ ወራት እና ዓመታት ሰብዓዊ መብታቸውን የተገፈፉትንና እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለመርዳት የምትችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ መሆኗ ታውቋል። ይህን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ለመፈጸም ያግዛት ዘንድ፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ውስጥ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ቢሮ በኩል አዲስ መመሪያ መዘጋጀቱ ታውቋል። መመሪያው በጦርነት፣ በጎሳ ግጭት፣ በረሃብ እና በአየር ለውጥ ምክንያት ቄያቸውን ለቀው ለሚሰደዱት የአገር ውስጥ ተፈላቃዮችን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ ዕርዳታን ለማቅረብ የሚያግዝ መመሪያ መሆኑን ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ ከቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2020 ዓ. ም. መግቢያ ላይ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ባደረጉበት ጊዜ፣ በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት ከማኅበረሰቡ ተገልለው በችግር ወስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦች ትኩረት በመስጠት አስፈላጊውን ዕርዳታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበው ቤተክርስቲያንም እነዚህን ችግረኞች በፍቅር ተቀብላ አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ የምትፈልግ መሆኗን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት በቅድስት መንበር የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ የሚከታተል ቢሮ በየአገራቱ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብ የሚያግዝ መመሪያ ማዘጋጀት ታውቋል። የዚህ መመሪያ መነሻ ሃሳቡ፣ ቅዱስ ዮሴፍ፣ እመቤታችን ቅድስት ማርያም እና ሕጻኑ ኢየሱስ ክርስቶስ የመኖሪያ ሥፍራቸውን ለቅው የደረሰባቸውን ችግር ለማምለጥ ወደ ግብጽ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የቀን አቆጣጠር በ2019 ዓ. ም. ብቻ 33.4 ሚሊዮን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በ145 አገሮች ውስጥ መመዝገባቸውን ያስታወሱት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ፣ ከእነዚህ ተፈናቃዮች መካከል 8,5 ሚሊዮን የሚሆኑት በክልላቸው በሚከሰቱ ጦርነቶች እና አመጾች ሲሆን፣ በቁጥር 1,900 በሚሆኑ አደጋዎች ምክንያት 25 ሚሊዮን ተፈናቃዮች በ140 አገሮች ውስጥ መመዝገባቸው ታውቋል። በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ለይቶ በማወቅ መጠለያንና ሌሎች እርዳታዎችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አስረድተዋል። ለተፈናቃይ ቤተሰቦች የሕይወት ከለላንና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን ማቅረብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ፣ ይህም እያንዳንዱ አገር ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ባለው ግንኙነት የሚወሰን ይሆናል ብለዋል። ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን እንደ ማኅበራዊ ሸክም አድርጎ ከመቁጠር ይልቅ በማኅበራዊ እድገት እቅዶች በማሳተፍ ራሳቸውን እና የሚገኙበትን ማኅበረሰብ መጥቀም የሚችሉ መሆናቸው ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አስረድተዋል። ተፈናቃዮችን ከሚገኙበት ማኅበረሰብ ጋር ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረግ ከሚደረግላቸ ድጋፍ አንዱ መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ፣ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ መካከል መገለል እንዳያጋጥማቸው፣ እንደ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጥረት ከሌሎች የስው ልጆች ጋር ግንኙነት ያላቸው የአንድ እግዚአብሔር አባት ልጆች መሆናቸውን ማስረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

አንዳንድ አገሮች ከመኖሪያ አካባቢዎች ለሚፈናቀሉት ሰዎች የሚደረገውን ድጋፍ እንደ መሠረታዊ መብት በመቁጠር ተግባር ላይ የሚያውሉት መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ፣ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ወደ ከተሞች ዙሪያ በመምጣት የከተማውን ሕዝብ ቁጥር ከፍ እንደሚያደርጉ ጠቅሰው ይህ በሚሆንበት ጊዜ በከተማው ዙሪያ ለሚሰፍሩት ቤተሰቦች የዕለት ቀለባቸውን፣ የጤና እና የትምህርት ዕድሎችን ማመቻቸት ግዴታ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም ይህን ችግር ለማቃለል የተለያዩ ማኅበራት እና ተቋማት ሕብረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው አዲስ ባረቀቁት መመሪያ ውስጥ የተቋማት ሕብረት የሚለዉን ሃሳብ ማካተታቸውን አስታውሰዋል። ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ በማከልም በዚህ ዙሪያ ከካቶሊካዊ ድርጅቶች እና ሀገረ ስብከቶች ጋር ተባብረው የሚሠሩ ሐይማኖታዊ ተቋማት እና የአብያተ ክስርቲያናት ድርጅቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በተረቀቁ መመሪያዎች፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉትን ለመርዳት በሚል ዓላም የተቋቋሙ የተለያዩ መንግሥታዊ እና የግል ተቋማት ተባብረው የሚሰሩበት አጋጣሚ መኖሩን ያስታወሱት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አስረድተዋል። ለእነዚህ የአገር ውስጥ ተቋማት ዓለማ አቀፋዊ እውቅና ይጎድላቸዋል ያሉት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ ይህም ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር የሚያግዙ ሕጎችን ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸው፣ ሆኖም ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል እየተጠና መሆኑን አስረድተዋል።

በተፈናቃዮች ላይ የሚደረግ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መኖሩን ያስታወሱት ክቡር አባ ፋቢዮ፣ ይህ ተግባር እያደገ መምጣቱን ጥቁመው ወደ መጡበት መንደር ተመልሰው የተሟላ ሕይወት መኖር እስካልቻሉ እና በሚሰደዱበት አካባቢ ለብዙ ዓመታት የሚቆዩ ከሆነው በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ወንጀለኞች እጅ መውደቃቸው አይቀርም ብለው አክለውም በማይሆን ተስፋ በቀላሉ በመታለል፣ የአካል ክፍላቸውን ተውስደው ለሞት የሚዳረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ በመጨረሻም ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎ ዓላማ በመመለስ ዘንድሮ በተከበረው የብርሃነ ትንሳኤው ክብረ በዓል፣ ለሮም ከተማ እና ለመላው ዓለም ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአስከፊ ሁኔታ ላይ የሚገኙትን በተለይም ከማኅበረሰብ ተገልለው አስፈላጊውን እገዛ ተንፍገው የሚገኙትን መዘንጋት የለብንም ማለታቸውን አታውሰው፣ በየከታማዉ ዙሪያ የድህነት እና የመከራ ሕይወት የሚኖሩትን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መርሳት የለብንም በማለት፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ መምሪያ ምክትል ዋና ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ፋቢዮ ባጆ አሳስበዋል። 

06 May 2020, 23:13