2ኛው የቫቲካን ጉባኤ፣ በእምነቶች መካከል የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ መንገድ የከፈተ መሆኑ ተገለጸ።
ባለፉት ዓመታት ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ይዘት በማጥናት ትርጉሙን በቀላል አገላለጽ ለማቀርብ ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ታውቋል። ሰነዱን ለማጽደቅ የተቀመጠው ጉባኤ በቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ የተሰጠው ሆኖ ተግኝቷል።
የቫቲካን ዜና፤
በቤተክርስቲያን አባቶች የተዘጋጀው እና በኋላም እንደ ጎርጎሮስውያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 28/1965 ዓ. ም. በቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ጸድቆ ይፋ የሆነው፣ በላቲን ቋንቋ “nostra aetate” ወደ አማርኛው ሲተረጎም “የእኛ ዘመን” የተሰኘው ሐዋርያዊ ሰነድ፣ በሐይማኖቶች መካከል የጋራ ውይይቶችን ለማካሄድ መልካም መንገድ መክፈቱ ይታወሳል። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በአይሁድ እምነት መካከል ግንኙነት ለመፍጠር የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ ለጀመሩት ጥረትም መልካም ውጤቶችን እንዳስገኘ እና ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ከተቀሩት ክርስቲያን ካልሆኑ እምነቶች ጋር መመስረት ለምትፈልገው የጋራ ውይይቶች መልካም መንገድ መፍጠሩ ይታወሳል። ሐዋርያዊ ሰነዱ ለጋራ ውይይት አመቺ መንገዶችን በመጠቆም በሐይማኖቶች መካከል የጋራ ወይይት ለማድረግ የሚያስችል የርጅም ጊዜ የሥራ ውጤት መሆኑ ታውቋል።
በክርስትና እና በአይሁድ እምነት መካከል ልዩ ግንኙነት እንዲፈጠር፣
በሐዋርያዊ ሰነዱ ውስጥ ከተጠቀሱት ሃሳቦች መካከል ማዕከላዊ ሥፍራ የሚሰጠው፣ በክርስትና እና በአይሁድ እምነት መካከል ያለውን ግንኙነት አጉልቶ የሚያሳይ ክፍል ነው። በዚህ ሐዋርያዊ ሰነድ አማካይነት ጠቅላላ ጉባኤው የአዲስ ኪዳን ዘመን ሕዝብ በመንፈሳዊነቱ ከአብርሃም ዘመን ወይም ከብሉይ ኪዳን ዘመን ሕዝብ ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ያስገነዝባል። በዚህ የጋራ መንፈሳዊ ሃብት በመመራት የክርስትና እና የአይሁድ እምነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ እና በስነ መልኮት ጥናቶች በመታገዝ በሁለቱ እምነቶች መካከል ያለው ግንኙነት በወንድማዊ ውይይት እንዲያድግ ጉባኤው ፍላጎቱን ገልጿል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሚያዚያ ወር 1986 ዓ. ም. በሮም ከተማ የሚገኘውን የአይሁድ ምኩራብ በጎኙበት ወቅት፣ የክርስትናን እና የአይሁድ እምነቶች የጋራ መሠረት የሚያረጋግጡ፣ በሁለቱ እምነቶች መካከል ልዩ ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያደረጉ በርካታ የጋራ ቃላት እንዳሉ መናገራቸው ይታወሳል። ከር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በመቀጠል እንደ ጎርጎሮሳዊያን የቀን አቆጣጠር 2010 ዓ. ም. በሮም የሚገኘውን የአይሁድ ምኩራብን የጎበኙት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛም “የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ውጤት የሆነው የጉባኤው ሰነድ፣ የካቶሊክ እና የአይሁድ እምነት ተከታይ ምዕመናን በመካከላቸው አዲስ ግንኙነትን እና ዘላቂ አንድነት ለመፍጠር የሚያግዙ፣ ወንድማዊ የወዳጅነት ውይይት እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
በአይሁድ ህዝብ ላይ ለተፈጸመው ግድያ የሚቀርብ ክስ ያበቃ ዘንድ፣
በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ውስጥ የተጠቀሰው ሌላው ሃሳብ፣ ፀረ-ሴማዊነትን የሚያወግዝ ክፍል መሆኑ ተመልክቷል። በአይሁዶች ላይ የሚንጸባረቅ የጥላቻ እና የስቃይ ተግባር፣ በማንኛውም ቦታ እና ጊዜ አይሁዶችን ያነጣጠሩ ፀረ-ሴማዊነት ሰልፎች፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በደፈናው የአይሁድ ማኅበረሰብን በሙሉ ተጠያቂ ከማድረግ መቆጠብ እንዳለበት ሐዋርያዊ ሰነዱ ያስገነዝባል። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ለተፈጸመው ግድያ ተጠያቂ የሚሆኑት የአይሁድ እምነት ተከታዮች በሙሉ እንዳልሆኑ እና አሁን በዘመናችን የሚገኙ የአይሁድ እምነት ተከታዮችንም ተጠያቂ ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ ሐዋርያዊ ሰነዱ በአጽንዖት ያስረዳል።
በሌሎች እምነቶች መካከል ያለውን እውነት መመልከት፣
በላቲን ቋንቋ “nostra aetate” በግርድፉ ሲተረጎም “የእኛ ዘመን” የተሰኘው ሐዋርያዊ ሰነዱ በመጀመርያ ምዕራፉ፣ “የሂንዱ፣ የቡዳ እና ሌሎች እምነቶች መሠረታዊ ዓላማ በምዕመናኖቻቸው ልብ ውስጥ መልካም እንዲያስቡ የሚያደርጋቸውን መንፈሳዊ አስተምህሮችን እና የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚያስተምሩ ናቸው” በማለት ይገልጻቸዋል። ካቶሊክ ቤተክርስቲያንም በእነዚህ እምነቶች አስተምህሮ ውስጥ እውነት እና የተቀደሱ መንገዶች መኖራቸውን ያምናል። የሌሎች እምነቶች እውነታዎች እና አስተምህሮች በንጹህ ልብ ተቀብሎ በማክበር፣ በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ እውነተኛ እምነት እንዲጣልበት እና እንዲሰርጽ በማለት ምኞቱን ይገልጻል።
ለእስልምና እምነት ተከታዮች ሊሰጥ የሚገባ አክብሮት፣
ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሐዋርያዊ ሰነዱ በሌላው ምዕራፍ ላይ፣ ለእስልምና ሐይማኖት ባለው ታላቅ አክብሮቱ፣ የእስልምና እምነት ሰማይንና ምድርን በፈጠረ፣ ርኅሩኅ እና ሁሉን ቻይ በሆነው እና የተስፋ ቃሉን ለሰው ልጅ በተናገረው አንድ አምላክ የሚያመልክ የእምነት መንገድ መሆኑን በስፋት ያብራራል። ሐዋርያዊ ሰነዱ በተጨማሪም የእስልምና እምነት በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱትን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳኖቹን በሙሉ ልብ የሚቀበል መሆኑን ያስረዳል። ኢየሱስ ክርስቶስን ነቢይ እንደሆነ በማመን፣ ለእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብርን በመስጠት፣ ውዳሴን የሚያቀርብ መሆኑን ያስረስዳል። የእስልምና እምነት በዚህ ብቻ ሳያበቃ በክርስትና እምነት ውስጥ የሚፈጸሙ መንፈሳዊ እና ሞራላዊ ግዴታውችን፣ ከእነዚህ መካከል የዘወትር ጸሎትን፣ የተቸገረን መርዳት እና ጾም የሚያዘወትር መሆኑን ይጠቅሳል።
ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እና የእስልምና እምነት አባቶች፣
ባለፉት ዓመታት በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች መካከል ለተደረጉት የጋራ ውይይቶች እንደ መልካም ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ሐምሌ ወር 1969 ዓ. ም. የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በኡጋንዳ ውስጥ የተገደሉ ሰማዕታትን ለማስታወስ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ፣ የሰማዕትነት ተጋድሎው በአካባቢው በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ከደረሰው ስቃይ ጋር በማወዳደር “በእኛ እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል አንድ የሚያደርገን የጋራ እሴቶች እንዳሉን እርግጠኞች ነን” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ከፍተኛ የእስልምና ሐይማኖት መሪዎች በተገኙበት በካምፓላ ንግግራቸው የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እንደተናገሩት፥ “በቅዱስ ወንጌል እና በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ የተገለጸው የእርቅ እና የምህረት መንገድ የእግዚአብሔር ልጆች በሆኑት የአፍሪካ ሕዝቦች ልብ ውስጥ በተግባር እንዲገለጽ ጸሎታችንን እናቀርባለን” በማለት መናገራቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ንግግራቸውን በመቀጠል “ታሪክ ሁል ጊዜ ሲያስታውሰው የሚኖረውን የካቶሊክ፣ የፕሮቴስታንት እና የእስልምና እምነት ተከታዮች በጋራ የሰጡትን ምስክርነት፣ ለእምነታቸው የከፈሉትን ሰማዕትነት አንድ ላይ መመልከት ያስፈልጋል” ማለታቸው ይታወሳል።
የአብርሐም ዘሮች ነን፣
የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር በህዳር ወር 1979 ዓ. ም. ወደ ቱርክ ዋና ከተማ አንካራ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ለአገሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ያላትን ፍቅር ሲገልጹ “በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነት ኅብረት ያለን የአብርሐም ልጆች፣ የክርስትና፣ የእስልምና እና የአይሁድ እምነት ተከታዮች፣ ይህን የጋራ እምነታችንን በሕይወታችን ውስጥ በተግባር ስንኖርበት፣ ሰብዓዊ ክብራችንን የምናስጠብቅበት፣ የወንድማማችነት እና የነጻነት ሕይወት የምንኖርበት፣ በመልካም ስነ ምግባር ማኅበራዊ ሕይወትን በጋራ በሰላም መኖር የምንችልበት መንገድ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
የካዛ ብላንካ ንግግር፣
የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ነሐሴ ወር 1985 ዓ. ም. ወደ ሞሮኮ፣ ካዛ ብላንካ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት፣ የእስልምና እምነት ተከታይ ወጣቶች ለቅዱስነታቸው ባሰሙት ንግግር፣ በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል በርካታ የጋራ እሴቶች እንዳሉ፣ በአንድ ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩ፣ ብዙ የተስፋ ምልክቶችን የሚያዩ፣ ችግሮችንም በጋራ የሚጋፈጡ እንደሆኑ መናገራቸውን አስታውሰዋል። “አብርሐም ለሁላችንም የእምነት አባታችን ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው “በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት በእርሱ በመታመን እንደ እርሱ ፈቃድ እንድንኖር ያስገድደናል” ብለዋል። “ዓለምን በፈጠረ፣ ፍጥረቱን ወደ ፍጹምነት በሚመራው በአንድ እግዚአብሔር እናምናለን” ያሉት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት ከምን ጊዜም በላይ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሳነ ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና ቤነዲክቶስ 16ኛ በአሲሲ፣
እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ጥቅምት 27/1986 ዓ. ም. ለሰላም ጸሎት እንዲደረግ በማለት፣ ልዩ ልዩ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮችን ወደ አሲሲ ከተማ የጋበዙት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በሐይማኖት ተቋማት መካከል ቀጣይነት ያለው የጋራ ውይይት ለማካሄድ እያንዳንዱ ምዕመን የበኩሉ ጥረት እንዲያድረግ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ባሁኑ ጊዜ በሐይማኖት ተቋማት መካከል የሚታየው መቀራረብ እና የሰላም ጭላንጭል፣ በፖለቲከኞች ጥረት እና በኤኮኖሚ ውህደት የተገኘ ሳይሆን ከሁሉም በላይ የጋራ ጸሎት ውጤት መሆኑን ታውቋል። በ25ኛ ዙር የሰላም ቀን መታሰቢያ ዕለት፣ ከሌሎች የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች ጋር በአሲሲ ተገኝተው ንግግር ያሰሙት የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቤነዲክቶስ 16ኛ፣ በእግዚአብሔር ስም የሚካሄዱ አመጾች እና ጥላቻዎች፣ በረጅም የክርስትና ታሪክ ውስጥ የተገለጹ የጦርነት ተግባራት አሳፋሪ እና ውርደትን ከማውረስ በተጨማሪ ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ እንቢ በማለት፣ በራስ ምርጫ የተፈጸሙ አመጾች መሆናቸውን ገልጸው፣ ለዚህም በማጎሪያ ካምፖቹ የተፈጸሙ አሰቃቂ ተግባሮችን እንደ ማሳያነት ማቅረብ ይቻላል ብለዋል።
ከቫቲካን ጉባኤ እስከ አቡ ዱቢ ሰነድ፣
“የእኛ ዘመን” የተሰኘው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሐዋርያዊ ሰነድ መግለጫ በመጨረሻ ምዕራፉ፣ ዓለም አቀፍ ወንድማማችነትን አስታውሶ ባቀረበው ሃሳቡ፣ አንድነታችንን ካልተቀበልን፣ በወንድማማችነት መንፈስ የማንኖር ከሆነ፣ እግዚአብሔርን የጋራ አባት ብሎ መጥራት፣ በእርሱ አምሳል የተፈጠርን ነን ማለት የማይቻል መሆኑን አስታውቋል። የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት፣ ከወንድሙም ጋር መተመሳሳይ ሁኔታ መገለጽ ይኖርበታል ያለው የሐዋርያዊ ሰነድ መግለጫው፣ በቅዱስ ቃሉ ላይ “ወንድሙን የማይወድ እግዚአብሔርን አያውቅም” የሚለውን በመጥቀስ፣ ማንኛውንም ፅንሰ-ሀሳብ እና ቃላት በመጠቀም በሕዝቦች መካከል ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ተግባራ እንዲያበቁ አሳስቧል። እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር የካቲት 4/2019 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በታላቁ ኢማም፣ አል አዛር አህመድ አል ጣይብ መካከል፣ በአቡዳቢ ከተማ በተፈረመው የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሰንድ ውስጥ “እግዚአብሔር የፈጠራቸው ሰዎች በሰብዓዊ መብታቸው፣ ግዴታቸው እና ክብራቸው እኩል በመሆናቸው፣ በወንድማማችነት መንፈስ እየኖሩ መልካም የጋራ እሴቶችን፣ ቸርነትን እና ሰላምን እንዲያሳድጉ ተጠርተዋል” የሚለውን ሃሳብ ሐዋርያዊ ሰነዱ በመግለጫው አስታውሷል።