ፈልግ

የቫቲካን ፖሊስ ፤ የቫቲካን ፖሊስ ፤ 

በለንደን የሚገኝ የቤተክርስቲያን ንብረት የምርመራ ሂደት ውጤት ይፋ ተደረገ።

በቫቲካን ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ሲጣራ የቆየው እና በለንደን የሚገኘው ሕንጻ ግዥ አደራዳሪ የነበሩትን አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲን ቫቲካን በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገለጸ። በለንደን ከተማ ውስጥ ስሎን ጎዳና የሚገኘው ግዙፍ ሕንጻ ግዥን ለማደራደር የቀረቡት አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲ የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ወደ ቫቲካን ፍርድ ቤት ቀርበው በመጀመሪያ ደረጃ የምርምራ ውጤት ወንጀለኛ ተብለው በቫቲካን ፖሊስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቫቲካን ኒውስ አስታውቋል።  

የቫቲካን ዜና፤

ለንደን ከተማ የሚገኝ ሕንጻ ግዥ አደራዳሪነት የተመረጡት አቶ ጃንሉዊጂ ቶርዚ በቁጥጥር ስር የዋሉት በቫቲካን የፍትህ አካላት እና የቫቲካን ፖሊስ በመተባበር ባካሄዱት ረዥም እና ውስብስብ ምርመራ በኋላ፣ ዓርብ ግንቦት 28/2012 ዓ. ም. መሆኑ ታውቋል። የፖሊስ ምርመራ የተደረገባቸው ሌሎች አምስት ግለሰቦች ሲሆኑ፣ በቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሚሠሩ ሁለት የቤተክህነት አባላት እና ሦስት ሠራተኞች መሆናቸው ታውቋል። ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች በተጨማሪ አንድ የሂሳብ መረጃ ክፍል ሥራ አስኪያጅ የሚገኝበት መሆኑን ቫቲካን ኒውስ አክሎ አስታውቋል።  

የሃይማኖታዊ ሥራዎች ተቋም ጠቅላላ አቤቱታዎች፣

የቫቲካን ፍርድ ቤት የምርመራ ሂደቱን መሠረት ያደረገው፣ ከዚህ በፊት በቅድስት መንበር የሃይማኖታዊ ሥራ አስከያጅ ተቋም በተቀበላቸው ሁለት የአቤቱታ ጥያቄዎች መሆኑ ታውቋል። የምርመራ ሂደቱን በሁለት ደረጃዎች ከፍሎ የተመለከተው የቫቲካን ፍርድ ቤት፣ የመጀመሪያው የምርመራ ሂደት የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2014 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ውስጥ “አቴና ካፒታል ግሎባል ኦፖርቹኒቲ ፈንድ” የተባለ ተቋምን በበላይነት ይመሩት የነበሩት እና በሎንደን ከተማ ስሎን ጎዳና የሚገኘው ሕንጻ ባለቤት በሆኑት በአቶ ራፋኤለ ሚንቾኔ ላይ መሆኑ ታውቋል። ሁለተኛው የምርመራ ሂደት የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር ከ2018 ዓ. ም. መጨረሻ እስከ 2019 ዓ. ም. የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት መከከል መሆኑ ታውቋል። በዚህ መካከል “አቴና ካፒታል ግሎባል ኦፖርቹኒትይ ፈንድ” ከተባለ ተቋም ገንዘብ ወጥቶ፣ በለንደን ከተማ ውስጥ ስሎን ጎዳና የሚገኘውን የአቶ ራፋኤለ ሚንቾኔ ሕንጻ ለመግዛት፣ አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲ በአደራዳሪነት ገብተው የማጭበርበር ተግባር በመፈጸማቸው ነው ተብሏል።

የ እ. አ. አ. የ2014 ፈንድ፣

የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት “አቴና ካፒታል ግሎባል ኦፖርቹኒቲ ፈንድ” ከተባለው እና በአቶ ራፋኤለ ሚንቾኔ ይመራ ከነበረው ተቋም፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስኬጃ ከተቀመጠው 454 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሁለት መቶ ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ ዶላር በማውጣት ለህንጻ ግዥ ማዋሉ ታውቋል። ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለንደን ከተማ ይገኛል ከተባለው ግዙፍ ሕንጻ 45 እጅ ከመቶ ለመግዛት መስማማቱ ታውቋል። ከቫቲካን መንግሥት ፍርድ ቤት የማረጋገጫ ሰነድ ለመረዳት እንደተቻለው እንደ ጎርጎሮስዊያኑ የቀን አቆጣጠር ህዳር ወር 2018 ዓ. ም. የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ መጠን፣ 137 ሚሊዮን ኤውሮ ብቻ እንደነበር እና ይህም ከጠቅላላው ተቀማጭ ገንዘብ 18 ሚሊዮን ኤውሮ መጉደሉን የሚያሳይ መሆኑ ታውቋል።

የሎንደን ሕንጻ ግዥ አደራዳሪ፣ አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲ፣

በቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የአስተዳደር ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ ፋብሪሲዮ ቲራባሲ “አቴና ካፒታል ግሎባል ኦፖርቹኒቲ ፈንድ” የተባለ ተቋም መሪ እና ሎንደን ከተማ የሚገኝ ሕንጻ ባለቤት ከሆኑት ከአቶ ራፋኤለ ሚንቾኔ እና ጠበቃቸው ከሆኑት ከአቶ ማኑኤለ ኢንተደንተ ጋር በመስማማት፣ በግዢው ሂደት በአደራዳሪነት እንዲያገለግሉ በማለት አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲን መምረጣቸው ታውቋል። በአደራዳሪነት የተመደቡት አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲ ከጎርጎሮሳዊያኑ የቀን አቆጣጠር 2018 ዓ. ም. ወዲህ የሚያቀርቡት የገንዘብ ጥያቄ እና ሪፖርት ከሚፈለገው ልክ በላይ እና እምነት የጎደለው ሆኖ ከመታየቱ በተጨማሪ የሕንጻው ባለቤትነት የተለያዩ የውጭ አገራት የገንዘብ ተቋማትን ያሳተፈ በመሆኑ፣ የቅድስት መንበር ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የባለቤትነት መብት ጥርጣሬ ወስጥ እንዲገባ ማድረጋቸው ታውቋል።  ጉዳዩ በቫቲካን ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ሲጣራ ቆይቶ፣ የሕንጻ ግዥ አደራዳሪ የነበሩትን አቶ ጃንሉዊጂ ቶርሲ በቫቲካን የፍትህ አካላት ከቫቲካን ፖሊስ ጋር በመተባበር ባካሄዱት ስምንት ሰዓት በወሰደው ውስብስብ ምርመራ በኋላ ዓርብ ግንቦት 28/2012 ዓ. ም. በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቫቲካን ኒውስ አስታውቋል።

09 June 2020, 17:23