ካርዲና ራኔሮ ካንታላሜሳ ከኢየሱስ ማንነት ጋር የግል ግንኙነት መፍጠር ይገባል አሉ!
የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ አሁን የምንገኝበት ወቅት የዐብይ ጾም ሳምንት መጠናቀቂያ ሳምንት ላይ ሲሆን ነገ መጋቢት 19/2013 ዓ.ም ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራውን ለመቀበል በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩስአሌም የገባበት የሆሳህና በዓል እንደ ሚከበር ይጠበቃል።
የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን
በዚህ የመጨረሻው የዐብይ ጾም ሳምንት ተገቢ የሆነ መንፈሳዊ ዝግጅት ለማድረግ ይቻል ዘንድ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት እና በቫቲካን የእርሳቸው የቅርብ የሥራ ተባባሪ የሆኑት ብጹዕን ጳጳሳት እና ቀሳውስት በአጠቃላይ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ሰባኪ የሆኑት ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ ይህንን የዐብይ ጾም ወቅት ምክንያት በማደረግ ዘወትር አርብ እለት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተገኙበት መንፈሳዊ አስተንትኖ እንደ ሚያደርጉ ከእዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። በእዚህም መሰረት እርሳቸው ለእዚህ ለጎርጎሮሳዊያኑ 2021 ዓ.ም የዐብይ ጾም ወቅት የመረጡት መሪ ሐሳብ “ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?” የሚለው ከማቴዎስ ወንጌል በተወሰደው ጥቅስ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደ ሆነ የተገለጸ ሲሆን በመጋቢት 17/2013 ዓ.ም በቫቲካን ባደረጉት አስተንትኖ ከኢየሱስ ማንነት ጋር ያለንን ግንኙነት አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ማለታቸው ተገልጿል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ስባኪ የሆኑት ካርዲናል ራኒሮ ካንታላሜሳ በወቅቱ ባደረጉት አስተንትኖ ከኢየሱስ ጋር በእውነተኛ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ መግባት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲያስረዱ ከሁሉም ሥነ-መለኮታዊ እና አስተምህሮዊ ውይይቶች የዘለለ ነው - ምክንያቱም እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ ነው ብለዋል።
ለሰው አዕምሮ ትልቁ እና የማይደረስበት ምስጢር እግዚአብሔር አንድ እና ሶስት ነው የሚለው ግንዛቤ አይደለም ፣ ነገር ግን እርሱ ምስኪን እና ምስጋና ያልተቸረው አካል እኔን የሚወድ እና እራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነው የሚለው ሐሳብ ነው ብለዋል። አንድ ሰው ‘እኔ’ ከሚለው አስተሳሰብ ወደ “አንተ” ወደ ሚለው አስተሳሰብ በመሻገር ከእሱ ጋር የግል ግንኙነት ውስጥ ካልገባ በስተቀር ኢየሱስ እንደ ሰው ሊታወቅ አይችልም ያሉት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ሰባኪ ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ አርብ ዕለት መጋቢት 17/2013 ዓ.ም ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እና ለቅርብ የሥራ ተባባሪዎቻቸው ባስተላለፉት የዚህ ሳምንት የዐብይ ጾም ሳምንት አስተንትኖ ላይ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ክርስቶስ - ሕያው ሰው ነው፣ ሀሳብ ወይም ገጸ ባህሪ አይደለም
ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ እንዳመለከቱት ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የሃይማኖት ምሁራን ፣ የቤተክርስቲያን ጉባሄዎች እና የቤተክርስቲያን አባቶች ኢየሱስ “እውነተኛ ሰው” እና “እውነተኛ አምላክ” አንድ አካል መሆኑን ማረጋገጥ ችለዋል። "ይህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሀሳብ ፣ ታሪካዊ ጉዳይ ወይም ገጸ ባህሪ ብቻ አለመሆኑን ማወቅ እና ማወጅን ያካትታል ፣ ነገር ግን እሱ አካል ነው ፣ እናም ለዚያም ሕያው ነው" ያሉ ሲሆን “ክርስትና ወደ ርዕዮተ ዓለም ወይንም በቀላሉ ወደ ሥነ-መለኮት አስተምሮ ብቻ እንዳይቀየር ለመከላከል የጎደለው እና በጣም የምንፈልገው ነገር ነው” ብለዋል።
ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ አስተንትኖዋቸውን ሲቀጥሉ እርሳቸውም ቢሆኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት የእዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ሰለባ እንደ ነበሩ በትህትና አምነዋል። በእዚህ መስረት እርሳቸው ስለኢየሱስ የተጻፉ መጻሕፍትን ፣ በኢየሱስ ላይ የተመሠረቱ ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎችን እና ዶክትሪኖችን፣ እንዲሁም ስለኢየሱስ ያላቸው ፅንሰ-ሀሳቦችን እንደሚያውቁ አድርገው ይገነዘቡ እንደ ነበረ፣ ነገር ግን ኢየሱስን “እዚህ እና አሁን እንደሚኖር ሕያው ሰው አድርገው ያውቁት እንዳልነበረ” አክለው ገልጸዋል። በተጨማሪም “በታሪክ እና በሥነ-መለኮት ጥናቶቼ ወደ እሱ ስቀርብ ቢያንስ እኔ በዚያ መንገድ አላውቀውም ነበር። ስለ ክርስቶስ ማንነት የነበረኝ ግንዛቤ እንዲያው በሩቁ ነው እንጂ በግለሰብ ደረጃ በነበረኝ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ እውቀት አልነበረኝም ነበር። የጎደለኝ ነገር ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ከኢየሱስ ማንነት ጋር የተገናኘው የቅዱስ ጳውሎስ ተሞክሮ ነው” ማለታቸው ተገልጿል።
ፍቅር ከሆነው እግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት መፍጠር
ፍቅር ከሆነው እግዚአብሔር ጋር የግል ግንኙነት መፍጠርን በተመለከተ ደግሞ ካርዲናል ካንታላሜሳ ሲናገሩ በቅድስት ሥላሴ ውስጥ ስላለው 'አካል' አስተሳሰብ ሲናገሩ እግዚአብሔር ማለት ግንኙነት ማለት ነው። ሰው መሆን ‘በግንኙነት ውስጥ መሆን’ ማለት ነው። ይህ ‘ንፁህ ግንኙነት’ ለፈጠሩ ለሦስቱ የቅድስት ሥላሴ አካላት መለኮታዊነት ይሠራል። “ለዚያም ነው አንድ ሰው ከ “እኔ” ወደ “እርሱ” በመሻገር ከእሱ ጋር ወደ የግል ግንኙነት ካልገባ በስተቀር ኢየሱስ እንደ ሰው ሊታወቅ አይችልም የምለው በእዚህ ምክንያት ነው ብለዋል።
የ 86 ዓመቱ የካፑቺን ማሕበር አባል የሆኑት ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ አክለው እንደ ገለጹት “እንደ አለመታደል ሆኖ ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ፣ ኢየሱስ ገጸ ባህሪ እንጂ ሰው አይደለም” ብለዋል። “እሱ ቀኖናዊ መግለጫዎች ፣ ሐይማኖታዊ አስተምህሮዎች እና መናፍቃዊ አስተሳሰብ ሰለባ ነው፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስረዓት ውስጥ በእውነት በቅዱስ ቁርባን ውስጥ አለ ብለን እናምናለን . . . ወዘተ። ሆኖም ፣ ከእሱ ጋር የህልውና ግንኙነት ካላዳበርን በስተቀር እሱ ከእኛ ውጭ ሆኖ ይቀራል ፣ ልባችንን ሳያሞቅ በአእምሯችን ውስጥ ብቻ መቅረት አይኖርበትም” ብለዋል።
ለዚህም ነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላቲን ቋንቋ “Evangelii Gaudium” በአማርኛ በወንጌል የሚገኝ ደስታ በተሰኘው በሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ውስጥ ሁሉም ክርስቲያኖች “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ታደሰ የግል ግንኙነት” እንዲመሰርቱ የጋበዙት በእዚህ ምክንያት እንደ ሆነ የገለጹ ሲሆን እናም በዚህ መልኩ በግል ከክርስቶስ ጋር ግንኙነት ከፈጠርን በኋላ ይህ ህይወትን የሚለውጥ ተሞክሮ የመንፈስ ቅዱስ እርምጃ ነው ብለዋል።
በቅድስት ሥላሴ ላይ ያተኮረው የቤተክርስቲያኗ ቀኖና በቅዱስ ዮሐንስ መግለጫ ላይ የተመሠረተ ነው በማለት አስተንትኖዋቸውን የቀጠሉት ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብለዋል። አጽናፈ ሰማይ እና ሰው ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሔር ከአስር ቢሊዮን ዓመታት በፊት እንኳን ለዘላለም ፍቅር ነበረው። “ከእሱ ውጭ የሚወደድ ነገር ከመኖሩ በፊት ፣ እግዚአብሔር በማያልቅ ፍቅር የወደደው ልጅ ፣ ማለትም‘ በመንፈስ ቅዱስ ’ውስጥ ያለው ቃል በራሱ ውስጥ ነበረው።” “በእግዚአብሔር ውስጥ መብዛቱ ከአንድነት ጋር አይጋጭም ምክንያቱም‘ እግዚአብሔር ፍቅር ነው ’!” ብለዋል።
የሰው ክብር እና መከራዎች
ለሰው ልጅ አክብሮት እና ክብር ያለው ዘመናዊ አስተሳሰብ የሚመነጨው በእርሱ ውስጥ የእግዚአብሔርን መልክ ከሚይዘው ሰው ነው። ሆኖም የዚህ ፅንሰ-ሀሳብ አመጣጥ ፍቅርን በሚገልጸው የቅድስት ሥላሴ ፍሬ ነገር ውስጥ መረዳት ይቻላል። ሌላ ሰው እንዲኖር እና ሌላም እንዲሆን ለማስቻል የራሱን ማንነት ለመሰዋት ፈቃደኛ በሆነ ፍቅር ከሌሎች ጋር በመተባበር ሰው በመሆን ማንነታችንን እናገኛለን። መለኮታዊ ፍቅር በራሳችን ሰብዓዊ ሕልውና ውስጥ ራሱን ሙሉ በሙሉ በሚገልጽበት በክርስቶስ መስቀል ላይ የተገኘበት ትክክለኛ መንገድ ነው። ስለዚህ ክርስቶስ ፣አምላክ ፣ ለእኔ በተናጥል ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ፣ ምስኪን ምስጋና ያልተቸረው አካል መስሎ ይሰማኛል ብለዋል።
ስለሆነም ከክርስቶስ ጋር ‘በግል የምናደርገው ግንኙነት’ በመሠረቱ የፍቅር ግንኙነት ነው። እሱ በክርስቶስ መወደድን እና ክርስቶስን መውደድን ያካትታል። እናም ይህ ግንኙነት በሚኖርበት ጊዜ እንደ መከራ ፣ ጭንቀት ፣ ስደት ፣ ረሃብ ፣ መታረዝ ፣ አደጋ ወይም ጎራዴ ያሉ መከራዎች - በቅዱስ ጳውሎስ እንደተጠቀሰው - ከክርስቶስ ፍቅር አይለዩንም፣ በፍቅር ላይ የተመሠረተ እንደ ውስጣዊ የመፈወስ ዘዴ ፣ የአሕዛብ ሐዋርያ የነበረው ቅዱስ ጳዎሎስ እንደ ገለጸው አሁን በስፋት እንደ ሚታየው የኮቪድ 19 ያሉ ወረርሽኝን ጨምሮ እነዚህን ሁሉ አደጋዎች እና መከራዎች እግዚአብሔር ይወደኛል ከሚለው አስተሳሰብ አንፃር እንድንመለከት ጋብዞናል ፣ ምክንያቱም “እግዚአብሔር ካለ እኛን ማን ይቃወመናል? ካሉ በኋላ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤት ሰባኪ የሆኑት ካርዲናል ራኔሮ ካንታላሜሳ አስተንትኖዋቸውን አጠናቀዋል።