ፈልግ

በስፔን በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ወቅት የተዘጋጁ የንስሐ መግቢያ ቦታዎች በስፔን በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ወቅት የተዘጋጁ የንስሐ መግቢያ ቦታዎች 

አቡነ ፊዚኬላ፥ ንስሐ መግባት፣ ምጽዋትን መስጠት እና ይቅርታን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ አሳሰቡ

ቤተ ክርስቲያናት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንቦችን ባከበረ መልኩ ከመጋቢት ሦስት እስከ መጋቢት አራት 2013 ዓ. ም. ድረስ ለምስጢረ ንስሐ ክፍት ሆነው የሚቆዩ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ምዕመናን የምሕረት ምስጢርን በመቀበል ራሳቸውን ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ታስቦ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው በቅድስት መንበር ለሕዝቦች አዲስ የወንጌል አገልግሎች ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሲሆን ከዚህ በፊትም በየዓመቱ ተመሳሳይ መርሃ ግብርን ሲያዘጋጅ የቆየ ሲሆን የዘንድሮ መሪ ቃል “እርሱ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል” የሚል መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች አዲስ የወንጌል አገልግሎች ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ እንዳስረዱት ዘንድሮ በተደረገው ዝግጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንቦችን በማክበር ጥንቃቄን ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንቦችን ባከበረ መልኩ ከመጋቢት ሦስት እስከ መጋቢት አራት 2013 ዓ. ም. ድረስ ቤተክርስቲያናት ለምስጢረ ንስሐ ክፍት ሆነው የሚቆዩ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በፊት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የሚሳተፉበት የተለመደው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዝግጅት ዘንድሮ የማይኖር መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በየሀገረ ስብከቱ በሚገኙ ቁምስናዎች፣ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እና ማረሚያ ቤቶች አካባቢ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንቦችን በማከበር የሚከናወኑ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።

ለማስተንተን ምቹ አጋጣሚ ነው

ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ እንዳስረዱት፣ ዝግጅቱ በግል ሕይወት ላይ ለማስተንተን ምቹ አጋጣሚን በማዘጋጀት የእግዚአብሔርን ምሕረት ማግኘት የሚቻልበት መሆኑን አስረድተው ለዚህም ከካህን ጋር መገናኘት የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ወቅት ማንነታችንን ለማወቅ ኃይል የምናገኝበት፣ የአቅም ውስንነት እንዳለብን የምናውቅበት እና ኃጢተኞች መሆናችንን ተገንዝበን ራሳችንን በእግዚአብሔር ስም ወደሚናገረን ሰው ፊት ቀርበን መጽናናትን እና የእግዚአብሔርን መለኮታዊ ምሕረትን የምናገኝበት ምስጢር መሆኑን አስረድተዋል። እግዚአብሔር ለእኛ ቅርብ መሆኑን፣ በተለይም በብርሃነ ትንሳኤው ምልክት አማካይነት እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን የሚያሳየንን ተጨባጭ ተስፋ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ምስጢረ ንስሐ እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ

በቅድስት መንበር ለሕዝቦች አዲስ የወንጌል አገልግሎች ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የምስጢረ ንስሐን ጥልቅ ትርጉም ከማወቅ ወደ ኋላ ማለት እንደማያስፈልግ አስረድተው፣ ከሌሎች በርካታ አገሮች ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ጋር በመወያየት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ደንቦችን ባከበረ መልኩ የምስጢረ ንስሐ ሥነ-ሥርዓት የሚፈጸምበትን ምቹ መንገድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል። ከምቹ መንገዶች መካከል አንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚኖሩትን ነጻ ሥፍራዎች ላይ ማኅበራዊ ርቀትን በመጠበቅ በአናዛዥ ካህን እና በተናዛዥ መካከል ሊኖር የሚገባውን ርቀት በመወሰን፣ የምስጢረ ንስሐ ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ መደረግ እንዳለበት አስረድተዋል።

ይቅር ማለት ከባድ ቢሆንም በተግባር መከናወን አለበት

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት መውጣት ለማይችሉ ምዕመናን ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ያሉት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተናገረውን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ ምጽዋትን መስጠት የብዙ ኃጢአቶች ይቅርታን እንደሚያስገኝ አስረድተው፣ በማከልም ምጽዋዕትን መስጠት ብቻ ሳይሆን የበደሉንን ይቅር ማለት ያስፈልጋል ብለዋል። የበደሉንን ይቅር ማለት ራስን ለሌሎች ክፍት እንድናደርግ ያግዛል ብለው፣ ሌሎችን ይቅር ማለት ቀላል እንዳልሆነ ገልጸው ይህን ለማድረግ ሰው እንደመሆናችን ከፍተኛ ድፍረት እና ራስን ለሌሎች አሳልፎ መስጠትን እና ረጅም ጊዜን ይጠይቃል ብለዋል። የእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ ዘወትር ከእኛ ጋር እንዳለ ያስረዱት ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንዲኖር ማድረጋችን ምሕረቱን እንደምናገኝ የምናረጋግጥበት መንገድ ነው ብለው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢራቅ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት እንደተናገሩት ሁሉ የበደሉንን ይቅር ማለት በክርስትና ሕይወት ለመኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። 

15 March 2021, 16:47