ፈልግ

በማሳ ላይ የበቀለ የስንዴ እህል በማሳ ላይ የበቀለ የስንዴ እህል 

ካርዲናል ታርክሰን ሁሉም ሰው በተመጣጣኝ ዋጋ የዕለት ምግቡን ሊያገኝ ይገባል አሉ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በአውታረ መረብ ሴሚናር ላይ ባቀረቡት ንግግር፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ ያባባሰውን ችግር መቀነስ እንዲቻል ዘላቂ እና የማታጠፍ የምግብ ስርዓቶችን ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። ካርዲናል ታርክሰን አያይዘውም ሁሉም ሰው በተመጣጣኝ ዋጋ የዕለት ምግቡን ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለዜጎች የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት፣ የገንዘብ ድጎማን ማድረግ እና ዘላቂነት ያላቸውን ፍትሃዊ የምግብ ስርዓቶችን መገንባት፣ በተለይም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ በሴሚናሩ ወቅት ተገልጿል። የአውታረ መረብ ላይ ሴሚናሩ የተዘጋጀው ስለ ጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚናገር የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ስድስተኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ መሆኑ ታውቋል። በአውታረ መረብ በቀጥታ በተላለፈው ሴሚናር ላይ ንግግር ካደረጉት ከብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኩዱዎ ታርክሰን በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮች መሆናቸው ታውቋል።       

የምግብ ዋስትና የጠፋው በፍትሕ መጓደል ነው

ግንቦት 18/2013 ዓ. ም ጠዋት የተከፈተው ሴሚናር “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሰባት ዓመት የተግባር መርሃ ግብርን፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችን እና የድሆችን ዋይታ ማድመጥ አስፈላጊነትን የሚያሳስብ መሆኑ ታውቋል። ይህን በማስታወስ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ መላውን የዓለማችን ሕዝብን መመገብ እንደሚቻል ገልጸው፣ በዓለማችን ውስጥ ረሃብ እና የጤና መቃወስ እየጨመረ የሄደው በተላላፊ በሽታ መዛመት ብቻ ሳይሆን በምግብ ብክነት እና ፍትሃዊ የምግብ ስርዓቶች ባለመኖራቸው ነው ብለዋል። በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት የቅርብ ጊዜን ሪፖርት ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን፣ በዓለማችን ከ150 ሚሊዮን ሰዎች በላይ የበቂ ምግብ ዋስትና የሌለው መሆኑን አስረድተዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እ. አ. አ በ2020 ዓ. ም ዓለም አቀፍ የምግብ ቀንን ምክንያት በማድርግ ባስተላለፉት መልዕክት “በዓለማችን ውስጥ ረሃብ መከሰቱ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ነው” ማለታቸውን ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን ጠቅሰዋል። 

ለሁሉም ተገቢ የሆነ የምግብ አቅርቦትን ማረጋገጥ

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ሐላፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን በዓለማችን የተከሰተው የምግብ ማነስ፣ ሕዝቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ከሚያደርገው ትግል ጋር የሚያያዝ መሆኑን አስረድተው የምግብ እጥረት ሊከሰት የሚችልበት ሌላው መንገድ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሂደቶች ባለመኖራቸው፣ የአካባቢ ጥበቃ እና እንክብካቤ ማነስ እና በብዝሃ ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ምግብ ለሕይወት

“ምግብ ለሕይወት” በሚል ርዕሥ የአውታረ መረብ ላይ ሴሚናሩን በጋራ ያዘጋጁት የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት፣ በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ በዓለም ምግብ ፕሮግራም የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ክፍል፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት እና በቫቲካን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ ምክር ቤት መሆናቸው ታውቋል። የአውሮፓዊያኑ 2021 ዓ. ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ 2030 ዓ. ም ድረስ ያቀደው የዘላቂ ዕድገት ሃሳቦች የሚቀርብበት ዓመት መሆኑ ታውቋል።

27 May 2021, 16:14