ሥነ-ምህዳርን የሚመለከተ አዲስ የትምህርት ዘርፍ መከፈቱ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበትን የጋራ መኖሪያ ምድራችን ስቃይ በማድመጥ፣ ለአየር ንብረት ለውጥም ተገቢ ምላሽ ለመስጠት የመፍትሄ መንገዶችን መፈለግ የጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲው ዋና ዓላማ መሆኑን ክቡር አባ ኦገስቲን አስታውቀል። በመሆኑም ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 23/2013 ዓ. ም በጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲው ኮርሱን መከታተል ለሚፈልጉት ተማሪዎች የአንድ ቀን የማስተዋወቅ እና የቅድመ ዝግጅት መርሃ ግብር መቅረቡ ታውቋል። በዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው የተቀናጀ ሥነ-ምህዳር ትምህርት ሦስት ዓመት የሚውስድ የፍልስፍና ወይም ሌሎች ሁለት ዓመት የሚወስዱ ትምህርቶችን የሚከታተሉ ተማሪዎች እንደ ባዮሎጂ ፣ ባሕል ፣ ስደተኞች ፣ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት እና ሐዋርያዊ የአካባቢ ጥበቃ ኮርሶችን ጨምሮ እንደ ልዩ ሞያ ትምህርት መውሰድ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል።
የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አቅጣጫን በተመለከተ
“ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለው የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በቂ የአተንትኖ እና የጥናት ጊዜ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ክቡር አባ ኦገስቲን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲያቸው ከዚህ በፊትም በተቀናጀ ሥነ-ምሕዳር ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን እና ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል። ኮርሱን በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለማስገባት እ. አ. አ ከ2015 ዓ. ም ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየ፣ በ“ውዳሴ ላንተ ይሁን” ቃለ ምዕዳን እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ሲደረግባቸው መቆየቱን ክቡር አባ ኦገስቲን አስረድተዋል። በአንቶኒያኑም ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጠው የተቀናጀ ሥነ-ምሕዳር ትምህርት በውስጡ መሠረታዊ የሆኑ ሦስት ፅንሰ-ሀሳቦች ያሉት መሆኑን የገለጹት ክቡር አባ ኦገስቲን እነርሱም ምድራችን ፣ በምድራችን ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት የእርስ በእርስ ግንኙነት እና ሦስተኛው በመኖሪያ አካባቢችን የሚገኙ ሕይወት ያላቸው እና ሕይወት የሌላቸውን ነገሮች የማስተዳደር ሃላፊነት የተጣለበትን መንግሥታዊ ተቋማት የሚሉ መሆኑን አባ ኦገስቲን ገልጸዋል። በተለይ ሦስተኛው እና የመንግሥት ሃላፊነትን የሚመለከተው ፅንሰ-ሀሳብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት አባ ኦገስቲን፣ ያለ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋማት እና ፖለቲካዊ የአቅጣጫ ጥቆማ ሰዎች ብቻቸውን የትም መድረስ እንደማይችሉ ገልጸው የተቀሩት ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችም በጋራ የሚሠሩበት መንገድ ካልተመቻቸ በስተቀር ውጤታማ መሆን አይቻልም ካሉ በኋላ በርካታ ጠቃሚ ሃሳቦች “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ የተገለጸ መሆኑን አስረድተዋል።
የተቋማት ተሳትፎ
በጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲያቸው የሚሰጥ የተቀናጀ ሥነ-ምሕዳር ትምህርት ከሌሎች የተለያዩ ፋካልቲዎች ከእነዚህም መካከል ከፍልስፍና፣ ከሥነ-መለኮት እና ከሕገ ቀኖና ትምህርቶች ጋር ተያያዥነት ያለው መሆኑን አባ ኦገስቲን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የተቀናጀ ሥነ-ምሕዳር ትምህርት ከሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመገናኘት የትምህርት አድማሱን ሰፋ የሚያደርግ፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ጋርም ግንኙነት የሚኖረው መሆኑን አስረድተዋል። በሮም የአንቶኒያኑም ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ዲን የሆኑት ክቡር አባ ኦገስቲን ሄርናንደስ አክለውም በር. ሊ ጳ ፍራንችስኮስ ግብዣ መሠረት የተለያዩ የትምህር ተቋማት ተባብረው የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከውድመት እና ከጥፋት ለማዳን የበኩላቸውን አስተዋጽዓን እንደሚያበረክቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።