ፈልግ

በቫቲካን አስተዳደር የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቫቲካን አስተዳደር የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ 

የቅድስት መንበር ኤኮኖሚ ምክር ቤት በአውሮጳውያኑ 2020 ዓ. ም በጀት ላይ ተወያየ

በብጹዕ ካርዲናል ማርክስ ሰብሳቢነት ሲካሄድ የቆየው የቅድስት መንበር ኤኮኖሚ ምክር ቤት ስብሰባ መጠናቀቁን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። ዓርብ ሐምሌ 9/2013 ዓ. ም ረፋዱ ላይ የተጠናቀቀው የኤኮኖሚ ምክር ቤት ስብሰባ የአውሮፓውያኑን 2020 ዓ. ም መጨረሻ የበጀት መጠን በማጽደቅ መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አክሎ አሰታውቋል። ምክር ቤቱ በተጨማሪም የቅድስት መንበር የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ጉዳዮችንም አንስቶ የተወያየ ሲሆን የሚቀጥለውን የምክር ቤት ስብሰባ በመስከረም ወር 2014 ዓ. ም ለማካሄድ ቀጠሮ መያዙ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ ፣ የኢኮኖሚ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ክቡር አባ ሁዋን አንቶኒዮ ጉዌሬሮ አልቬስ፣ የምክር ቤታቸውን ብቃት እና ዓመታዊ የሥራ ክንውን የሚገልጽ ሪፖርት ማቅረባቸውን አስታውቋል። በወ/ሮ ኤቫ ካስቲሎ የተመራው የውይይት መድረኩ በቅድስት መንበር የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ላይም ውይይት ማድረጉ ታውቋል።

በስብሰባው ላይ የቅድስት መንበር ኤኮኖሚ ምክር ቤት ፕሬዚደት ብጹዕ ካርዲናል ሬይንሃርድ ማርክስ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ብራያን ኤድዊን ፈርሜ መገኘታቸው ታውቋል። ስብሰባውን ከተካፈሉት ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት መካከል ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኤርዶ፣ ብጹዕ ካርዲናል አንድሬስ አርቦሬሊውስ፣ ብጹዕ ካርዲናል ዮሴፍ ዊሊያም ቶቢን እና ብጹዕ ካርዲናል ጁሰፔ ፔትሮኪ የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪ ከአገራቸው ሆነው የምክር ቤቱን ስብሰባ የተካፈሉት፣ በደቡብ አፍሪካ የዴርባን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ዊልፍሪድ ፎክስ ናፒየር፣ ከብራዚል ብጹዕ ካርዲናል ኦዲሎ ሽሬር እና በካናዳ የኪቤክ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጄራልድ ሲፕሪያን ላክሯ መሆናቸው ታውቋል። ከቫቲካን የኤኮኖሚ ምክር ቤት ስብሰባን የተካፈሉት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን እና የቫቲካን ፋይናንስ ቢሮ ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ካሲኒስ ሪጊኒ መሆናቸው ታውቋል።

በመጨረሻም የስብሰባው ተካፋዮች የተገኙበት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሥነ-ሥርዓት የመሩት የቅድስት መንበር ኤኮኖሚ ምክር ቤት ፕሬዚደት ብጹዕ ካርዲናል ሬይንሃርድ ማርክስ ሲሆኑ፣ የሚቀጥለውን የምክር ቤቱ ስብሰባ በመጭው መስከረም ወር 2014 ዓ. ም ለማካሄድ ቀጥሮ መያዙን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። 

17 July 2021, 15:05