ፈልግ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ከአየር ንብረት ለውጥ አዲስ መነሳሳትን እንዲገኝ መጠየቃቸው ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በመወከል በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ውስጥ ዱባይ ከተማ ከኅዳር 20 እስከ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄደውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP28) በመካፈል ላይ የሚገኙት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የአየር ንብረት ለውጥ፥ ጦርነቶች እና መከፋፈል በምድሪቱ ላይ ያስከተለው ቀውስ ቅዱስነታቸውን እንዳሰጋቸው ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዱባይ ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP28) የሚካፈሉ የቅድስት መንበር ልኡካንን የመሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እንደሆኑ ታውቋል። የልዑካን ቡድኑ ወደ ዱባይ የተጓዘው ዓርብ ኅዳር 21/2016 ዓ. ም. ሲሆን፥ ዕለቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደዚያች አገር ለመጓዝ ዕቅድ ያደረጉበት ዕለት ቢሆንም ከሐኪማቸው በተሰጣቸው ምክር መሠረት በታላቅ ቅሬታ መሰረዛቸው ይታወቃል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ መነሳሳት እንደሚያስፈልግ እና  ቆራጥ አቋም ሊኖር እንደሚገባ፣ አዳዲስ የሀገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ፖሊሲዎችን ማርቀቅ እንደሚያስፈልግ፥ የሰው ልጅ ለወገንተኝነት፣ ለጠባብ አመለካከት እና ለራስ ወዳድነት ስሜት እንዳይጋለጥ እንደሚፈልጉ ገልጸው፥ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለአየር ንብረት ለውጥ ሳይንስ በሚጠይቀው የጊዜ ገደብ ቆራጥ፣ ግልጽ እና አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥበት ጥሪ ማቅረባቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ዱባይ መጓዝ ባይችሉም፥ በጉባኤው ላይ ለመገኘት ከፍተኛ ምኞት ያላቸው መሆኑን፥ “እግዚአብሐርን አመስግኑ” የሚለውን ሁለተኛውን ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንዳስታወቁት ገልጸው፥ ከስምንት ዓመት በፊት ይፋ ባደረጉት “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚለው የመጀመሪያው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው አማካይነትም በጋራ መኖሪያ ምድራችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይ የሚጋሩት እና ከልብ የሚጨነቁት በሙሉ እንክብካቤ እንዲያደርጉላት መፈለጋቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

“እግዚአብሐርን አመስግኑ” በሚለው ሁለተኛው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥  ከጊዜ ሂደት ጋር እስካሁን የተሰጡት ምላሾች በቂ እንዳልሆኑ እና የምንኖርበት ምድራችን ወደ መፈራረስ ደረጃ እየተቃረበች እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማስረዳታቸውንም ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

በሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚፈጠረውን የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ አሳሳቢነትን አጉልተው የሚያሳዩት ሳይንሳዊ ጥናቶች ብቻ እንዳልሆኑ የተነገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ውስጥ በፍጥረታት ላይ የሚደርሱትን ከፍተኛ ጉዳቶች ማየት የዕለት ተዕለት ክስተት እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም የሰው ልጅ የሕይወት ጥራት በእጅጉ እንደጎዳው በተለይም ለአየር ንብረት ቀውሱ በጥቂቱም ቢሆን ተጠያቂ የሆነውን ክፍል ለጉዳት ማጋለጡን አስረድተዋል።

“እግዚአብሐርን አመስግኑ” የሚለው ሁለተኛው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት በግልጽ አስቀምጦታል ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ “የሰው ልጅ አንዳንድ ጥቃቅን ፍላጎቶቶቹን አልፎ በሰፊ ማሰብ ከቻለ እና ባለው አቅሙ ላይ እርግጠኛ ከሆነ፥ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ውጤታማ እንደሚሆን እና የኃይል ሽግግርን ለማፋጠን እንደሚያስችል እና በቀጣይነት ክትትል ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ጉባኤው በተጨማሪም የአቅጣጫ ለውጥን ሊያደርግ እንደሚችል፣ ይህም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1992 ዓ. ም. ጀምሮ ሲደረግ የነበረውን ጥረት ውጤታማ እንደሚያደርገው፥ ይህ ካልሆነ ትልቅ ተስፋ አስቆራጭ እና እስካሁን የተገኘውን ማንኛውንም መልካም ነገር አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) ተስፋ፥ ጥረቱን በማበረታታት ግልጽ ምልክቶችን ሊሰጥ እንደሚችል ገልጸው፥ ከቅሪተ አካል ነዳጅ አጠቃቀም ቀስ በቀስ ወደ ታዳሽ ሃይሎች እና ወደ ቁጠባ እንዲሁም ለትምህርታዊ ሥነ-ምህዳር ከፍተኛ ቁርጠኝነት በማድረግ በተለያዩ መንገዶች ሊዳብር ወደሚችል የኃይል ሽግግር መድረስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

“በእርግጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ቅድስት መንበር ብዙ ጊዜ የደገሙትን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ መልካም ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካዊ ዘዴዎች አስፈላጊ ቢሆኑም ነገር ግን በቂ እንዳልሆኑ ገልጸው፥ በአዲስ እና በተቀናጀ የሰው ልጅ ልማት፥ ቀጣይነት ያላቸውን ሞዴል በማስተዋወቅ ላይ የተመሠረተ እንክብካቤ እና ወንድማማችነት፥ በሰዎች መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር፥ በአኗኗር ዘይቤ እና በፍጆታ መጠን ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድር ትምህርታዊ ሂደት መታጀብ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ይህን ሃሳብ በማጠናከር፥ “በእውነት ላይ የተመሠረተ ልግስና” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው እንደተናገሩት፥ በሰዎች እና በአካባቢ መካከል ያለው ጥምረት፥ “ከእርሱ ዘንድ የመጣንበት እና ወደ እርሱ የምንጓዝበት የእግዚአብሔር ፍቅር በተግባር የሚታይ መሆን አለበት” (ቁ. 50) ብለዋል። 

“የአየር ንብረት ቀውስ ውስብስብ፣ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ እና ከሰብዓዊ ክብር ጋር ቅርበት ያለው ነው" ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ከዚህም በላይ የረጅም ጊዜ መዘዝን የሚያስከትል የአረንጓዴ ጋዝ ልቀት ከመጨመር የሰው ልጅ ባህሪ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረድተው፥ በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ከታየው የኢንዱስትሪ አብዮት የተፈጠረ እና ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል። በአየር ንብረት ላይ ጥናት የሚያካሂዱት የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ ጠበብት እንደገለጹት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 1850 ዓ. ም. ጀምሮ ከታየው 42% ጠቅላላው የልቀት መጠን ከፍተኛው ከ 1990 በኋላ የታየ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጨማሪም፥ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ ከ 2015 ዓ. ም. ጀምሮ ተከታታይ ቀውሶች መኖራቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በኅብረተሰባችን ውስጥ ያሉ የማያቋርጡ ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስታወሱ በቂ እንደሆነ ተናግረው፥ ዩክሬን ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነት ጨምሮ አሁን በቅርቡ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የተከሰተው ግጭት፥ እነዚህ ግጭቶች በሙሉ በሲቪሉ ማኅበረሰብ ላይ የሚያደርሱት ጉዳቶች ተቀባይነት የሌላቸው እና አስከፊ ተጽእኖ የከማሳደራቸው በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተፅእኖዎችን እንደሚያሳድሩ የሚያሳዩ ምሳሌዎች እንደሆኑ ተናግረው፥ እነዚህ ቀውሶች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ከአየር ንብረት ለውጥ የመነጠል ስጋት እንዳላቸው አስረድተዋል።

የአየር ንብረት ለውጡ ወደፊት እየገሰገሰ እንደሚገኝ እና የሰው ልጅ መልካም ተግባራትን እንደማይጠብቅ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን ልብ ማለት ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም አንድ ላይ በመሆን እንደሚገባ ሊገነዘብ ይገባል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእንግሊዝ ግላስጎው ከተማ ለተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በላኩት መልዕክት፥ “የአየር ንብረት ለውጡ በሰው ልጆች ላይ ያስከተለውን ቁስል ከዓለም አቀፍ ግጭት ጋር ማነጻጸር ይቻላል” ማለታቸውን ጠቅሰው፥ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት እንደነበረ ሁሉ፥ ዛሬ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለአብሮነት እና ለአርቆ አሳቢነት ተግባራት ቅድሚያን ሊሰጥ ይገባል ብለው፥ እውነተኛው ጠላት ዛሬም ቢሆን ነገ በሁሉም የሰው ልጆች ዘንድ ተጽእኖ የሚፈጥር ሃላፊነት የጎደለው ባህሪ በመሆኑ ምላሹ ፈጣን እና የተቀናጀ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

“በመካሄድ ላይ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28)፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ ያሳዩትን ፍላጎት በተግባር ለማዋል እገዛ ቢያደርግ መልከም ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ከኢንዱስትሪ አብዮት በኋላ ያለው ጊዜ በታሪክ ውስጥ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ተደርጎ ቢወሰድም፥ የሰው ልጅ ተስፋ የሚያደርግበት ምክንያት እንዳለው እና በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ከባድ ኃላፊነቶቹን በልግስና መሸከም እንደሚገባ የሚያስታውስበት እና እንደዚህ ዓይነት ሃላፊነቶችን ለመወጣት የሚያስችል ዘዴ እና አቅም ያለው በመሆኑ ተስፋ አለ ብለዋል።

“የሃማስ ታጣቂዎች እና በሌሎች የፍልስጤም ድርጅቶች ድጋፍ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በእስራኤል ላይ የተጸመው ጥቃት በእስራኤላውያን እና በሁላችንም ላይ ከባድ እና ጥልቅ ጉዳት አድርሶብናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ የዚያ ሕዝብ ደህንነት በእንደዚህ ዓይነት አረመኔያዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችድስኮስ ገና ከጅምሩ እንደተናገሩት፥ “ሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነት በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ላለው ግጭት መፍትሄ ሊሆን አይችልም” ማለታቸው አስታውሰዋል።

አስቀድሞም ቢሆን ደካማ የነበረው የእስራኤል እና የፍልስጤም የሰላም ሂደት አሁን የበለጠ ውስብስብ ሆኗል ብለው፥ በሌላ በኩልም ምናልባት የአሸባሪዎቹ ዓላማ ሁልጊዜም እንደሚገልጹት፥ የሐማስ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር ሰላም ለመፍጠር ፍላጎት እንደሌላቸው፥ በተቃራኒው ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ወደ መጥፋት ጎዳና ለመድረስ ይመኙ ነበር ብለዋል። ይህም የፍልስጤም ግዛት ባለስልጣናት በተለይም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ዘወትር እንደሚያረጋገጡት፥ ከእስራኤል መንግሥት ጋር መነጋገር እንፈልጋለን ከሚሉት ጋር የማይገናኝ መሆኑን ተናግረው፥ ቅድስት መንበር ለብዙ ዓመታት ስታራምደው የቆየችው እና ለኢየሩሳሌም ልዩ ሕግ የሚደነግግ “ሁለት መንግሥታት” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ በእስራኤል በኩል ሙሉ ተቀባይነት እንድትሰጥበት ስትጠይቅ መቆየቷን አስታውሰዋል።  

“በዚህም ሁኔታ ወደ ፊት ቅን የሆኑ የውይይት መንገዶች እንደሚኖሩ ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ምንም እንኳን ይህን ጥረት የሚያግድ ሁኔታ ባይታይም፥ በቫቲካን የአትክልት ሥፍራ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2014 ዓ. ም. የእስራኤሉ ፕሬዝደንት ሺሞን ፔሬዝ፣ የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንንችስኮስ እና ፓትርያርክ በርተሎሜዎስ በኅብረት የተከሉት የወይራ ዛፍ በጸሎት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲያድግ የተስፋ ውሃ ማጠጣትን እንቀጥላለን ብለዋል።

“በአሁኑ ወቅት በፍልስጤም ላይ የሚደርስ የጅምላ ግድያ እንዲያበቃ እና በርካታ እስራኤላውያንን እና ሌሎች ታጋቾችን ለማስፈታት በተደረገው ድርድር ላይ የብርሃን ጭላንጭል መኖሩን አይተናል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ አለመታደል ሆኖ ዛሬ ውጊያው መቀጠሉን ተናግረው፥ ሁሉም ዓይነት ሁከት በተቻለ ፍጥነት እንዲቆም ቅድስት መንበር የምትጠይቅ መሆኗን ተናግረዋል። ግብፅ እና ኳታር ከአሜሪካ መንግሥት ጋር በመሆን ያደረጉት የውይይት ጥረት እና የእስራኤል ታጋቾችን ለማስፈታት ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ የሚመሰገን እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በጋዛ ሰርጥ ያለው ሰብዓዊ ሁኔታ ለቅድስት መንበር ትልቅ ስጋት እንደሆነ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ከ15,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እና ስለ መጥፋታቸው እናወራለን ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ሰዎች ጋዛ ውስጥ አስተማማኝ ሥፍራ ባለማግኘታቸው በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች እና በየአምልኮ ሥፍራዎች መጠለላቸውን አስታውሰው፥ ከትንሿ የፍልስጤም ምድር ዜጎች ወደ ደቡባዊው ክፍል እንዲዛወሩ መገደዳቸውን እና ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ቤት አልባ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦትን በማስተባበር ላይ የምትገኝ የግብፅ ሚና እና የፍልስጤምን ሕዝብ ለመርዳት እየሞከሩ የሚገኙት የዮርዳኖስ፣ የኳታር እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጥረት የሚያስመሰግን እንደሆነ ተናግረው፥ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎችም በጋዛ የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥረት እናበረታታለን ብለው፥ ጦርነቱ እንዲቆም እና ሃማስ እና ሌሎች የፍልስጤም ድርጅቶች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ እና ለእስራኤላውያን ስጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ ሌሎች መንገዶችን መፈለግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀደም ሲል እንደተናገሩት ሁሉ፥ ይህ ግጭት ቅድስት ሀገርን መንካቱ የሁሉንም ሰው ልብ እና ስሜት እንደሚነካ፥ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በእስራኤላውያን ላይ የተፈጸመው ጥቃት ብዙዎችን እንዳስቆጣቸው እና በጋዛ ሕዝብ ላይም እየደረሰ ያለው ስቃይን ጨምሮ በአንዳንድ አገራት ውስጥ ያለው ግጭት የሚያስከትለውን ስቃይ እና በተለይ በብዙ አገሮች የተከሰቱት የፀረ-ሴማዊነት ድርጊቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል።

02 December 2023, 17:58