ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቫቲካን በተካሄደው የጳጳሳት ሲኖዶስ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ በተገኙበት ወቅት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቫቲካን በተካሄደው የጳጳሳት ሲኖዶስ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ በተገኙበት ወቅት 

በ2024 (እ.አ.አ) ለሚካሄደው ሁለተኛ ዙር የሲኖዶስ ጉባኤ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች እና የ16ኛው ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሰብሳቢ ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የሚቀጥለውን ዓመት የሲኖዶሱ የመጨረሻ ጉባኤን በማስመልከት ስለ ሲኖዶሱ ቀጣይ የሂደት ደረጃዎችን በማስረዳት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ብጹዓን ጳጳሳት መልዕክት ጽፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሲኖዶሳዊነት ላይ ውይይት በማካሄድ ላይ የሚገኘው የጳጳሳት ጉባኤ በተቀመጠለት የጊዜ ሠሌዳ መሠረት  እስከ ጥቅምት ወር 2024 (እ.አ.አ) የሚቀጥል ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያናት ዘንድሮ በጥቅምት ወር በተገባደደው የመጀመሪያ ዙር ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ጭብጥ ላይ እንዲያሰላስሉ ተጠይቀዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ከሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተላከላቸውን መመሪያ፥ የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች እና የ16ኛው ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆሌሪች በጋራ ከላኩት መልዕክት ጋር ተቀብለዋል።

ባለ አራት ገጽ መመሪያው፥ በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር በተካሄደው የሲኖዶሱ የመጀመሪያ ዙር ጉባኤ ላይ የተሳተፉት አባላት የነበራቸውን ልምድ አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ ሲሆን፥ የተሳታፊዎቹ ሃሳብ ከተቀበልናቸው ስጦታዎች ውስጥ የማይካዱ እና የማይሻሩ መሆናቸውን በማስታወስ፥ የትኛውም ጽሑፍ ሊጨምረው የማይችል የልምድ ውጤት መሆኑን መመሪያው ገልጿል።

የሲኖዶሱ ሂደት አሁንም የሚቀጥል ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመጀመሪያ ዙር ጉባኤ ጭብጥ ባጸደቁበት ወቅት እንደ ገለጹት፥ “ጉባኤው ስለ ሲኖዶሳዊነት እንጂ በሌላ ርዕሠ ጉዳይ ላይ አይደለም” ማለታቸውን በማስታወስ፥ ዋናው ጥያቄ የጉባኤው ተካፋዮች ያቀረቡትን አስተያየት በሲኖዶሳዊነት መንገድ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንደሆነ መመሪያው አሳስቧል።

መወያየት ያለባቸው ርዕሶች

እስካሁን የወጡትን ጭብጦች በተመለከተ፥ መመሪያው በዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ እና በቅድስት መንበር ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ጋር መተባበር እንደሚገባ ያስረዳል። የቅድሚያ ጥናቱ የላቲን ሥርዓተ አምልኮን፣ የሕገ ቀኖና አንቀጾችን እና የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓቶች ደንቦችን በማዘመን ረገድ፣ የተቀቡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ስልጠና ላይ ያለውን “Fundamentalis” ወይም መሠረታዊ ምክንያቶች እና "Mutuae Relationes" ወይም የጋራ ግንኙነቶች የሚሉ ሠነዶችን፣ በጳጳሳት እና በገዳማውያን/ገዳማውያት መካከል ያለውን የጋራ ግንኙነት እና በተለይም ሴት ምዕመናንን ለድቁና አገልግሎት ማብቃትን በተመለከተ ነገረ-መለኮት እና ሐዋርያዊ ምርምሮችን በጥልቀት እንደሚመለከት ታውቋል።

የጉባኤው ውይይት ርዕሠ ጉዳዮች ዝርዝር ፍሬ ሃሳብ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚቀርብ ሲሆን፥ ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን እና ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች፥ በሲኖዶሱ ጠቃላይ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችንስኮስ ያቀረቡትን የሲኖዶሳዊነት መንገድ የሚያሳይ የሲኖዶሱ የሥራ ሂደት ሪፖርት እንደሚቀር ታውቋል።

በተልዕኮ ውስጥ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንዴት መሆን እንደሚቻል ማሰብ

በሚቀጥለው ወር የሚካሄደው ውይይት፥ በተልዕኮ ውስጥ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንዴት መሆን እንደሚቻል በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ላይ የሚያተኩር ሲሆን፥ ዓላማውም መከተል ያለባቸውን መንገዶች በመለየት፥ እያንዳንዱን ምዕመን እና ቤተ ክርስቲያን ከሞት የተነሣውን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ወንጌሉን ለዓለም የማወጅ ተልዕኮ ልዩ አስተዋጽዖን ለማሳደግ እንደሆነ ታውቋል።

መመሪያው እንደሚያብራራው፣ ሂደቱ የቤተ ክርስቲያንን መዋቅር የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በአምልኮ ሥርዓት ማሻሻያ ዕቅድ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ይልቁንም  በሚስዮናዊነታችን ላይ የሚያተኩር መሆን እንዳለበት፣ በአንድነት እና በልዩነት መካከል ያለውን ተለዋዋጭነት ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለመግለጽ መጠራታችንን ያስረዳል።

በዚህ ረገድ መመሪያው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ኢቫንጀሊ ጓውዲየም” ወይም “የወንጌል ደስታ” የተሰኘውን ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ አንቀጽ 27ን በመጥቀስ፥ ሁሉን ነገር መለወጥ የሚችል ሚስዮናዊ ግፊት፣ የቤተ ክርስቲያን ልማዶች፣ የነገሮች አሠራር፣ ትክክለኛ ጊዜ እና መርሃ ግብሮች፣ ቋንቋዎች እና አወቃቀሮች፣ ቤተ ክርስቲያን ከራሷ ይልቅ ለዛሬው ዓለም ወንጌልን በተገቢው መንገድ ማዳረስ እንደሚገባ የሚያሳስበውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሠነድ ይጠቅሳል።

ሁለት ደረጃዎች

አዲሱ መመሪያው፥ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሲኖዶሱን ጠቅላላ ጭብጥ ዘወትር እንደ ማመሳከሪያ በማቅረብ በሁለት ደረጃዎች መቅረብ እንደሚገባ ይገልጻል። ከአገራት ደረጃ የሚነሱት ጥያቄዎችን በተመለከተ፥ ቤተ ክርስቲያናት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ተልዕኮ ውስጥ የተለያዩ የጋራ ኃላፊነቶችን እንዴት ማሳደግ እንደሚችሉ፣ ከተልዕኮው ጋር የተያያዙ አወቃቀሮችን፣ የማስተዋል እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደትን እና የጋራ ኃላፊነትን እንዴት መቅረጽ እና ማስፋፋት እንደሚቻል፣ ይህን የጋራ ኃላፊነትን በተሻለ መንገድ ለመግለጽ የሚያግዙ አገልግሎቶችን እና አሳታፊ አካላትን አዘጋጅቶ ስለ ማቅረብ ይጠይቃል።

በአገራት በሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት እና በሮማው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው ጥያቄው፥ "በጠቅላላው የቤተ ክርስቲያኗ ስፋት እና በአካባቢያዊ ቤተ ክርስቲያኖች መካከል ያለውን ተለዋዋጭ ሚዛን እንዴት መግለፅ እንደሚቻል ይጠይቃል። ይህን ሁሉ ታሳቢ በማድረግ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ የምክክር ሂደት እንዲያደርግ የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጥሪውን ያቀርባል።

ከባዶ አለመጀመር

መመሪያው እንደሚያብራራው፥  ይህ ሥራ ከባዶው መጀመር እንደሌለበት ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2021-2023 ዓ.ም. የተከናወነውን የማዳመጥ እና የምክክር ሂደት በድጋሚ መመልከት እንደሚገባ ያሳስባል። በዚህ አዲሱ ምዕራፍ፥ በሀገረ ስብከት ደረጃ ከሚገኙ ተሳታፊ አካላት እና ቀደም ሲል ከተቋቋመው የሲኖዶስ ቡድን በተጨማሪ በእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል የተለያዩ ልምዶች፣ ሙያዎች፣ የቸርነት አገልግሎት ልምድ ያላቸው ሰዎችን እና ቡድኖችን ማሳተፍ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። እነዚህ ሰዎች የነገረ-መለኮት እና የሕገ ቀኖና ሊቃውንትን እንዲሁም የትምህርት ተቋማትን የሚያካትቱ መሆን እንደሚገባ ተገልጿል።

እስከ ግንቦት 7/2016 ዓ. ም. ድረስ የሚቀርቡ አስተዋጽዖዎች

አስተያየቶች እና ሃሳቦች ከሀገረ ስብከቶች ከተሰበሰቡ በኋላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች እና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ግንቦት 7/2016 ዓ. ም. ድረስ ለሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ባለ 8 ገጽ የማጠቃለያ ጭብጥ የማዘጋጀት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። የተሰበሰበውን የማጠቃለያ ጭብጥ መሠረት በማድረግ ወደ ሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሚላክ የሥራ ሠነድ ይዘጋጃል።

የሲኖዶሱን የለውጥ ኃይልን ሕያው ማድረግ

የአገራት ቤተ ክርስቲያናትም የጠቅላላ ሪፖርቱን ጭብጥን በሚገባ ተመልክተው የሚገኙበት ሁኔታ መሠረት ያደረጉ ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ ተጋብዘዋል። ይህም መላውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማሳተፍ ተገቢ የሆኑ ውጥኖችን፥ ለምሳሌ የስልጠና ተግባራትን፣ የነገረ መለኮት ጥልቅ ጥናቶችን፣ በሲኖዶሳዊ ዘይቤ በዓላትን ማክበርን፣ መሠረታዊ ምክክሮች፣ በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ በቁጥር ዝቅተኛ ሕዝቦችን እና ቡድኖችን ማዳመጥ እና ሌሎችን ጉዳዮችንም ለመመልከት ያስችላቸዋል

እነዚህን ሥራዎች ማከናወን የሚፈልግ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን፥ በአካባቢው የተከናወኑ ሥራዎችን የሚገልጽ አጭር ምስክርነት፥ ለሚስዮናዊ የሲኖዶሳዊነት ዕድገት ጠቃሚ ናቸው የሚባሉ መልካም ልምዶችን ቢበዛ በሁለት ገጾች አዘጋጅቶ ለአካባቢው ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መላክ እንደሚገባ ሠነዱ ያሳስባል።

ሠነዱ በመጨረሻም፥  የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሂደቱን እንዲከታተሉት፥ የመመሪያውን ጥያቄ በጥልቀት በማጥናት የተቀበሉትን አስተዋፅኦ ማጠቃለያ በማዘጋጀት እስከ ግንቦት 7/2016 ዓ. ም. ድረስ ለሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እንዲልኩ ጠይቋል። ሲኖዶሳዊ እንቅስቃሴው ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል የሚደረገውን ቁርጠኝነት በተመለከተ፥ የቤተ ክርስቲያንን ሲኖዶሳዊ እና ሚሲዮናዊ ገጽታ የሚያራምዱ ውጥኖችን በማበረታታት፣ በሀገረ ስብከቶች የቀረቡትን ምስክርነቶች እና መልካም ተግባራት በማሰባሰብ፥ የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ባስቀመጠው ቀነ ገደብ እንዲልኩ ተጋብዘዋል።

 

 

 

13 December 2023, 14:45