ቤተ ክርስቲያን፥ ሰዎች ከአመጽ እና ከጥላቻ እንዲርቁ እንደምትፈልግ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ፥ በኢየሩሳሌም የቅዱስ መካነ መቃብር ማኅበር መሪ ከሆኑት ከአቶ ቪስኮንቲ ዲ ሞድሮን ጋር ከታኅሳስ 18-24/2016 ዓ. ም. ድረስ በቅድስት አገር መንፈሳዊ ንግደት አድርገዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ከሆኑት ከብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ ጋር ሰኞ ታኅሳስ 22/2016 ዓ. ም. የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ዓመታዊ በዓል ዕለት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ "እግዚአብሔር ለአይሁዶች፣ ለክርስቲያኖች እና ለሙስሊሞች በተገለጠባት ቅድስት አገር ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች በመከባበር አብሮ የመኖርን መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።
የልኡካን ቡድኑ በኢየሩሳሌም የቅዱስ መካነ መቃብር ማኅበር አባላትን በመወከል ከታኅሳስ 18-24/2016 ዓ. ም. ድረስ ወደ ቅድስት አገር ያደረገው የሰላም ጉዞ፥ ማኅበሩ ለቅድስት አገር ያለውን ቅርበት በተጨባጭ ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል። ብፁዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ከል ኡካን ቡድኑ አባላት ጋር በመሆን በኢየሩሳሌም ያደረጉት ቆይታ ከአገሪቱ ቤተ ክርስቲያን ጋር የመተባበር እና የመቀራረብ ምልክትን ለመግለጽ እንደሆነ ታውቋል።
ለኢየሩሳሌም ፓትርያርክ የቀረበ የድጋፍ ምልክት ነው
በኢየሩሳሌም የቅዱስ መካነ መቃብር ማኅበር በኩል የተላከ አንድ መልዕክት እንደገለጸው፥ ልኡካኑ ወደ ቅድስት አገር ያደረግው የሰላም ጉዞ፥ በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ ያላቸውን ተጨባጭ ድጋፍ ለመግለጽ መሆኑን አስታውቋል። የልኡካን ቡድኑ ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን በተከበረበት ታኅሳስ 22/2016 ዓ. ም. በጦርነት ስቃይ ውስጥ በምትገኝ ቅድስት አገር ሰላም እንዲሰፍን ጸልየዋል።
ከብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ ጋር የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት
ብፁዕ ካርዲናል ፌርናዶ ፊሎኒ፥ ሰኞ ታኀሳስ 22/2016 ዓ. ም. ተከብሮ በዋለው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ዓመታዊ በዓል ቀን በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ በብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የመሩትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተካፍለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፌርናዶ ፊሎኒ በመስዋዕተ ቅዳሴው ወቅት ሰላምን በማስመልከት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ሰላም መሠረታዊ የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ አስገንዝበው፥ በመሆኑም ሁሉም ሰው ሰላምን በድፍረት እንዲፈልግ እና እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል። “እራሳችንን ለአመጽ አሳልፈን መስጠት አንችልም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፌርናዶ ፊሎኒ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ለተገኙት ምዕመናን ባሰሙት ቃለ ምዕዳንም፥ በኢየሩሳሌም የቅዱስ መካነ መቃብር ማኅበር አባላት ከምእመናኑ ጋር ያላቸውን አንድነት እና መቀራረብ በመግለጽ፥ በጸሎትም የሚያሳታሷቸው መሆኑን አረጋግጠዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፌርናዶ ፊሎኒ በማከልም፥ ቅድስት አገር እና በቅድስት አገር የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ባለ አስቸጋሪ ወቅት በእስራኤል ሕዝብ እና በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የደረሰውን ከባድ መከራ መላው ሕዝብ የሚጋራው መሆኑን አስረድተዋል።
የሰላም ጸሎት
ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ የሰላም መሣሪያ መሆን እንደምትፈልግ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፌርናዶ ፊሎኒ በማከልም፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና በዓለም ብጹዓን ጳጳሳት ልባዊ ጸሎት ሰዎች ከጥቃት፣ከአመጽ እና ከጥላቻ በመራቅ አብሮ የመኖርን መንገድ እንዲከተሉ፣ የሰላም እና የመግባባት መሣሪያ እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን የምትጋብዛቸው መሆኗን ተናግረዋል። "እግዚአብሔር ለአይሁዶች፣ ለክርስቲያኖች እና ለሙስሊሞች በተገለጠባት ቅድስት አገር ውስጥ ሕዝቦች እርስ በእርስ በመከባበር አብሮ የመኖርን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ ተናግረው፥ “ጥላቻ የእግዚአብሔር አይደለም” በማለት አስገንዝበዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፌርናዶ ፊሎኒ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያ ላይ፥ “አዲስ የተወለደውን ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስ በእቅፏ በመያዝ እርሷ የተመረጠችበትን ቅድስት አገር ወደ እግዚአብሔር እንድታቀርብ” በማለት ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ጸሎታቸውን አቅርበው፥ ከሴቶች መካከል የተመረጥሽ እናታችን ማርያም ሆይ! በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደች የቅድስት ምድር ሕዝቦች ሰላም ኃላፊነት ያለባቸውን ሰዎች ልብ እና አእምሮ እንድትከፍት አደራ እንላለን” በማለት በቅድስት መንበር ለሕዝቦች የወንጌል አገልግሎች ስርጭት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ፊሎኒ ጸሎታቸውን ደምድመዋል።