ፈልግ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥  

ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ካለፈው የሲኖዶስ ጉባኤ የተገኙ ዋና ዋና ውጤቶችን ገለጹ

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ በፊሊፒንስ በተካሄደው አዲስ የወንጌል አገልግሎት ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ “በተልዕኮ ላይ ያለች ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕሥ በጥቅምት ወር ከተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ የተገኙትን ዋና ዋና ውጤቶችን አስታውሰው፥ በሚቀጥለው ጥቅምት ወር 2017 ዓ. ም. ላይ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር በሮም በተካሄደው 16ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተሰማቸውን ደስታ ከጉባኤው ተካፋዮች ጋር የተጋሩት ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ ከጉባኤው የተገኙ ውጤቶችን ካስታወሱ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ሊካሄድ በታቀደው ጉባኤ ላይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ በፊሊፒን መዲና ማኒላ አዲስ የወንጌል አገልግሎትን በማስመልከት በተካሄደው ጉባኤ ላይ ተገኝተው ለተሳታፊዎቹ ንግግር አድርገዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ግሬች በፊሊፒንስ ስለሚካሄደው ጠቅላላ የሲኖዶስ ሂደት፣ ስለአካባቢያዊ ዝግጅቶች እና ተሞክሮዎች የበለጠ ለማወቅ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፥ በ2017 ዓ. ም. በጥቅምት ወር ሊካሄድ በታቀደው ዓለም አቀፍ የሲኖዶስ ጉባኤ እና በእስያ አኅጉር ስለምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ያላቸውን አመለካከት ገልጸዋል።

በቅድሚያ የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ የስብሰባ አዳራሽ ካህናት እና ምእመናን በጠረጴዛ ዙሪያ የተሰባሰቡበትን የሲኖዶሱን ሂደት አጉልተው አሳይተዋል። ቀጥለውም በሲኖዶሳዊው ሂደት ውስጥ የታየው አዲስ ተሞክሮ በወቅቱ ለተደረጉት መንፈሳዊ ውይይቶች መድረክ እንዲዘጋጅ ማገዙን አስታውሰው፥ በሦስተኛ ደረጃ ምእመናን፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ዲያቆናትን እና ካህናትን ጨምሮ ብጹዓን ጳጳሳት ሙሉ እና እኩል ተሳትፎ እንደነበራቸው አስታውሰዋል። በሌሎች የመደመጥ ልምድ የመገለል ስሜትን እንደሚያሸንፍ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ ሰዎች ጊዜን ሰጥተው ሊያዳምጧቸው ጥረት ማድረጋቸው ርኅራሄን በማጎልበት አብሮነትን የሚገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ግሬች በሲኖዶሳዊ ጉባኤ ጭብጥ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና ሃሳቦችን ጠቅሰው፥ ጭብጡ በየአገራቱ የሚገኙ ቤተ ክርስቲያናት በማኅበረሰባቸው ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር የተሻለ መስተጋብር፣ በምስጢራት ሕይወት እና በወንጌል ተልዕኮ ጥረቶች አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት ሰጥቷል። ፊሊፒንስን ጨምሮ በመላው እስያ አኅጉር የምትገኘው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፥ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ ለወጣቶች አማራጮችን ለማዘጋጀት እና ለዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን አመራርን ለመስጠት በሚያስችል ጥሩ ቦታ ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፥ አብዛኛው የዓለም ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በእስያ አኅጉር እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወር ከተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ የተገኘው ሁለተኛው ውጤት፥ የምድራችንን እና የድሆችን ጩኸት ማዳመጥ አንድ ነው ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥ የጉባኤውን ጭብጥ በመጥቀስ ባደረጉት ንግግር፥ ከድሆች ጋር መቆም እና የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ለመንከባከብ መተባበር አንድነትን እንደሚጠይቅ ገልጸው፥ ለጩኸቱ ምላሽ አለመስጠቱ የሥነ-ምህዳር ቀውስ እና የአየር ንብረት ለውጥ እንደሚያስከትል በተለይም ለሰው ልጅ ህልውና ስጋት እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የፊሊፒንስ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወት ጋብዘው፥ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሁላችንም ግንዛቤን በመጨበጥ ለጋራ መኖሪያ ምድራችን እና ለድሆች ጩኸት ምላሽ መስጠት እንድንችል ህሊናን ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ግሬች በመጨረሻም፥ በጉባኤው ጭብጥ ላይ ትኩረት በማድረግ ባሰሙት ንግግራቸው፥ የጉባኤው ጭብጥ ከወንጌል የሚገኘውን ደስታ በመላበስ፥ በአእምሯችን እና በልባችን ውስጥ የበላይ የሆነውን፥ የምሥራቹን ቃል በመስማት እና በመስበክ የሚገኘውን ደስታ እንዴት ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው፥ በሚቀጥለው ዓመት በጥቅምት ወር 2017 ዓ. ም. ስለሚካሄደው ሁለተኛው ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት እንደተገሩት፥ የወንጌል ተልዕኮ የጋራ ኃላፊነት የዕለት ተዕለት ገጠመኝ በሆነበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መኖር ምን እንደሚመስል የምንረዳበት እና ልምዳችንን የምናጠናክርበት ጊዜ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ እና አገልግሎት ሁሉንም ምእመናን ባሳተፈ መልኩ፣ ሲኖዶሳዊ እንቅስቃሴን በቤተ ክርስቲያን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ በማካተት፣ በየአገራቱ በምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያለው ሲኖዶሳዊነት እኛ በምንረዳበት እና በምንኖርበት ሕይወት ውስጥ የበለጠ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በማለት የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

22 January 2024, 15:55