ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ  (ANSA)

ካርዲናል ካንታላሜሳ፥ በቃሉ እና በቅዱስ ስጋው መካከል ወደሚገኘው አንድነት መመለስ ይኖርብናል አሉ

በቅድስት መንበር ውስጥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና የቅርብ ተባባሪዎቻቸው መንፈሳዊ ስብከቶችን የሚያሰሙት ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፥ የላቲን ሥርዓት በምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ የተጀመረውን የዐብይ ጾም ወቅት በማስመልከት ያዘጋጁትን የመጀመሪያ ዙር ስብከታቸውን አሰምተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዮሐ. 6:35 ላይ "እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፤ በእኔ የሚያምን በፍጹም አይጠማም።” ተብሎ በተጻፈው በኢየሱስ ክርስቶስ ንግግር ላይ በማስተንተን የዘንድሮው የዐብይ ጾም ስብከታቸውን አቅርበዋል።   

የፍራንችስካውያን ካፑቺን ወንድሞች ማኅበር አባል የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ ለቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች የሚያሰሙትን የዐብይ ጾም ስብከት፥ በጸሎት እና በሱባኤ ላይ ይገኙ ስለ ነበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሊካፈሉት አልቻሉም። 

ቃል እና ቅዱስ ምስጢራት

"የሕይወት እንጀራን ከወዴት ልናገኝ እንችላለን?” በማለት የጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፥ የሕይወት እንጀራ የሚገኝባቸውን ሁለት ቦታዎች በመለየት እነርሱም ቅዱስ ቁርባን እና ቅዱስ መጽሐፍ እንደሆኑ አስረድተዋል።

በጥንት ዘመን ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቁርባን እና በቅዱስ ቃል ውስጥ እንደሚገኝ መረዳቷን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ፥ ቆይቶም የምዕራቡ ዓለም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለቅዱስ ቁርባን የምትሰጠው ትርጓሜ በክርስቲያኖች መካከል መከፋፈልን ቢያስከትልም ነገር ግን ሉተር በምላሹ “የሕይወት እንጀራ የእግዚአብሔር ቃል ነው” ማለቱን አስታውሰዋል።

ስለዚህ የሚያስፈልገን “በቅዱስ ቃል እና በቅዱስ ስጋው መካከል ወዳለው ወደ መጀመሪያው የአንድነት መንገድ መመለስ ይኖርብናል” ብለዋል። “ይህም ከቅርብ አሥርት ዓመታት ወዲህ ወደ ተስፋፋው የክርስቲያኖች አንድነት ወይም ‘ኢኩሜኒካል’ ወደሚባለው የክርስቲያኖች የአንድነት መንገድ ሊመራን ይችላል” ብለዋል።

ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱሳት ምስጢራት አንዳንድ ጊዜ በሥነ-መለኮት ዕይታ በተቃራኒነት ቢታዩም፥ በሥርዓተ አምልኮ ውስጥ ዘወትር ተስማምተው እንደሚኖሩ አስታውቀዋል። ከመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያን ዓመታት ጀምሮ መስዋዕተ ቅዳሴ ሁለቱንም ማለትም ቅዱስ ቃልን እና ቅዱስ ቁርባንን አካትቶ የያዘ መሆኑን ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ አስታውሰዋል።

የስንዴ እህል

ነገር ግን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን አንድ ጥያቄ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ እንዴት የሕይወት እንጀራ ሆኖ ቀረበ?” የሚል መሆን አለበት ብለዋል። መልሱም፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዮሐ. 12:24 ላይ እንደተጻፈው፥ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” የሚል እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ ተናግረዋል።

ስለዚህም የሕይወት እንጀራን መቀበል ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፥ ነገር ግን በእርሱ እንድንለወጥ መፍቀድ እንዳለብን፥ ይህም መከራን መቀበል እንደሚገባ፥ መከራን መቀበል የቅድስና መንገድ እንጂ ልብን ማደንደን፣ ጥላቻን እና ቅሬታን ማስፋፋት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

መከራን መቀበል

ብፁዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ ስብከታቸውን በመቀጠል፥ ይህንን አመለካከት በተግባር ልናሳይ የምንመራባቸውን ሁለት ተጨባጭ መንገዶችን አቅርበዋል። “የመጀመሪያው ራሳችንን ዘወትር ትክክለኞች ከማድረግ ይልቅ የሌሎችን ወቀሳ ለመቀበል ፈቃደኞች መሆን እንደሚገባ ተናግረው፥ ይህን ስናደርግ ራስ ወዳድነታችን እና ኩራታችን ይቀንሳል” ብለዋል።

መከራን መቀበል ወደ አንድነት መንገድ ስለሚመራ አስፈላጊ እንደሆነ ብጹዕ ካርዲናል ካንታላሜሳ ገልጸው፥ ቅዱስ አጎስጢኖስ “ስንዴ ወደ እንጀራነት ከመቀየሩ በፊት መበጠር፣ መወቃት እና መጋገር ይኖርበታል” ሲል የተናገረውን በመጥቀስ፥ ክርስቲያኖችም ከመዋሄዳቸው አስቀድመው በጾም እና በንስሐ ራሳቸውን መለወጥ እንዲሁም ለመንፈስ ቅዱስ እሳት መጋለጥ አለባቸው ብለዋል።

24 February 2024, 16:18