ፈልግ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ  

ትምህርት፣ ሥራ እና ቤተሰብን መደገፍ ድህነትን በማጥፋት ረገድ ቁልፍ ሚናን እንደሚጫወቱ ተገለጸ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ የመንግሥታቱ ድርጅት 62ኛ የማኅበራዊ ልማት ኮሚሽን ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የትምህርት ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድልንም ማመቻቸት እና የቤተሰብን ደኅንነት መጠበቅ ድህነትን ለማጥፋት ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጠንካራ የማኅበራዊ ጥበቃ ሥርዓቶች ቤተሰብን ከመደገፍ ጋር የትምህርት እና የሥራ ዕድልን ማመቻቸት፣ ድህነትን ለመዋጋት እና የሰው ልጅ ዕድገትን ለማምጣት ወሳኝ መሆናቸውን ኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈር ቤት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ ይህን የተናገሩት፥ ድህነትን እስከ 2030 (እ.አ.አ) ድረስ ማጥፋት የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጀንዳን ተግባራዊ ለማድረግ በማኅበራዊ ፖሊሲዎች ላይ በተወያየው 62ኛ የማኅበራዊ ልማት ኮሚሽን ስብሰባ ላይ እንደሆነ ታውቋል።

የትምህርት ዕድል ለሁሉም ማረጋገጥ

ድህነትን ማጥፋት የሚቻለው መሠረታዊ ምክንያቶቹን በመለየት እንደሆነ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል፥ ትምህርት ለሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት ዋና አጋዥ በመሆን ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ገልጸው፥ ወደ ከፍተኛ ዕድሎች በመምራት ለሁሉም የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።

ስለዚህም ለድሃ ቤተሰቦች የትምህርት ተደራሽነት ለማረጋገጥ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ ከድሃ ቤተሰብ የሚወለዱትን ጨምሮ ሕጻናት በተፈጥሮ ባገኙት ክብራቸው መሠረት አቅማቸውን ሙሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ከሥራ ገበታ የተገለሉትን ጨምሮ ጎልማሶች ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ትክክለኛ ሥራ እና ፍትሃዊ ክፍያ ማግኘት

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል በማከልም፥ ለዕድገት አስፈላጊ የሆነውን ሌላ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ጠቅሰው፥ በሥራ ቦታ እና በምጣኔ ሃብት ዙሪያ ፍትህን በሚያበረታቱ የሠራተኛ ፖሊሲዎች አስፈላጊነት ላይ በማሰላሰል ሥራ የሰዎች መገለጫ እንጂ የተፈጠሩበት ምክንያት ፍጻሜ አለመሆኑን አስረድተዋል።

"ሥራ ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለበት፤ ተገቢ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ የሚከናወን እና ሠራተኞች የቤተሰቦቻቸውን ሕይወትን ከአደጋ ለመጠበቅ እና እንዲዝናኑ በሚያስችል ደረጃ የሚከፈል መሆን አለበት" ብለዋል።

ቤተሰብ ጥበቃ እና ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ በመጨረሻም፥ ቤተሰብ በማኅበራዊ ልማት ውስጥ ወሳኝ ተዋናይ በመሆኑ ከኅብረተሰቡ እና ከመንግሥት ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲደረግለት እና የሚገባው ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል። በዚህ ረገድ ቅድስት መንበር ቤተሰብ በዓለም አቀፍ ውይይቶች ላይ ያለው እውቅና እየቀነሰ መምጣቱ እንዳሳሰባት ደግመው ሲናገሩ፥ “ቤተሰብ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ እየተመናመነ አልፎ ተርፎም እየተናቀ ነው” ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።

ቤተሰብ በዓለም ዙሪያ ለብዙዎች የመጀመሪያው ብቻ ሳይሆን ብቸኛው የማኅበራዊ ደኅንነት ዋስትና እንደሆነ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሱ፥ መሠረታዊ የሆነው ቤተሰብ በኅብረተሰብ ውስጥ ማኅበራዊ ፍትህን እና ዕድገትን በማሳካት ወሳኝ ሚና የሚጫወት በመሆኑ በማኅበራዊ ፖሊሲዎች ሊደገፍ ይገባል ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ቤተሰብ ጥልቅ ሰብዓዊ ትምህርት ቤት፣ የፍቅር እና የወንድማማችነት፣ የመተሳሰብ እና የመጋራት፣ የእንክብካቤ እና ሌሎች እሴቶችም በተጨባጭ የሚታዩበት እና የሚተላለፉበት የመጀመሪያ ቦታ ነው” በማለት ማስረዳታቸውን፥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ካቻ አስታውሰዋል።

 

15 February 2024, 17:07