ፈልግ

ሱዳናዊት እህት ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ ሱዳናዊት እህት ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ 

ወጣቶች ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም ያላቸውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ላይ ናቸው

ቤተ ክርስቲያን አሥረኛውን ዓለም አቀፍ የጸሎት እና የጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ግንዛቤን ማስጨበጫ ቀንን ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ. ም. እንደምታከብር ታውቋል። ዕለቱን ለማክበር ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ 50 የሚሆኑ ወጣቶች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሰጠውን ልዩ ስልጠና በሮም በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ. ም. ለአሥረኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የጸሎት እና የጸረ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የወንጀሉ ሰለባ የሆነችው ሱዳናዊት እህት የቅድስት ጆሴፊን ባኪታ ዓመታዊ ክብረ በዓል ያወጁበት እና ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ከአደጋው ለመታደግ ያላትን ቁርጠኝነት የገለጸችበት ዓለም አቀፍ ምልክት እንደሆነ ይታወቃል።

በዓሉ በሚከበርበት ሐሙስ ጥር 30/2016 ዓ. ም. በብዙ በሚቆጠሩ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች፣ ማኅበረሰቦች እና ማኅበራት ዘንድ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “ከቦታ ቦታ በክብር መጓዝ፣ አንዱ ሌላውን ማዳመጥ እና ማለም” በሚሉ ርዕሦች ዙሪያ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉዳይ ላይ ለማሰላልሰል፣ ለመጸለይ እና የተሳትፎ ልምዳቸውን ለማካፈል እንደሚሰበሰቡ ታውቋል።

በዚህ ዓለም አቀፍ ርዕሠ ጉዳይ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ውይይት ከሚያካሂዱት ግለሰቦች መካከል ከጥር 24-30/2016 ዓ. ም. ድረስ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በማስመልከት የተዘጋጀውን ስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብርን በአምስቱ አህጉራት ከሚገኙ አጋር ድርጅቶች የተወጣጡ 50 የሚሆኑ ወጣት ተማሪዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ተመራማሪዎች፣ የብዙሃን መገናኛ ባለሞያዎች እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በሮም በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሁድ ጥር 26/2016 ዓ. ም. ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን መካከል ከአምስቱም አህጉራት የተወጣጡ ወደ 50 ለሚጠጉ አባላት አቀባበል አድርገውላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስስ በቪዲዮ ቅንብር አማካይነት የበዓሉን ቀን ልዩ ትርጉም በማብራራት በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ቆራጥ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

 

06 February 2024, 16:20