ፈልግ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን  

ካርዲናል ፓሮሊን፥ እኛ እርስ በርስ የሚደጋገፍ የሰው ልጆች ስብስብ ነን ማለታቸው ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በጣሊያን ፓዶቫ ከተማ “ሲኒማ ለፍጥረት” በሚል ርዕሥ በመካሄድ ላይ ለሚገኘው ሦስተኛ ዙር ፌስቲቫል የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል። የፌስቲቫሉ መሪ ሃሳብ፥ “ዓለምን የሚያድኑ ኃይሎች ውበትን እና ፍቅርን የተመገቡ ናቸው” የሚል እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በፓዶቫ ከተማ በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ማዕከል በተዘጋጀው የፊልም ፌስቲቫል ላይ ለተገኙት አባላት ዓርብ መጋቢት 13/2016 ዓ. ም. የቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል። “ሲኒማ ለፍጥረት” በሚል ርዕሥ ከየካቲት 1/2016 ዓ. ም. ጀምሮ ሲካሄድ በሰነበተው የፊልም ፌስቲቫል ላይ “የቅዱስ ፍራንችስኮስን ግርምት አንድ ላይ በመሆን ብቻ” በሚል ርዕሥ በጓልቲየሮ ፒርስ መሪነት የተሠራ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ መቅረቡ ታውቋል።

ሁሉም ነገር እርስ በርስ የሚደጋገፍ ነው

ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን በመልዕክታቸው፥ “ሲኒማ ለፍጥረት” የሚለው የፌስቲቫሉ ርዕሥ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ እና በተለይም “ዓለምን የሚያድኑ ኃይሎች ውበትን እና ፍቅርን የተመገቡ ናቸው” የሚለው የፌስቲቫሉ መሪ ሃሳብ ዋጋ ያለው እንደሆነ ገልጸው፥ “ግጭቶች፣ ራስ ወዳድነት፣ ግዴለሽነት እና አለመደማመጥ በሚታይበት ዓለማችን ውስጥ የመተባበር ተግባር የበለጠ አስፈላጊ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሁሉም ነገር እርስ በራሱ የተደጋገፈ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው በፌስቲቫሉ ላይ ለተገኙት ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ይህም አንድ የሆነው እና እርስ በርስ የሚደጋገፍ የሰው ልጆች አካል መሆናችንን ቀስ በቀስ እንድንገነዘብ ያደርገናል” ብለዋል።

የጋራ መኖሪያ ምድራችን ከአካባቢነት በላይ ናት

“የጋራ መኖሪያ ምድራችን ከአካባቢ በላይ ናት” የሚለው እሳቤ “በዓለም አቀፍ ፖሊሲዎች ላይም ሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ የምግባር ለውጥን እንድናመጣ ይጠይቃል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፥ ይህም “የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ጥንቃቄ የተሞላበት እንክብካቤ በማድረግ ላይ ያተኮሩ መሆን አለባቸው” ብለዋል። ለጋራ መኖሪያ ምድራችን የሚደረግ እንክብካቤ ለአካባቢ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻችን እና ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ይጨምራል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ሃላፊነት ያለበትን የባህሪ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ጠቅላላ ሥነ-ምህዳርን በመቀየር ብቻ እንደሆነ ገልጸው፥ ወደ ሕማማት ሳምንት ስንቃረብ የለውጥ ጉዟችን ተነሳሽነት ማዕከል በሆኑት ሁለት መሪ ሃሳቦች እነርሱም በውበት እና በፍቅር የታገዙ መሆን አለበት ብለዋል።

ትስስርን የሚፈጥር እና አንድ ሰው ከራሱ እንዲወጣ የሚያደርግ ፍቅር እንደሆነ ገልጸው፥ በማከልም፥ “ከዚያም በዙሪያችን ያለውን ውበት በመገንዘብ እና በሰዎች እና በአካባቢ መካከል ያለውን ቃል ኪዳን በማጠናከር አስደናቂ ፍጥረታትን እና ለእንክብካቤአቸው እና ዕድገታቸው ትኩረት መስጠትን መቀጠል አስፈላጊ ነው” ስሉ አስገንዝበዋል።

የፍጥረትን ውበት ማውቅ ምስጋናን እንድናቀርብለት ያግዘናል ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፔትሮ ፓሮሊን፥ ለፍጥረት የምናቀርበው የምስጋና ስጦታ ከእኛ በኋላ ለሚመጡት እንድናስተላልፍ ያሳስበናል ብለዋል። “ምስጋናን ማቅረብ በአሁኑ ጊዜ በኅብረተሰባችን ውስጥ ጎልቶ ከሚታየው የብክነት ባሕል ወጥተን ወደ እንክብካቤ ባሕል እና ሁሉን አቀፍ የሥነ-ምህዳር ለውጥ እንድንሸጋገር ይረዳናል” ሲሉም አክለዋል።

የተቀናጀ የሥነ-ምህዳር ባሕል አስፈላጊ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሙሉ የሚያሰኝ ሥነ-ምህዳራዊ ለውጥ ልዩ የአስተሳሰብ እና የማየት መንገድን እንደሚጠይቅ መናገራቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውሰዋል።

አንድ ሰው ብቻውን የለውጥ እርምጃ መውሰዱ በቂ እንዳልሆነ፥ ነገር ግን በርካታ ግለሰቦች በጋራ በመለወጥ በአገር ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመወያየት በተግባር እውነተኛ ሰብዓዊ፣ ሁለንተናዊ እና ቀጣይነት ያለው ልማትን፣ በአዲስ እይታ የውበት እና የፍቅር ቀስቃሽ ኃይል ለመገምገም የሚያስችል የሥነ-ምህዳር ትምህርትን የሚያበረታታ መሆን አለበት ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ለፌስቲቫሉ አዘጋጆች ምስጋናቸውን አቅርበው፥ በወሳኝ ሥነ-ምህዳራዊ የለውጥ ጎዳና ላይ በደስታ መጓዝን እንዲቀጥሉ በማበረታታት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

26 March 2024, 15:43