ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በአማን በሚገኝ የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲመሩ  ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በአማን በሚገኝ የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ሲመሩ  

በጋዛ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታ አስከፊ እና ተቀባይነት የሌለው መሆኑ ተገለጸ

በዮርዳኖስ የአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በጋዛ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ሁኔታ አስከፊ እንደሆነ ገለጹ። በዮርዳኖስ እና በቅድስት መንበር መካከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት መታሰቢያን ለማክበር በሥፍራው የሚገኙት በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ባሰሙት ንግግር፥ ቅድስት መንበር “ሲቪሎችን ከጦርነት አደጋ መጠበቅ የግድ ነው” የሚለውን የሰብዓዊነት መርህን የምትከተል መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጋዛን ሕዝብ በጸሎታቸው ዘወትር እንደሚያስታውሱት እና ከናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ምዕመናን ጋር እንደሚገናኙ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ገልጸው፥ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በጋዛ እና አከባቢው አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርግ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። በዮርዳኖስ እና በቅድስት መንበር መካከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተመሠረተበትን 30ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘት ከመጋቢት 2-5/2016 ዓ. ም. በመካከለኛው ምሥራቅ አገር ዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ ዋና ጽሕፈት ቤቱ አማን ውስጥ ለሚገኝ የሐሼማይት ዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት ሠራተኞች ንግግር አድርገዋል።


ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ የዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅቱ ፕሬዝደንት ለአቶ ሁሴን ቺብሊ ሰላምታ ሲሰጡ ባሰሙት ንግግር፥ ንጉሥ አብዱላህ ዳግማዊ እና ሁሉም የዮርዳኖስ ሕዝብ በጋዛ ሰርጥ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ፍልስጤማውያን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ያሳዩትን ልግስና እና ርህራሄን ጠቅሰው፥ ተቀባይነት በሌለው እና አስከፊ በሆነው ጦርነት ለሚሰቃይ የጋዛ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታን ለመሰብሰብ፣ ለማዘጋጀት እና በአየር ለማጓጓዝ የተሠራው ሥራ ታላቅ ዋጋ ያለው ክርስቲያናዊ ተግባር እንደሆነም ተናግረዋል። “ቅድስት መንበር፥ አሳዛኝ እና አስከፊ ጦርነት በተከሰተ ቁጥር በሁሉም ሕዝቦች ልብ ውስጥ የተቀረጸው እና ‘ሲቪሎችን ከጦርነት አደጋ መጠበቅ ይገባል’ የሚለው ግዴታ ከመናገር ወደኋላ አትልም” ብለዋል።

“የእያንዳንዱ ሰው ክብር፣ የሕክምና ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች እና የአምልኮ ቦታዎች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ መሠረት የደኅንነት ዋስትናቸው የተረጋገጠ ቢሆንም በወታደራዊ ተልዕኮ ስም በተፋላሚ ወገኖች ዘንድ ብዙ ጊዜ እንደሚጣስ ጠቁመው፥ ይህ ከባድ የሰው ሕይወት እና የንብረት ጥፋት በእነዚህ ስልቶች ፈጽሞ ሊጣረስ አይገባም ሲሉ አስገንዝበዋል። ስለዚህም ጉዳት ለደረሰበት ሰላማዊ ሕዝብ የሚውል ሰብዓዊ ዕርዳታ ሳይደናቀፍ በፍጥነት ሊደርስላቸው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በዮርዳኖስ የምትገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የዕርዳታ አገልግሎቷን የምታበረክተው በአካባቢው በሚገኝ “ካሪታስ” በተሰኘ የዕርዳታ ድርጅቷ አማካይነት እንደሆነ አስታውሰው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዮርዳኖስ በሚገኝ የቅድስት መንበር እንደራሴ ጽሕፈት ቤት በኩል 50,000 ዩሮ ለመላክ መመደባቸውን ገልጸዋል። የጦርነቱ ተጎጂዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው በድጋሚ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ “ጋዛ ውስጥ በሚገኝ በናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ውስጥ የተጠለሉ 600 ክርስቲያኖችን፣ የካቶሊክ እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስደተኞችን ልናስታውሳቸው ይገባል” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በማከልም፥ እስራኤላውያን ታጋቾች በአስቸኳይ ተፈተው በጉጉት ወደሚጠብቋቸው ቤተሰቦች እና ዘመዶች እንዲመለሱ፣ የፍልስጤም ሲቪል ሕዝብም ደህንነቱ ተጠብቆለት ሰብዓዊ ዕርዳታ ማግኘት እንደሚችል ተስፋ በማድረግ፣ የዕርዳታ ድርጅቱ ላደረገው ታላቅ ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸው፥ በጦርነቱ ሕዝቡ ብዙ ስቃይ ቢደርስበትም ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ አሳስበዋል።

በአማን ከተማ በምትገኝ የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ውስጥ በቅድስት አገር ውስጥ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች እና በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ የተገኙበትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሰኞ መጋቢት 2/2016 ዓ. ም. መርተዋል።“በአንዳንድ አገራት ክርስቲያኖች በቋንቋቸው መጸለይ አይችሉም፤ ቤተ ክርስቲያን መገንባት አይችሉም፤ በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የመሳተፍ ነፃነት የላቸውም” ሲሉ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን ላይ አስምረውበታል።

ኢየሱስም፥ “ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፤ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና” በማለት ማጽናናቱን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ጋላገር አስታወሰው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያው ጴጥሮስን እና ተተኪዎቹን ቤተ ክርስቲያኑን የሚያንጽበት ዓለት አድርጎ መምረጡን እና ለዚህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ተጨባጭ የክርስቲያን አንድነት ምስክር መሆናቸውን አስረድተዋል። በዓለም ዙሪያ ያለች መላዋ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጸሎት በዚህ አንድነት መወለድ እንዳለበት አጥብቀው የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረግ በድጋሚ ተስፋ አድርገዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 2014 ዓ. ም. በዮርዳኖስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ያሰሙትን ቃለ ምዕዳን በማስታወስ፥ መንፈስ ቅዱስ “ከሃሳብ፣ ከቋንቋ፣ ከባህል፣ ከሃይማኖት ልዩነት ባሻገር ከወንድሞቻችን ጋር ለመገናኘት ልባችንን እንዲያዘጋጅ፤ የስሕተቶችን፣ ያለመግባባቶችን እና የውዝግቦችን ቁስሎች በሚፈውስ የምሕረት ዘይቱ እንዲቀባን እና ሰላም ፍለጋ ፈታኝ ቢሆንም፥ ፍሬያማ በሆነ መንገድ አገልግሎትን በሚያቀርቡ ማዕከላት ዘንድ የትህትና እና የየዋህነት ጸጋን እንዲልክልን" በማለት ተማጽነዋል።

 

13 March 2024, 13:29