በቅርብ የተቀቡት ካህናት በእርቅ ላይ የሚሰጥ ስልጠናን በሮም በመካፈል ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በንስሐ እና በይቅርታ ላይ ውይይት በማድረግ አዲስ ለተቀቡ ካኅናት ስልጠናን የሚሰጥ ዓመታዊ ስብሰባ በሮም መጀመሩ ታውቋል። ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ይህን ስብሰባ ያዘጋጀው በቫቲካን ሐዋርያዊ የንስሐ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሲሆን፥ ዓላማውም አዲስ የተቀቡ ካህናት እና የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች በምስጢረ ንስሐ ሥነ-ሥርዓት ላይ አስተንትኖ እንዲያደርጉ እና ጥልቅ ሥልጠናን እንዲያገኙ ዕድል ለመስጠት እንደሆነ ታውቋል።
ባለብዙ የትምህርት ዘርፍ ውይይቶች
በስብሰባው ወቅት ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተውጣጡ ባለሞያዎች ከምኞታዊ ድርጊቶች ጀምሮ እስከ ንስሐ ምስጢር እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ድረስ ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ለተሳታፊዎች ግንዝባቤን ያስጨብጣሉ። የስልጥናው አዘጋጆች በጋዜጣዊ መግለጫቸው፥ “የቤተ ክርስቲያን ማስተዋል እና ምሕረት ላይ የሚቀርቡ ተጨባጭ እና ውስብስብ ጉዳዮችን ለመፍታት ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስታውቀው፥ በእያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ በተሳታፊዎች መካከል ክርክር እንደሚደረግም ገልጸዋል። ስብሰባው በሚገባደድበት ዕለት ማለትም ዓርብ የካቲት 29/2016 ዓ. ም. የስልጠናው ተካፋዮች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር እንደሚገናኙ አስታውቋል።
ዕርቅ ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ እንደ ቅድመ ሁኔታ
ስብሰባውን ሰኞ የካቲት 25/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በንግግር የከፈቱት በቅድስት መንበር የንስሐ አገልግሎት ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ፒያቼንዛ እንደነበሩ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጪው 2025 የሚከበረውን የኢዮቤልዩ ዓመት በዓል በማስታወስ ንግግራቸውን የጀመሩት ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ፒያቼንዛ፥ “ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ትኩረት ሳይሰጠው ቢቀርም ዕርቅ የበዓሉ ዋና ርዕሠ ጉዳይ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፥ መገናኛ ብዙኃኑ ለኢዮቤልዩ በዓል ወደ ሮም እንደሚመጡ በሚጠበቁ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ምዕመናን ላይ ትኩረት ቢያደርግም፥ የንስሐ ሥነ-ሥርዓት ለበዓሉም እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
የይቅርታ ብርሃን በዓለም ላይ ከመብራቱ በፊት በቅድሚያ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ማብራት እንደሚገባ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ፒያቼንዛ አሳስበዋል። “በእርግጥም ያለ እኛ የግል መታደስ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም መታደስ ላይ ተስፋ ማድረግ የማይታሰብ ነው” ሲሉ ጠቁመዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ፒያቼንዛ የንስሐ ምስጢር ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ አስፈላጊ እንደሆነ እና ተሐድሶ በማንኛውም ጊዜ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። “ቤተ ክርስቲያንን መቅረጽ እኛ እንደ ምንፈልገው ሳይሆን፥ ይልቁን ደካማ የሆነው ሰብዓዊ የግንባታ ሂደት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚላክ ምሕረት እንዲወገድ ልንፈቅድ ይገባል” ብለዋል።
በቅድስት መንበር የንስሐ አገልግሎት ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብፁዕ ካርዲናል ማውሮ ፒያቼንዛ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ፥ በነገረ-መለኮት ውስጥ ስለ ሞት፣ ስለ መጨረሻው ፍርድ እና የሰው ልጅ ነፍስ የመጨረሻ እጣ ፈንታን በሚመለከት የንስሐ ምስጢር ላይ በማሰላሰል፥ ንስሐ በምድር ላይ ካለች ቤተ ክርስቲያን ጋር ብቻ ሳይሆን በሰማይ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ጋርም እንድንገናኝ የሚያደርገን እና ከመላው የቤተ ክርስቲያን አካል ጋርም ያስታርቀናል በማለት ለንስሐ ምስጢር አጽንኦትን ሰጥተዋል።