ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፕሮፌሰር ዮአኪም ቮን ብራውንን ሲቀበሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፕሮፌሰር ዮአኪም ቮን ብራውንን ሲቀበሉ 

አገር በቀል የጤና አጠባበቅ ጥበብ የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ እየጠቀመ መሆኑ ተገለጸ

ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይት ያደረጉት ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ዮአኪም ቮን ብራውን፥ አገር በቀል የጤና አጠባበቅ ጥበብ የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ መጥቀሙ ገልጸዋል። በቫቲካን ድጋፍ በአገሬው ቀደምት ተወላጆች እና በአየር ንብረት ላይ በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰር ቮን ብራውን፥ አገር በቀል ጥበብ በጤና አጠባበቅ እና በሳይንስ መስክ የሰውን ልጅ በእጅጉ ማሳደጉን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአገሬው ቀደምት ተወላጆች በሳይንስ በመታገዝ ምድራችንን የሚጎዱ ቀውሶችን ለመቋቋም የሚያስችል የጥበብ ሀብት እንዳላቸው፥ በተለይም በጤና አጠባበቅ መስክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል። የሳይንስ አካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዮአኪም ቮን ብራውን ይህን የተናገሩት በቫቲካን ድጋፍ በአገሬው ቀደምት ተወላጆች እና በአየር ንብረት ላይ በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ ተገኝተው ጉዳዩን በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት ከመጋቢት 5-6/2016 ዓ. ም. ድረስ በቫቲካን የተካሄደውን አውደ ጥናት የተካፈሉትን አባላት ያለፈው ሐሙስ በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ያደረጉላቸው ሲሆን፥ በመልዕክታቸውም አገር በቀል ዕውቀቶች በአየር ንብረት እና በብዝሃ ሕይወት ላይ ለሚደርሱ ችግሮች መፍትሄዎችን በማዘጋጀት ዓለም አቀፍ አደጋዎችን ሊከላከሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

“ቀደምት የአገሬው ተወላጆች፣ ሳይንሳዊ ዕውቀት፣ ተጋላጭነትን እና ችግርን የመቋቋሚያ መፍትሄዎች” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀው አውደ ጥናቱ፥ እነዚህን ጉዳዮች በማስመልከት በቀደምት የአገሬው ተወላጆች እና በሳይንስ ማኅበረሰብ መካከል ባለው የትብብር ዕድሎች ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአውደ ጥናቱ ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር የአየር ንብረት ለውጥን እና የአካባቢ ቀውሶችን ለመቅረፍ አገር በቀል ባለሙያዎችን መንከባከብ እና ለሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ዋጋ መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ብቻ ሳይሆን የብዝሃ-ሕይወት መጥፋትን እና የምግብ እና የጤና ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮችን ለመፍታት በአገር በቀል ዕውቀት እና በሳይንሳዊ ዕውቀት መካከል የበለጠ ትብብር እንዲኖር አደራ ብለዋል።

የአገሬው ተወላጅ መሪዎች እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች እንዴት እንደሚዛመዱ የተጠየቁት ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ሲመልሱ፥ የአገሬው ተወላጆች ዕውቀት ከብዙ ትውልዶች የመነጨ እንደሆነ እና የሰው ልጅ በልምድ እና በሙከራ እንዲሁም ስለ መፍትሄዎች እና ስለ ዕድሎች በማሰብ መማሩን ገልጸው፥ ይህም የሀገር በቀል ዕውቀትን ከሳይንሳዊ ዕውቀት ጋር እንደሚያዛምድ አስረድተዋል።

የሳይንስ ጠበብት በጉጉት፣ በመገረም እና ለሰው ልጅ ችግሮች መፍትሄን ለማፈላለግ መነሳሳታቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን፥ ሁለቱ የሚለያዩት ሳይንስ ከተሞክሮ ይልቅ በሙከራ እና በቴዎሪ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጸው፥ ሁለቱን ማሰባሰብ በብዝሃ-ሕይወት፣ በጤና እና በግብርና ዘርፎች ለመሥራት ሰፊ ዕድሎችን እየሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

የአገሬው ተወላጆች የዓለም አመለካከት ከተፈጥሮ ጋር ቅርበት እንዳለው የገለጹት ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን፥ በተለይም ለተፈጥሮ ባላቸው ክብር ከተለመደው የከተማ ሕይወት የበለጠ በመሆኑ ከነርሱ ጥበባቸው መማር ለሳይንስ ማኅበረሰቦች ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

በጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ ውስጥ በእምነት እና በሳይንስ መካከል ላይ ያለውን ልዩነት አንመለከትም ያሉት ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን፥በአገሬው ነባር ተወላጆች ዘንድም ተመሳሳይ በመሆኑ የጋራ አቋም እንዳላቸው አስረድተዋል። ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን በማከልም፥ ተፈጥሮን የምናስተናግድበትን መንገድ ብቻ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ሁለታችንም የፍጆታ እና የምርት መጠንን በመቀነስ ላይ ማተኮር አለብን ብለዋል።

በዓለም ላይ ያለው የፍጆታ ልማዳችን የአየር ንብረት ለውጥን፣ የብዝሃ-ሕይወት መጥፋትን እና የተፈጥሮ ውድመትን እያስከተለ በመሆኑ ስለዚህ ሳይንስ እና የአገር በቀል ዕውቀት የአኗኗር ዘይቤአችንን፣ የምርት እና የፍጆታ መጠን ችግራችንን መፍታት አለባቸው ብለዋል።

የአገሬው ነባር ተወላጆች በጤናው ዘርፍ ያላቸው ዕውቀት የሰውን ልጅ በእጅጉ እያገዘ እንደሚገኝ የተናገሩት ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን፥ ከምንጠቀማቸው የሕክምና አገልግሎቶች መካከል ሃምሳ ከመቶው ነባር ተወላጆች በተክሎች እና ድብልቅ ነገሮች ላይ ባላቸው ዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ብዙዎች እንደማያቁት ገልጸው፥ ይህም ዋና ዋና በሽታዎችን እንደሚፈውስ አስረድተዋል።

አለመታደል ሆኖ የአገሬው ነባር ተወላጆች ዛሬም እኩል መብት እንደሌላቸው ገልጸው፥ ወጣቶች እና ሴቶች በተለይም የአገሬው ነባር ተወላጆች በመብት እጦት እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። እነዚህን ጉዳዮች የሚፈቱ አዳዲስ የትምህርት ሥርዓቶች ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉ አውቀናል ያሉት ፕሮፌሰር ጆአኪም ቮን ብራውን፥ የአገሬው ነባር ተወላጅ ሕዝቦች ልጆችን እና በአጠቃላይ የዓለም ወጣቶች ጥበብን ከተፈጥሮ እና ከአመለካከት የሚያመነጩ የትምህርት ሥርዓቶች ዘላቂነትን ለመረዳት እና ለመቅረጽ እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዮአኪም ቮን ብራውን በመጨረሻም፥ የአገሬው ነባር ተወላጆች ዕውቀት ከምድር ጋር ብቻ ሳይሆን ሁሉንም አቅጣጫ እንደሚመለከት፥ መስተካከል ያለባቸው ከባድ ስጋቶች እንዳሉ፣ እነርሱም በብርሃን ብክለት የተነሳ ሰማዩን በግልጽ እንዳናይ የሚያግዱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሕዋ ላይ መንኩራኩሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

 

 

 

16 March 2024, 16:32