ፈልግ

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፥  

የኢዮቤልዩ ታሪክ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት

በቅድስት መንበር የባሕል እና የትምህርት ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዚደንት የነበሩት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ጃንፍራንኮ ራቫዚ፥ የቅዱስ ዓመትን አመጣጥ ከብሉይ ኪዳን እስከ ወንጌላት ያሉትን ታሪኮችን በማስደገፍ ከቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ ወቅት አብራርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የ“ኢዮቤልዩ” እውነታን ከአውራ በግ ቀንድ ድምጽ ጋር ማዛመድ የተለመደ ነው። የቀንድ ድምጽ ከኢየሩሳሌም ተነስቶ ወደ መንደሮች ይደርሳል። እንግዲህ በሁሉም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ዮቤል” የሚለው ቃል ሃያ ሰባት ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን ስድስት ጊዜ የአውራ በግ ቀንድ ማለት እንደሆነ እና በተቀሩት ሃያ አንድ ጊዜ የኢዮቤልዩ ዓመትን የሚያስታውስ ስለ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ሌላኛው መሠረታዊው የማመሳከሪያ ክፍል ኦሪት ዘሌዋውያን ምዕ. 25 ነው። ይህ መጽሐፍ የካህናት ወገን ስለ ሆኑ የሌዊ ልጆች እና የሥርዓቶችን ሰፊ ታሪክ የያዘ እንዲሁም የኢየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ሥርዓቶች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የሚገልጽ ነው።

የባሕል ትርጉም ሥነ-ጽሑፍ መቅድም

“ዮቤል” የሚለው ቃል በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕ. 25 ከተጠቀሰው በተጨማሪ በምዕ. 27 ላይም ይገኛል። በጥንታዊው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ “ዮቤል” የሚለውን ቃል “ኢዮቤልዩ” በሚለው ትርጉም ከመተርጎም ይልቅ በሕገ ቀኖና መሠረት ኢዮቤልዩ ዓመት በማለት ተርጉሞታል። በግሪክ ትርጉሙም “ይቅርታ” ፣ “ነጻ መውጣት” ወይም “ምሕረት” ማለት እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ቃል ለኢየሱስ ክርስቶስ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እንደምንመለከተው ስለ ኢዮቤልዩ አልተናገረም። ነገር ግን በጥንታዊው የግሪክ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ በሉቃስ ወንጌል “አፌሲስ” የሚለውን ቃል ይጠቀማል። በእርግጥ በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ “ኢዮቤልዩ” የሚል ቃል አልተጻፈም። ሰባዎቹ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች

እጅግ ከሚያስደንቅ የአምልኮ ሐቅ ወደ ሥነ-ምግባራዊ፣ ሞራላዊ እና ነባራዊ ጽንሰ-ሐሳብ ወደ ሆነው እና የኢዮቤልዩ ይዘት ወዳለው ዕዳን ከመሠረዝ እና ባሪያዎችን ነጻ ከመውጣት ጋር ያገናኙታል። ስለዚህ የኢዮቤልዩ ጭብጥ ከቋንቋ እና ከሥርዓተ-አምልኮ ወደ ማኅበራዊ ሥነ-ምግባር ልምድ ተወስዷል። ይህ ትርጉም ዛሬም ኢዮቤልዩን ወደ በዓልነት ወይም ወደ ሥርዓት ብቻ ለመቀየር ሳይሆን ወደ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሳሌነት ለመቀየር ጠቃሚ ነው። አንዳንድ ሊቃውንት “ዮቤል” የሚለው ቃል ከበጉ ቀንደ የመለከት ድምፅ ጋር ሳይሆን የዕብራይስጥ መሠረት ካለው እና “ዮባል” ከሚለው ቃል ጋር የተገናኘ ነው ብለው ያስባሉ። ትርጉሙም “ማዘግየት፣ መመለስ ወይም መልቀቅ” ማለት ነው።

“መላክ” የሚለው ቃል ትርጉም ነፃነት ሳይሆን ግዳጅ ይመስላል። “አፌሲስ” የሚለው የግሪክ ቃል በተለይም በኢየሱስ ክርስቶስ አጽንዖት በተሰጡባቸው የባሕል ትርጉም የተለያዩ ማብራሪያዎች ተሰጥቶታል። ነገር ግን መነሻው ሥርዓት መሆኑ መታወቅ አለበት። በፊንቄ ቋንቋ አንዳንድ አገላለጾች ታላቅ እህት ወይም ተመሳሳይ የዘር ሐረግ ያለው የሚለውን የዕብራይስጥ ትርጉም ማመልከቱ ትኩረት የሚስብ ነው።

ስለዚህም የቀንደ መለከቱ ድምፅ የተቀደሰ ጊዜ ምልክት የሆነው “ኢዮቤልዩ” ለሚለው ቃል መሠረት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ነገር ግን ወደ ሌላኛው ግንድ ማለትም ወደ ግሪክ ትርጉም ማምራቱ ሊረሳ አይገባም። “ኢዮቤልዩ” ለሚለው ቃል የአምልኮ ሥርዓትን ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች ህልውና ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊኖረው የሚገባው ቃል እንደሆነ እንገነዘባለን። ከዚህ የመግቢያ ትርጉም ቀጥሎ እርስ በርስ የተሳሰሩ የሚመስሉ አንዳንድ መሠረታዊ የ “ኢዮቤልዩ” ጭብጦችን ለማየት እንሞክራለን።

መሬትን ማሳረፍ

እንደ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ጽሑፍ የመጀመሪያው ጭብጥ መሬት “ማሳረፍ” ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት የሰንበት ዕቅድ መሠረት መሬት በየሰባት ዓመቱ እንዲያርፍ ተፈቅዶለታል። በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕ. 25 ላይ እንደተገለጸው፥ በኢዮቤልዩ ዓመት ማለትም በሃምሳኛው ዓመት ሰባት ሳምንታት መሬትም እንዲሁ ማረፍ ነበረበት። ተግባራዊነቱን በተጨባጭ ማሳየት አስቸጋሪ ይመስላል። ነገር ግን እንደ ጥንታዊው የምሥራቅ ሥልጣኔ መሠረት መሬትን ለአንድ ዓመት ማሳረፍ ይቻላል።

ነገር ግን መሬትን ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ማሳረፍ በራሱ የግብርናውን ህልውናውን ወደ ቀውስ ውስጥ የሚያስገባ ነበር። ስለዚህ የኢዮቤልዩ ሰባተኛውን ዓመት ከሰባተኛው ሳምንት ጋር እንዲገጥም ማድረግ ወይም ኢዮቤልዩ ከተጨባጭ አተገባበር ይልቅ ከሁሉም በላይ የተስፋ እና የምልካም ምኞት  ምልክት እንዲሆን ማድረግ ከተለመደው የአኗኗር ዘይቤ በላይ ዕይታ እንዲኖረው ማድረግ ነበር። መሬትን ማሳረፍ ማለት አለመዝራት እና ፍሬውን አለማጨድ ማለት ነው። ይህ ምርጫ በአንድ በኩል መሬት ስጦታ እንደሆነ እና በመጠኑም ቢሆን አንድ ነገር ማምረት እንደምንችል እንድናውቅ ያደርገናል። ምክንያቱም ፍሬው ይነስ እንጂ ምንም አይጎድልም።

በዚህም የተፈጥሮ ዑደቶች በሰው ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ እጅ ላይ መሆናቸውን እንገነዘባለን። በሌላ በኩል በዛሬው ዘመን ለግል ወይም ለአንድ ወገን ብቻ የሚለውን አስተሳሰብ በማሸነፍ ከመሬት ሊገኝ የሚችለው ፍሬ ለሁሉ እንዲዳረስ ለማድረግ ሙከራ ተደርጓል። ይህ በተግባር ሲታይ ሁሉም ነገር ለሁሉም ሰው ለሚለው ለሁለገብነት መድረሻ እውቅናን ሰጥቷል። ይህ ጭብጥ በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ሊኖረው ይችላል። የሰው ልጅ በአንድ ወገን የተጋነነ ሃብት ያከማቸበት፣ በሌላ ወገን የተቀረው ወገን ጥቂት ፍርፋሪ ባለበት ጠረጴዛ ዙሪያ የተሰበሰበበትን ምስል ሊወከል ይችላል። ከዚህ አንፃር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” በማለት ያቀረቡትን ሐዋርያዊ ቃለ መዕዳን ነጸብራቆች መጥቀስ ተገቢ ነው።

ዕዳን መሠረዝ እና መሬትን መመለስ

ሁለተኛው እና ዋናው ጭብጥ ዕዳን ይቅር ማለት እና የተራቆቱ እና የተሸጡ መሬቶችን ለዋናው ባለቤት መመለስ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ራዕይ ምድር የግል ሳትሆን የነገድ እና የጎሳዎች ይዞታ ነበረች። እያንዳንዱም የራሱ የሆነ ክልል ነበረው (መጽ. ኢያሱ 13-21)። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደምናነበው፥ ከከነዓን ድል በኋላ በየጊዜው በተወሰነ መልኩ በእግዚአብሔር ምርጫ እና በተለያዩ ምክንያቶች በታዋቂው የመሬት ክፍፍል ወቅት ጎሳው መሬቱን አጥቷል። በኢዮቤልዩ ዓመት ማለትም በየግማሽ ምዕተ ዓመት የተስፋው ምድር ካርታ እንደገና ይሠራል። እግዚአብሔር እንደሚፈልገው መለኮታዊ ስጦታ የሆነው መሬት በእስራኤል ነገዶች መካከል ይከፋፈላል። ሌሎች ነገዶች ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት በሚሰጥ መዋጮ ከሚኖሩት ከሌዊ ነገድ በስተቀር ሁሉም የየራሳቸውን ድርሻ ይቀበላሉ። ዕዳንም በተመለከተ ተመሳሳይ ነገር ነው።

በኢዮቤልዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሁሉም ሰው በእኩል የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛል። በኋላ ግን አንዳንዶች በስንፍና ወይም ባለመቻል ንብረታቸውን ያጣሉ። ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ሁሉም ሰው ካለው ፍፁም እና ተስማሚ የሃብት ይዞታው ጋር በእኩልነት ደረጃ ላይ መገኘቱን በማረጋገጥ ወደ መጀመሪያው የኑሮ ደረጃ ላይ እንዲመለስ ይወስናል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ንብረቱ፣ መሬቱ እና ልጆቹ ይመለስለታል። በኦሪት ዘዳግም መጽሐፍ በቀረበው ጥሪ ይህ ማኅበራዊ ተሃድሶ በአይሁድ ማኅበረሰብ ዘንድ ሳያቋርጥ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፥ ሁል ጊዜ ሊሳካ የማይችል ዕቅድ መሆኑ ቢታወቅም መከተል ያለበት የማኅበራዊ ሞዴል እንደ ሆነ ይቆጠር ነበር። እንዲህ ተብሎ የተጻፈውን እናነባለን:- “ነገር ግን አምላክ ጌታ ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስት አብዝቶ ስለሚባርክህ በመካከልህ ድኻ አይኖርም። አምላክህ ጌታ በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖርም በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አትጨክንበት ወይም እጅህን አትሰብስብበት (ዘዳ. ምዕ. 15: 4 እና 7)። ለወንድማማችነት እና ለአብሮነት ተስማሚ የሆነ ቁርኝት ብቻ ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ ተጨባጭ ማኅበራዊ ቁርጠኝነትን የሚያመለክት ምርጫ ነው። ቅዱስ ሉቃስ በተለያዩ ጊዜያት በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እንደገለጸው፥ የኢየሩሳሌም ክርስቲያን ማኅበረሰብ የነበረውን መገለጫ እናስታውስ። “ያመኑትም አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሯቸው፤ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው አንድ ነገር እንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም” (ሐዋ. 4:32)።

ከባርነት ነፃ መውጣት

መጽሐፍ ቅዱሳዊ የኢዮቤልዩ መዋቅር ሦስተኛው ጭብጥ በተመሳሳይ መልኩ ቀስቃሽ እና ፈታኝ ነው። የኢዮቤልዩ ዓመት ዕዳ የሚሠረዝበት ብቻ ሳይሆን ባሪያዎችም ነፃ የሚወጡበት ዓመት ነበር። ሕዝ. 46:17 የኢዮቤልዩ ዓመት የነጻነት፣ የመቤዠት፣ ከድህነት ተርፈው ለአገልግሎት የሄዱት ወደ ቤታቸው የተመለሱበት፣ ዕዳቸው የተሠረዘበት፣ ምድራቸውን እና ነፃነታቸውን እንደገና የሚያገኙበት ዓመት እንደሆነ ይናገራል። ሕዝቦች እንደገና ከተሰደዱበት፣ ከባርነት እና ከአድልኦ ካባ ነፃ የሚወጡበት ዓመት ነው። በተጨማሪም ከአሁን በኋላ አንዱ በሌላው ላይ ጉስቁልናን የማያስከትልበት፣ የእግሩ ሰንሰለት የሚፈታበት እና አንድ ሆኖ ወደ አንድ ግብ የሚሄድ ማኅበረሰብን ለመፍጠር የሚታሰብበት ነበር።

አግባብነቱ እንደ ዛሬው ማለቂያ በሌላቸው የባርነት ታሪኮች፣ በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት፣ በዝሙት አዳሪነት፣ ሥራን ሆነ በጾታን ምክንያት በማድረግ ሕፃናትን መበዝበዝ ጨምሮ የብልግና ተግባር የሚካሄድባቸው ሌሎች በርካታ አስነዋሪ ተግባራት መኖራቸው ግልጽ ነው። በተጨማሪም ለኃያላን አገራት ባሪያዎች የመሆን አደጋን ማሰብ እንችላለን። ምክንያቱም የሃያላን አገራት እንቅስቃሴ ብዙውን ጊዜ አንዳንድ ድሃ መንግሥታትን እና ማኅበረሰቦችን በዕዳ በማስጨነቅ እውነተኛ የኢኮኖሚ አምባ ገነንነታቸውን ያሳያሉ። ስለዚህ የኢዮቤልዩ የነጻነት ድምጽ ማስተጋባት በዘመናችን ትልቅ ትርጉም አለው። ይህ ደግሞ ውስጣዊ የነጻነት ጥሪን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። አንድ ሰው ውጪው ነፃ ሆኖ ነገር ግን ውስጡ በተወሰኑ የማይታዩ ሰንሰለቶች ታስሮ ባሪያ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የብዙኃን መገናኛ፣ የታይታ ብቻ፣ የብልግና ተግባር እና የመረጃ ጥገኛ እንደ መሆን ማለት ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ ኢዮቤልዩ

ሉቃስ ወንጌል እንደሚለው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በናዝሬት በምትገኝ መንደሩ ስብከቱን በይፋ በመጀመረበት ወቅት ወደ ምኩራብ ገባ። በዚያም ቅዳሜ ዕለት ከትንቢተ ኢሳያስ መጽሐፍ ተነበበ። የማወጅ እና አስተያየት የመስጠት ተራ እርሱን ደረሰው። በእነዚያ ቃላቶች አማካይነት ለሚቀጥሉት ዘመናት በሙሉ የሚዘልቅ እና ክርስቲያኖች በመንፈስ እና በእውነት የሚያከብሩትን ፍጹም ኢዮቤልዩን ለመክፈት ከአብ ዘንድ እንደተላከ ራሱን አቀረበ፡- “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ስለዚህ እርሱ ቀብቶኛል ለድሆችም ወንጌልን እንድሰብክ፥ ለታሠሩትም ነጻነትን፣ ለዕውሮችም ማየትን፥ የተገፉትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፥ የጌታንም የሞገስ ዓመት እንድሰብክ ላከኝ” (ኢሳ. 61:1)።

ይህ ከብሉይ ኪዳን ሌላ የክርስቲያን ኢዮቤልዩ የተገለጸበት ነው። በኢየሱስ ቃላት የቅዱስ ዓመት አድማስ እና የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ መርሃ ግብር የሆኑትን መከራዎች ሁሉ የሚያሰፋ እና የሚያቅፍ የክርስቲያን ሕይወት ምሳሌ ይሆናል። "የጌታ የጸጋ ዓመት" ማለትም የማዳኑን አራት መሠረታዊ ምልክቶችን ያካትታል። የመጀመሪያው “ለድሆች ወንጌልን ማብሰር” የሚል ነው። የግሪክ ግስ በትክክል ወንጌል የሚለውን ቃል “የምሥራች” ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት “መልካም መልዕክት” ተቀባዮቹም “ድሆች” እንደሆኑ ይገልጻል። ማለትም በምድር ዝቅተኞች የሆኑ፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ኃይል የሌላቸው ነገር ግን በኢየሱስ ለማመን ልባቸው ክፍት ያደረጉ ናቸው። ኢዮቤልዩ ትሁታንን፣ ድሆችን፣ ምስኪኖችን፣ በውጪም በውስጥም በእግዚአብሔር እና በወንድሞቻቸው ላይ ጥገኛ የሆኑትን ነው

ወደ ቤተ ክርስቲያን መሃል ለማምጣት የተዘጋጀ ነው። ነፃነት ሁለተኛው የኢዮቤልዩ ጭብጥ ነው። ይህ ጭብጥ አስቀድሞ በእስራኤላውያን ዘንድ ያየነው ኢዮቤልዩ ነበር። ኢየሱስ እስረኞችን በምሳሌያዊ አነጋገር ጠቅሷል። እዚህ ላይ በታሪኩ መጨረሻ በፍርድ ትዕይንት ላይ የሚደግመውን እነዚህን ቃላት እንጠብቃለን፡- “ታስሬ ጠይቃችሁኛል” (ማቴ. 25:36)። ሦስተኛው ጭብጥ ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ብዙ ጊዜ ያከናወነውን እና “የዕውሮችን ዓይን መልሶ ማብራቱን የሚመለከት ነው። ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው የሚገልጽ ክፍል እንመልከት (ዮሐ. ምዕ. 9)። ይህ እንደ ብሉይ ኪዳን እና የአይሁድ ወግ መሠረት የመሲሑ መምጣት ምልክት ነበር። እንደውም ዓይነ ስውሩ በሚገኝበት ጨለማ የታላቅ መከራ መግለጫ ብቻ ሳይሆን ምልክትም አለ። በእውነቱ ከሥጋ ጋር የማይጣጣም እና በጥልቀት ማየት አለመቻል የውስጥ ዓይነ ስውርነት አለ።

ምናልባትም ከሥጋዊው የበለጠ ብዙ ሰዎችን ነፍሶቻቸውን የሚይዝ የብርሃን ጨረር ነው። በመጨረሻም እንደ አራተኛው እና የመጨረሻው ቃል ኪዳን፣ ከጭቆና ነጻ መውጣት፥ ይህም ከአይሁድ ኢዮቤልዩ ጋር በተያያዘ ከላይ የተጠቀሰው ባርነት ብቻ ሳይሆን አካልን እና መንፈስን የሚያስጨንቁ መከራዎችን እና ክፋቶችን ሁሉ ያጠቃልላል። መላው የኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚመሰክረው ይህንኑ ነው። ስለዚህ እውነተኛው የክርስቲያን ኢዮቤልዩ ትክክለኛ ግብ ይህ መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ እና ነባራዊ ኢዮቤልዩ ነው።

 

11 April 2024, 17:44