በሕንድ የሚነገር የካናዳ ቋንቋ የቫቲካን ሚዲያ 53ኛ ቋንቋ ሆኖ መቅረቡ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሕንድ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚናገሩት የካናዳ ቋንቋ ከማክሰኞ መጋቢት 24/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ከሚደመጡ 53 ቋንቋዎች መካከል አንዱ በመሆን፥ የቋንቋው ተናጋሪዎች በጽሑፍም ጭምር የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ዜናዎችን በቫቲካን የዜና አገልግሎት ድረ-ገጽ ላይ እንደሚያገኙት ታውቋል። ይህ የተነሳሽነት ተግባራዊ የሆነው በሕንድ የካርናታካ ግዛት፣ በቅድስት መንበር መገናኛዎች እና በባንጋሎር ሀገረ ስብከት ትብብር መሆኑ ታውቋል።
በሕንድ የባንጋሎር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፒተር ማቻዶ፥ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ድረ-ገጽ በካናዳ ቋንቋ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፒተር በመልዕክታቸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ የቅድስት መንበርን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እና ዓለም አቀፍ ዜናዎችን ማግኘት ለካርናታካ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሲኖዶሳዊነት ለማሳደግ እና ወንጌልን ለሌሎች ለማድረስ ላደረጉት ተከታታይ ጥረት አመሰግነው፥ ምእመናን ከቫቲካን ሬዲዮ ድረ-ገጽ ላይ ጽሑፎች ማንበብ፥ እንደዚሁም በድምጽ እና በምስል የሚተላለፉ ስርጭቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፒተር ከዚህም ጋር በማያያዝ የባንጋሎር ሀገረ ስብከት የመገናኛ መምሪያ ኩላዊት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሕዝቡ እንደሚያደርስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የቫቲካን የዜና አገልግሎት ከሚገለገልባቸው ቋንቋዎች መካከል ሌላ አዲስ ቋንቋ መጨመሩን የገለጹት፥ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ የካናዳ ቋንቋ ሕንድ ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚናገሩት ጥንታዊ ቋንቋ እንደሆነ ተናግረው፥ “ትንሽ ቢመስልም ትልቅ በሆነው ድርጅት ውስጥ እኛን የሚያግዘንን ካቶሊካዊ ማኅበረሰብን ሕያው ማድረግ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የካናዳ ቋንቋ ሕንድ ውስጥ 35 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚናገሩት የገለጹት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፣ በቫቲካን የዜና አገልግሎት ውስጥ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ ለባሕላቸው ክብር መስጠት እና ትክክለኛ የእርስ በርስ ግንኙነት በማድረግ በኅብረት መጓዝ እንደሆነ አስረድተዋል።
በ52 ቋንቋዎች የሬዲዮ አገልግሎት በሚሰጥበት የቫቲካን ሬዲዮ ውስጥ የካናዳ ቋንቋን ለመጨመር የተወሰነው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልዕክት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕንዳውያን ለማድረስ መሆኑን የቫቲካን መገናኛዎች ርዕሠ አንቀጽ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ አንድሪያ ቶርኒኤሊ ተናግረው፥ የተጠሩበት ዋና ዓላማ የሮም ጳጳስ የሆኑትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን እና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል እንደሆነ አስረድተዋል። “ችግር በበዛበት እና እርግጠኝነት በጠፋበት፣ ጦርነት እና ዓመፅ በሚታይበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ ቤተ ክርስቲያን በሮም እና በመላው ዓለም መካከል ያለውን ግንኙነት በኅብረት እና በመተጋገዝ የምታጠናክርበት የሚያጽናና ምስክርነት ነው” በማለት አቶ አንድሪያ ቶርኔሊ አስገንዝበዋል።
“የቤተ ክርስቲያን ስፋት በእውነት ድንቅ ነው” በማለት አጽንኦት የሰጡት የቫቲካን ሬዲዮ ሃላፊ አቶ ማሲሚላኖ ሜኒኬቲ፥ ከ93 ዓመታት በፊት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ አቶ ጉሊየልሞ ማርኮኒ ለዓለም ተስፋ የሚሆነውን የቫቲካን ሬዲዮ እንዲያቋቋም አደራ ማለታቸውን አስታውሰዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1990ዎቹ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ የሬዲዮ መልዕክት እስከ ቬትናም መድረሱን እና በሬዲዮ ጣቢያው አማካይነት የሚሠራጭ የወንጌል አገልግሎት አዲስ እና ሕያው ቤተ ክርስቲያንን እንደፈጠረ ገልጸው፥ ዛሬ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በአጫጭር ሞገዶች፣ በሳተላይቶች እና በድረ-ገጽ አማካይነት መልካም ዜናን በጦርነት እና በአመጽ ለቆሰለው የዓለማችን ክፍል ለማድረስ ብዙ ዕድሎችን ያመቻቸ መሆኑን አቶ ማሲሚላኖ ሜኒኬቲ አስረድተዋል። ሃላፊው በመጨረሻም “የካናዳ ቋንቋ ሌላው የሕያውነት እና የወንድማማችነት ምሳሌ” ነው ብለው፥ ምኞታችን እነዚህን መንገዶች በሃላፊነት እና በአንድነት መጓዝ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።