ፈልግ

 "ከአየር ንብረት ቀውስ ወደ የአየር ንብረትን መቋቋም" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የቫቲካን ጉባኤ "ከአየር ንብረት ቀውስ ወደ የአየር ንብረትን መቋቋም" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ የቫቲካን ጉባኤ  (AFP or licensors)

ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እና መሪዎች ለቫቲካን የአየር ንብረት ጉባኤ ተሰበሰቡ

ሳይንቲስቶች፣ የክልል እና የአካባቢ መሪዎች፣ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ባለሙያዎች “ከአየር ንብረት ቀውስ ወደ የአየር ንብረትን መቋቋም” በሚል ርዕስ በቅድስት መንበር ከፍተኛ የሳይንስ ትምህርት ተቋም እና በቅድስት መንበር የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ተቋም የተዘጋጀ ጉባኤ ላይ ለመካፈል በቫቲካን ተገናኝተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ከዓለም ዙሪያ የተውጣጡ ባለሙያዎች እና መሪዎች በቫቲካን በመሰብሰብ፥ በፕላኔታችን ላይ ያለውን የአየር ንብረት ቀውስ በልዩ ሁኔታ እንዴት መቆጣጠር እና መቋቋም እንደሚቻል ልዩ ትኩረት በመስጠት በመወያየት ላይ ናቸው። በቫቲካን የቅድስት መንበር የሳይንስ ትምህርት ከፍተኛ ተቋም እና የቅድስት መንበር የማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ ተቋም በጋራ በመሆን “ከአየር ንብረት ቀውስ ወደ የአየር ንብረትን መቋቋም” በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት የሚቆይ የመሪዎች ጉባኤ አዘጋጅተዋል።

ሀሳቦችን መለዋወጥ እና መፍትሄዎች ዙሪያ መወያየት

ከግንቦት 7 እስከ 9 ድረስ የሚካሄደው ይህ ስብሰባ ከአሜሪካ፣ እስያ እና አፍሪካ የመጡ የባለሙያዎች ስብስብን ከከተማዋ ከንቲባዎች እና ከክልሉ መንግስት አመራሮች ጋር አንድ ላይ ሆነው በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ እንዲወያዩ መንገድ ከፍቷል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችም እየተሳተፉበት ሲሆን፥ በቫቲካን ከተማ ውስጥ በሚካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ሁሉም የየራሳቸውን ገለጻ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።

የአየር ንብረት መቋቋምን ማበረታታት

የዓለም የአየር ንብረት ቀውስ አሳሳቢነት እና በሚቀጥሉት ጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ እንዴት እንደሚጨምር የስብሰባው ተሳታፊዎች የተስማሙበት ሲሆን፥ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ፤ ወደ አየር ንብረት የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረው በ50 በመቶ እንደጨመረና፥ የአየር ንብረት ለውጥ ይዞት የሚመጣውን መዘዝ ለማስቀረት ዋነኛ መፍተሄው የሙቀት መጠንን መቀነስ እንደሆነ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ይህም የምድራችን የሙቀት መጠን እ.አ.አ. በ2030ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአደጋ ገደብ ላይ እንዳይደርስ በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺዬስ መገደብ እንዳለበትም ተወያይተዋል።

የሙቀት-አማቂ ብክለት አጠቃቀምን ለመቀነስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ጥረት በምላሹ ጭማሪው በግማሽ ምዕተ-ዓመት መጨረሻ ላይ ከፍተኛ እንደሚሆን ሲጠበቅ፣ ሌሎች አካባቢዎች ግን 'የአየር ንብረትን የመቋቋም አቅም' አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ተብሏል። ይህ ጽንሰ-ሀሳብ የሰው ልጅ እንዴት የአየር ንብረት ለውጥን አስተማማኝ፣ ጤናማ፣ የበለጠ ፍትሃዊ እና ቀጣይነት ያለው ዓለምን እንዴት ማስተዳደር፣ ማላመድ እና መትረፍ እንደሚችል ይዳስሳል።

መተግበር፣ ማላመድ፣ ማስተዳደር

በቫቲካን የቅድስት መንበር የሳይንስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በዓለም ላይ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ብቸኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን፥ “ያልተበከለ ሳይንስ በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ማክበር፣ ነፃነቱን ማረጋገጥ እና ለሳይንስ እድገት ምርምርን የማበረታታት” ተልዕኮው አለው።

በ2014 ዓ.ም. የአየር ንብረት ለውጥን ሳይንሳዊ እና ማህበረሰባዊ ተግዳሮቶችን በተሻለ ለመረዳት ተመራማሪዎችን፣ ፖሊሲ አውጪዎችን እና የእምነት መሪዎችን በማሰባሰብ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አዲስ ተነሳሽነት ጀምሯል። የአየር ንብረትን የመቋቋም ፅንሰ-ሀሳብ የሶስት ቀናት የመሪዎች ውይይቶች ዋና መሰረት ሲሆን፥ ሶስት ነጥብ ያለው ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ የአየር ንብረት አደጋዎችን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት፥ የማይቀሩ አደጋዎችን ለመቋቋም የማስተካከያ ዘዴዎችን መውሰድ፥ እንዲሁም ቀጣይነት ያለው ቅነሳ እና የማላመድ እርምጃዎችን የሚያበረታታ የህብረተሰብ ለውጥ አካል ነው።

በአብሮነት መስራት

ጉባኤው ተሳታፊዎች እንደ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሃ ህይወት መጥፋት እና የዓለም አቀፍ እኩልነት ችግሮች ባሉ ተያያዥ የአካባቢ ተግዳሮቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፥ እነዚህን እውነታዎች ለመቆጣጠር እና ለመቅረፍ የመፍትሄ ሃሳቦችን እና አቀራረቦችን በመወያየት እና በማመላከት ላይ ናቸው።

የስብሰባው አዘጋጆች ይህ ተመራማሪዎችን፣ መሐንዲሶችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን፣ ሳይንሳዊ ባለሙያዎችን፣ የማህበረሰብ እና የእምነት መሪዎችን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እና ሰፊውን ሕዝብ የሚያሳትፍ ጉባኤ ባለብዙ ዲሲፕሊን አካሄድ እና አጋርነት እንደሚያስፈልገው ያውቃሉ።

የፕላኔታዊ የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮቶኮልን መተግበር

እነዚህ ጥረቶች በጉባኤው መደምደሚያ ላይ በሁሉም ተሳታፊዎች በተፈረሙ ‘የፕላኔታዊ የአየር ንብረት መቋቋም ፕሮቶኮል’ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። እንደ የሞንትሪያል ፕሮቶኮል ሁሉ፣ ሰነዱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም መመሪያዎችን እና እርምጃዎችን ያስቀምጣል ተብሏል። ፕሮቶኮሉ ለተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ቀርቦ በዓለም ዙሪያ ላሉ ሀገራት ይሰራጫል።

ለሰው ልጅ ሕይወት ተገቢውን ክብር መስጠት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ‘ላውዳቴ ዲየም’ ወይም ‘እግዚያብሄርን አወድሱት’ በሚለው ሐዋርያዊ ማሳሰቢያቸው ላይ እንደገለጹት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምክንያት ዓለም የሚያጋጥመውን አደጋ በተለይም ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ሰዎች የሚጎዳ መሆኑን እና ቀውሱን ለመቅረፍ አስቸኳይ ትብብር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

“ይህ ዓለም አቀፋዊ ማህበራዊ ጉዳይ የሆነ እና ከሰው ልጅ ህይወት ክብር ጋር የተያያዘ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ ጳጳሳት 'እርስ በርሳችን ያለን እንክብካቤ እና ለምድር ያለን እንክብካቤ አንድ ላይ የተሳሰሩ ናቸው' በማለት ከሥነ-ምህዳር አቀራረብም የሚያልፈውን የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ያለንን ስጋት እና ማህበራዊ ትርጉም በሚገባ ገልጸውታል።"
 

16 May 2024, 16:02