ፈልግ

ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ በጋዛ ውስጥ ብጹእ ካርዲናል ፒዛባላ በጋዛ ውስጥ 

ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ በዚህ ጨለማ ወቅት በጎ ሥራ ከሚሠሩት ጎን እንቆማለን አሉ

የኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓት አምልኮን የምትከተል ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹእ ካርዲናል ፒየር ባቲስታ ፒዛባላ በቅድስት ሀገር ስላለው አስቸጋሪ ሁኔታ እና ከችግሩ መውጫ መንገዶቹም ምን ያክል ከባድ እንደሆኑ ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“ጊዜው በጣም አስቸጋሪ እና የሚያም ነው፣ እያሳለፍን ያለነው በጣም ረጃጅም ሌሊቶች ነው፥ ነገር ግን ሌሊቶቹ እንደሚያልፉ እናውቃለን። ቤተክርስቲያን ለሁሉም ሰው የሚሆን ቆንጆ እና ጥሩ ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑ ሁሉ ጋር መስራት ያለባት ጊዜ ነው” በማለት ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ በሮም በኩል ሲያልፉ በእስራኤል፣ በጋዛ እና በዌስት ባንክ ስላለው አስቸጋሪ ሁኔታ ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

በአሁኑ ጊዜ በእስራኤል እና በተለይም በጋዛ ስላለው ሁኔታ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከነበሩት ውጣ ውረዶች ጋር ሲነጻጸር ሁኔታው ብዙ ለውጥ አላመጣም። ጋዛ አሁን ሰሜን እና ደቡብ፣ ራፋህ እና መሃከለኛው የጋዛ ከተማ በመባል ተከፋፍላለች። ብዙ ሰብአዊ እርዳታዎች በተለይም በሰሜን በኩል እየመጡ ያሉበት ወቅት ነበር። አሁን እንደገና ትንሽ ውስብስብ ሆኗል። ለምሳሌ ስጋ ጠፍቷል፣ የውሃ ችግር አለ፣ በአጠቃላይ ሁኔታው በጣም እየተባባሰ እና ከችግሩ መውጫ መንገዶችን ለማየት በጣም አስቸጋሪ ነው፥ የተጀመረው ድርድር ወደ ምንም ነገር እየመራ ያለ አይመስለኝም፥ ሆኖም ግን በፓርቲዎች በኩል አንድ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እውነተኛ ፍላጎት አለ።

በተጨማሪም በሊባኖስ ግንባር በኩል ያለው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ነው፥ ያሉት ነገሮች በጣም አበረታች አይደሉም ብለዋል።

በጦርነቱ ስለተጎዱት ሰዎች የተጠየቁት ብጹእነታቸው፥ የጋዛ ከተማ ፈርሳለች፥ ስለዚህ ተጎጂዎቹ ብዙ ናቸው። አሃዞችን መስጠት አስቸጋሪ ቢሆንም ነገር ግን ብዙ እንደሆኑ ይታወቃል፥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሁልጊዜም በርካታ መሆኑ የማይቀር ሀቅ ነው በማለት መልሰዋል።

የተፈጠረውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ህብረተሰቡን እና አብሮ መኖርን መገንባት ስለሚቻልበት ሁኔታ እና በተመሳሳይ ጊዜ የተከሰተውን ነገር ማሸነፍ የሚቻልባቸውን መንገዶች ያነሱት ብጹእነታቸው፥  “ስለዚህ ጉዳይ ለመነጋገር በጣም ገና ነው ብዬ አስባለሁ፥ አሁን በጦርነት እና በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” ካሉ በኋላ፥ ሁሉንም ሰው የነካው ይህ አሰቃቂ ሁኔታ ምን ያህል እንደሆነ እና ውጤቱን ለመረዳት ጊዜ ይወስዳል። መልሶ መገንባት አስፈላጊ ነው፣ ቁርጠኝነቱም አለ ይህንን በግልፅ ተረድቻለሁ። ግን በምን መንገድ፣ በምን መስፈርት እና ከማን ጋር? ለማለት ጊዜው በጣም ገና ነው ብለዋል።

በዌስት ባንክ ውስጥ ስላለው ሁኔታ የተጠየቁት ብጹእነታቸው፥ ዌስት ባንክ ሁል ጊዜ በፍንዳታ አፋፍ ላይ ናት፣ ችግሮቹም ቀጣይነት አላቸው፣ በተለይ በሰሜን በኩል ባሉት በጄኒን እና ናቡልስ አካባቢ የከፋ ነው። በሰፋሪዎች እና በአረብ መንደር ነዋሪዎች መካከል ያለው ግጭት ቀጣይነት ያለው ነው፥ ይህ ወደ መልካም ነገር የማያመራ መጥፎ ሁኔታን እየፈጠረ ያለ ነገር ነው በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በእስራኤል ውስጥ ወደፊት ምን ሊከሰት እንደሚችል የተጠየቁት ብጹእ ካርዲናል ፒዛቤላ፥ በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የውስጥ ችግር አለ፥ ማንም ጦርነት አይፈልግም ነገር ግን ማንም ሊያቆመው የሚችል አይመስልም፥ ችግሩም ይህ ነው። እርግጥ የሰሜኑ በኩል ያለው ጦርነት ቢጀመር፣ ሊባኖስ ቢያንስ በደቡብ ክፍል ሌላ ጋዛ የመሆን ስጋት ላይ ይወድቃል። እኔ በውትድርና ጉዳዮች ላይ ኤክስፐርት አይደለሁም፣ ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነታ ከዚህም በከፋ ሁኔታ ሊባባስ እንደሚችል ያሳያል በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ አውድ ውስጥ የክርስቲያኖች ሕይወት ምን እንደሚመስል ያነሱት ብጹእነታቸው፥ “ክርስቲያኖች የተለየ ሕዝብ አይደሉም፣ ሌሎቹ የሚኖሩትን ይኖራሉ። በጋዛ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ እናውቃለን፥ ነገር ግን በዌስት ባንክ ውስጥ በተለይም ከኢኮኖሚያዊ እይታ አንጻር በጣም ችግር አለ፣ ሙሉ በሙሉ ሽባ ሆኗል ማለት ይቻላል፣ ስራ ቀንሷል ወይም የለም፣ እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ህዝቡን ለስደት ያጋልጣሉ፥ በሚያሳዝን ሁኔታ በተለይ ክርስቲያኖች ለዚህ የተጋለጡ ናቸው” በማለት ክርስቲያኑ ማህበረሰ ስለሚደርስበት ችግር ጠቁመዋል።

ከጦርነቱ በኋላ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን ሊያደርግ ይችላል? ሰላምንስ ለማምጣት ከሁሉም በላይ ሊረዳ የሚችለው ማነው? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፥  “በዚህ ጊዜ ሰላም መፍጠር በጣም የራቀ ግብ ሆኖ ይታየኛል። በአሁኑ ጊዜ ፖለቲከኞች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግጭቱን ለማስቆም በዋነኛነት መስራት አለባቸው። ሰላም ለመፍጠር እና ከዚህ የተሻለ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ላይ ለመድረስ በእርግጠኝነት ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል እና ሃማስ ግጭቱን እንዲያቆሙ እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል መንገድ መፈለግ አለበት፥ ይህም ይበልጥ ወጥነት ወዳለው፣ ጠንካራ እና የተረጋጋ ወደሆነው የመጀመሪያ እርምጃ መውሰድን ይፈልጋል” ብለዋል።

ብጹእነታቸው የሚቀጥለው የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በአከባቢው ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ሲገልጹ፥ በእርግጠኝነት የአሜሪካ ምርጫ ተጽእኖ ይኖረዋል። ይሁን እንጂ መፍትሔዎቹ በአገር ውስጥ፣ በሁለቱ ወገኖች ማለትም በእስራኤልና በሐማስ መካከል መገኘት አለባቸው ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

የሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ ማድረስ ስለሚቻልባቸው ሁኔታዎች በማንሳት፥ አንዳንድ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፥ አህጉረ ስብከታችን ዕርዳታን ለማድረስ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፥ እንዲያውም ነገ የመጀመሪያው በርካታ ቶን ምግብ እና መሰረታዊ ፍላጎቶች ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን፥ ሆኖም ገና ብዙ ሥራ መሰራት አለበት፣ ምክንያቱም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለ በማለት አስረድተዋል።

እነዚህን ሁሉ ችግሮች እንደ አንድ የእምነት ሰው ያለዎት እይታ ምን ይመስላል? ተብለውን ከቫቲካን ዜና ለተጠየቁት ጥያቄ፥ “ተስፋ የእምነት ልጅ ነች። ጊዜው በጣም አስቸጋሪ እና የሚያም ነው፣ እያሳለፍን ያለነው በጣም ረጃጅም ሌሊቶችን ነው፥ ነገር ግን ሌሊቶቹ እንደሚያልፉ እናውቃለን። ቤተክርስቲያኒቷ በግዛቱ ውስጥ እንደመገኘቷ ለሁሉም ሰው የሚሆን ቆንጆ እና ጥሩ ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑት ሁሉ ጋር መስራት ያለባት ጊዜ ነው” ካሉ በኋላ፥ ሁሉም ሰው እርስ በርሱ ላይ እንቅፋት ሲፈጥር ቤተክርስቲያን ሁል ጊዜ እጇን ለሌላው መዘርጋት አለባት። ይህ በዚህ ጊዜ ልንሰራ የተጠራንበት ብሮን የተወለደ የእምነታችን ተግባር ነው ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ፒየር ባቲስታ በመጨረሻም ቅዱስ አባታችን በዓለም ላይ እንዳሉት ሌሎች በርካታ ሀገረ ስብከቶች ሁሉ፣ ከእኛም ጋር ሁል ጊዜ በጣም ይቀራረባሉ በዚህም ይቀጥላሉ” በማለት ከዓለም አቀፋዊቷ ቤተክርስቲያን የሚደረግላቸውን አብሮነት ገልጸዋል።
 

26 June 2024, 13:05