ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ይህን የማጽናኛ መልዕክት የተናገሩት በዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ እና የኪየቭ-ሃሊች ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሸቭቹክን በጎበኙበት እሑድ ሐምሌ 14/2016 ዓ. ም. ነበር።
የካርዲናል ፓሮሊን የዩክሬን ጉብኝት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክተኛ ሆነው ከሐምሌ 12-17/2016 ዓ. ም. ድረስ በዩክሬን ሐዋርያዊ ጉብኝት ያካሄዱት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በአገሪቱ የላቲን ሥርዓት ተከታይ ካቶሊክ ምዕመናን በበርዲቺቭ ወደሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በሚያደርጉት መንፈሳዊ ጉዞ ማጠቃለያ ላይ የሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለመምራት ነው።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የምሥራቅ አውሮፓ አገር ዩክሬንን የጎበኟት ሩሲያ ሙሉ ወረራ ካካሄደችባት ከየካቲት ወር 2016 ዓ. ም. በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. መጎብኘታቸው ሲታወስ፥ ከዚያን ጊዜ በኋላ በአገሪቱ ለታየው “ትልቅ ዕድገት” የግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባት እና መሪ ብጹዕ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሸቭቹክንን አመስግነዋቸዋል።
በእምነት አብሮ መጸለይ
ብጹዕነታቸው ከዚህ ቀደም አገርቱን በጎበኙበት ወቅት እንዳደረጉት ሁሉ፣ የዩክሬን ቤተ ክርስቲያን የነቢዩ ኤልያስን ምሳሌ በመከተል ትንቢታዊ ሚና እንዳላት አስታውሰው፥ “ሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” ከሚል እምነት በመነሳት ለሰላም መጸለይ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ምንም እንኳን ተስፋችን ጥቂት እና የተገደበ ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ከራሳችን፣ ከልባችን እና ከችሎታችን በላይ እንደሆነ እናውቃለን” ብለዋል።
የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን መልዕክት ለዩክሬን ሕዝብ ማድረስ
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አጽናኝ ከሆነ ማሳሰቢያቸው ጋር ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተላከለትን የወንድማማችነት መልዕክት ለዩክሬን ሕዝብ ካደረሱ በኋላ ቅዱስነታቸው ላለፉት ዓመታት በጦርነቱ በተመሰቃቀለች አገር ዩክሬን ላይ የሚደርሰውን መከራ ደጋግመው በማስታወስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ 21/2010 ዓ. ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባሰሙት ንግግርም ከመጀመሪያው ጀምሮ ዩክሬን ሕዝብ ባላችው ቅርበት ስቃዩን እና ሕመሙን እንደሚጋሩት መግለጻቸውን አስታውሰዋል።
የሰላም ፍላጎት እና የጦርነቱ መፍትሄ
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዩክሬን ውስጥ በአካል መገኘታቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም መገኘት ሕያው ገጽታን እንደሚጨምር ገልጸው፥ ይህም የሕዝቡን ስቃይ መጋራታቸውን እና በተለይም ሰላም የሚገኝባቸውን መንገዶች ለመክፈት እና መፍትሄን ለማምጣት እንደሚፈልጉ የሚገልጽ እንደሆነ ተናግረው፥ የዩክሬን ሐዋርያዊ ጉብኝቴ ከዚህ አንጻር ትንሽ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በንግግራቸው መደምደሚያ፥ በዩክሬን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እና ጠቃሚ ጊዜን በጋራ በመካፈላቸው የተሰማቸውን ደስታ በድጋሚ ገልጸዋል።