ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ትሪየስቴ ከተማን በጎበኙበት ዕለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን ትሪየስቴ ከተማን በጎበኙበት ዕለት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto) ርዕሰ አንቀጽ

“ከመልካም ሃሳቦቻችን ጋር በሁለት እግር ጠንክረን እንቁም!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለ50ኛ ጊዜ የተከበረውን የማኅበራዊ ሳምንት በማስመልከት በትሪየስቴ ከተማ እሑድ ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። በቅዱስነታቸው ንግግር ላይ በማስተንተን የቫቲካን መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ ያጋሩትን ሃሳብ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ “ሎዘርቫቶሬ ሮማኖ” በርዕሠ አንቀጽ አምዱ ላይ አስፍሯል እንደሚከተለው ቀርቧል፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኔ 30/2016 ዓ. ም. በትሪየስቴ ከተማ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር ‘ፖለቲካ ለኛ ምንድን ነው?’ በማለት ያቀረቡት ጥያቄ እያንዳንዱን ሰው የሚመለከት እንጂ ፕሮፌሽናል ፖለቲከኞች ነን የሚሉትን ብቻ የሚመለከት አይደለም።

ከዚህ ጥያቄ ጋር የተገናኙ ሁለት ተጨማሪ ጥያቄዎች አሉ። የመጀመሪያው ዴሞክራሲ ምንድን ነው? እያንዳንዱ ግለሰብ፣ የክርስቲያኖች እና ካቶሊክ ምዕመናን በዴሞክራሲ ቀውስ ውስጥ ያላቸው ሚና ምንድን ነው? የሚሉት ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ከትምህርት ጠበብት የሚሰጡ መልሶችን የሚጠብቁ አይደሉም።

እነዚህ ጥያቄዎች ይልቁን ፖለቲካን ወደ ስልጣን፣ ወደ ስሌት፣ ወይም ወደ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ደረጃ ስናወርደው ወይም የአዛዥነት ቦታ ለመያዝ ስንጠቀም እና ዴሞክራሲን ወደ ቀላል የሕግ ማስታወሻ ደብተር በመገልበጥ ትኩረትን ከሚሰርቁ ረቂቅ ጉዳዮች እንድንወጣ የሚያደርጉን ናቸው። ብዙ ሰዎች በስህተት እነዚህ ጥያቄዎች ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የቀረቡ አድርገው ያስባሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ ተዋንያን ከመሆን ይልቅ ተመልካቾች ብቻ በመምሰል ወደ ሌላ አቅጣጫ በመመልከት እንደ ጴንጤናዊው ጲላጦስ መሆንን እንቀጥላለን። እጆቻችንን አጣጥፈን መቀመጥ የሁለቱን ማለትም የፖለቲካ እና የዲሞክራሲ ቀውሶችን ያባብሳል። በመጨረሻም ዕጣ ፈንታው የሁላችን ይሆናል።

ነገር ግን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምላሽ የተለየ ነው። በችግር ወቅት በረቂቅ ነገሮች ላይ ተጠምደን ጊዜን ሳናባክን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሕዝብ የግል እና የጋራ ኅሊናችንን በተጨባጭ መንገድ እንድንመረምር ይጠይቀናል።

ምን እየሠራን እንገኛለን?
ፖለቲካ እና ዲሞክራሲ የሚመለከቱት የተወሰኑትን ሰዎች ብቻ ካልሆነ፥ ለምርጫ ድምጽ የሚሰጡትን፣ የሚያስተዳድሩትን፣ የሚቃወሙትን፣ የሚታገሉትን እና ጎዳና የሚወጡትን ከሆነ፥ እነርሱም ትግላቸው የእያንዳንዳችንን ሕይወት እና ፍላጎት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ከሆነ፥ ምርጫችንን የምንገልጸው በቅጽበት ሳይሆን ሁሉም ነገር እርስ በርስ የተገናኘ ከሆነ የእኛ ሚና ታዲያ ምንድን ነው? ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ‘ፖለቲካ ለኛ ምንድን ነው?’ በማለት ያቀረቡት ጥያቄ እኛ ራሳችንን እንድንመለከት ይጋብዘናል። በእርግጥም አስፈላጊ ጥያቄ ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀድሞው ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት አስተምህሮችን በመጥቀስ፥ ‘የፖለቲካ በጎ አድራጊነት ሚና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። በጥንቃቄ የተገነቡ የልዩነት ውጥኖችን ያስወግዳል። የፖለቲካ በጎ አድራጊነት አርቆ አሳቢነትን ያላገናዘበ የዘመናችንን አካሄድ አይከተልም። የሁሉን ተሳትፎ የሚጠይቅ፣ ምልክቶቹን እና መንስኤዎቻቸውን ለማሳወቅ የሚጥር የፍቅር ምሳሌ ነው። የፖለቲካ በጎ አድራጊነት ኃላፊነትን በመውሰድ ልዩነትን የሚያስወግድ የበጎ አድራጎት ዓይነት ነው’ በማለት ተናግረዋል።

ለሌሎች ፍቅር የቆመ በጎ ፖለቲካ በእኛ ውስጥ ምን ቦታ አለው? በጎ ፖለቲካ በግልጽ የሚታይ ተጨባጭ እና ሁሉን የሚያካትት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስምረውበታል።

በጎነት ያለበት ፖለቲካ የእያንዳንዳችንን የኑሮ ሁኔታ ያውቃል። ወደ ሰብዓዊ ዕድገት በሚወስድ ጎዳና የግል ሃላፊነት እንድንወስድ ይጠይቀናል። ሌሎች አማራጮችን በማቅረብ መገለልን ከሚያስከትል የሞራል ውድቀት መውጣትን ያካትታል። ፖለቲካን እና ዲሞክራሲን ለሚያበላሽ፣ ጥላቻን እና ግዴለሽነትን ለሚያስፋፋ አካሄድም ትክክለኛ መድሐኒት ነው።

ስለዚህ ፖለቲካን ሳናሳንስ በበጎነት መመልከት የሁላችን ሃላፊነት ነው። ተስፋን ወደ ነበረበት መመለስ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው። ትንቢቶቻችንን፣ ውጥኖቻችንን፣ ታሪኮቻችንን እና የጋራ ጥቅሞችን ማስከበር የሁላችን ሃላፊነት ነው። ፖለቲካ የአንድን ብሔር፣ ቤተሰብ እና ጓደኛ ጥቅምን ለማስከበር የቆመ ሳይሆን እያንዳንዱን ሰው ለመንከባከብ የቆመ ‘ተሳትፎ’ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተናግረዋል።

ተሳትፎ ሃላፊነት ያለበት ነው። ሕዝባዊነት በሌላ በኩል የእያንዳንዱን ሰው ተሳትፎ ይሰርዛል። በትልቁ በማሰብ በአንድነት ትልልቅ ሥራዎችን ለማከናወን መዘጋጀት የካቶሊኮች ተግባር ነው።

ከመልካም ሃሳቦቻችን ጋር በሁለት እግር ጠንክሮ መቆም
አባ ፕሪሞ ማዞላሪ እንደሚሉት መድረሻውን እና ውጤቱ ሳንዘነጋ ዘወትር ቀጣይነት ባለው ጉዞ፥ ደረጃ በደረጃ እውነታውን መለወጥ እንደምንችል በመገንዘብ፥ ታላቅ የእውነት ስሜት እና ገደብ ያለን ሰዎች ለመሆን ተጠርተናል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ‘የወንጌል ደስታ’ በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ “ትክክለኛ እምነት ሁል ጊዜ ዓለምን ለመለወጥ፣ እሴቶችን ለሌሎች ለማስተላለፍ እና ይህችን ምድር ካገኘናት በተሻለ መንገድ ለመተው ያለንን ጥልቅ ፍላጎትን ያካትታል” ሲሉ ጽፈዋል።

አባ ፕሪሞ ማዞላሪ ይህን በተጨባጭ ሲተረጉሙ ወደ ግራ እና ቀኝ ወይም ወደ መሃል ሳንመለከት ወደ እግዚአብሔር ብቻ እንድንመለከት ጋብዘውናል። ጴንጠናዊው ጲላጦስን ከመምሰል እና አዲስ ጀብድ ከመሥራት ይልቅ አዲስ ሰው ከመሆን ጀምሮ በነጻነት እና በቁርጠኝነት ራሳቸውን የሚያከብሩ ሰዎች መሆን ያስፈልጋል። ሌሎችን ለመታዘብ ከዳር የማይቆሙ ለፍትህ የሚታገሉ ናቸው። ፍቅርን ወደ ጥላቻ አንቀይርም። ለጉልበተኛ ባሕል እጅ አንሰጥም። አስማታዊ መፍትሄዎችንም አንስብክም። በፖለቲካ ውስጥ የበጎ አድራጎት አገዛዝን አንክድም። በምድር ላይ መንግሥተ ሰማያትን እንገነባለን ብለው ራሳቸውን የማያታልሉ፣ በአሸናፊውና በተሸናፊው መካከል በሚደረግ ጊዜያዊ የፖለቲካ ፈተና የማይሳሳቱ፣ ይልቁን ፖለቲካ ሁላችንም የተጠራንበት መንገድ እንደሆነ አድርገው የሚኖሩ እና ሁልጊዜ የተሻለ ለመሥራት እንደተጠሩ የሚያስቡ ናቸው።

አልዶ ሞሮ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በነበረበት ጊዜ የተናገራቸው ቃላት ወደ አእምሯችን ይመጣሉ፥ “ምንም እንኳን ሁሉ ነገር ቢኖረን፣ የታሪክ ዝግመታዊ ለውጥ፣ ለለውጥ ዋነኛ መንስኤዎች ብንሆንም ተስማሚ ፍላጎታችንን አያረካውም። በእነዚያ ሃሳቦች ውስጣዊ ጥንካሬ እና ውበት ውስጥ የተካተተ የሚመስል አስደናቂ ተስፋ እንዲኖር አይጠበቅም። ይህ ማለት ወንዶች ሁል ጊዜ ከሕግ እና ከመንግሥት ጋር ሲጋፈጡ ብዙ ወይም ጥቂት አስከፊ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ መሆን ይኖርባቸዋል።

ሕመማቸው ሙሉ በሙሉ አይጠፋም። ነገር ግን በሕመም እና በሕይወት አለመርካት የተነሳ የሰው ልጅ ብዙውን ጊዜ ጎስቋላ ነው። ዘወትር ከሚፈልገው ያነሰ የሚያገኝ ከሆነ፣ ሕይወቱ ከሚመኘው የተለየ ከሆነበት የሰው ልጅ በሕመም ውስጥ ይገኛል። ምናልባት ፍትህን ሙሉ በሙሉ እውን ሳያደርግ ዘወትር እየተጠማ ለዘለዓለም መኖር ሁሌም ታላቅ ዕጣ ፈንታው ይሆናል።”

 

09 July 2024, 16:14