ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዶ/ር ኮንቼታ ብሬሻ የገንዘብ ነክ መረጃ ባለሥልጣን ምክር ቤት አድርገው ሾሙ!
የእዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው የተሾሙትን ዶ/ር አንቶኔላ ስቺያሮን አሊብራንዲን በመተካት ዶ/ር ኮንቼታ ብሬሻ ሞራን የቫቲካን ቁጥጥርና የገንዘብ ነክ መረጃ ባለሥልጣን (ASIF) ምክር ቤት አባል አድርገው ሾሙ።
የቫቲካን የበላይ ቁጥጥር እና የገንዘብ ነክ መረጃ ባለስልጣን (በጣሊያንኛ ፊደሎች ASIF የሚታወቀው) እ.አ.አ በ2010 ዓ.ም በቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቤኔዲክት 16ኛ የተቋቋመው የገንዘብ ነክ ጉዳዮች ግልፅነት በተሞላው መልኩ ለመስራት እና የገንዘብ እጥበት እና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ለመደገፍ የሚደርገውን ጥረት ለመግታት ታስቦ የተቋቋመ ማሕበር ነው።
ዶ/ር ኮንቼታ ብሬሻ ሞራ የባንክ እና የገንዘብ ነክ ገበያ ህግ እና የአውሮፓ ህብረት የፋይናንሺያል ህግን ስያስተምሩ የነበረበትን በሮም ‘ትሬ’ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ህግ ሙሉ ፕሮፌሰር ናቸው። በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በአውሮፓ የባንክ እና የፋይናንሺያል ህግ የኢንተር ዲፓርትሜንታል ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው።
ሥራቸውን በጣሊያን ባንኮች ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ከጀመሩ በኋላ፣ በትምህርት ገበታ ውስጥ በመግባት የምርምር ሥራቸውን ጀመሩ፣ በትላልቅ የሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ላይ የምርምራቸውን ውጤት አሳትመዋል።
ዶ/ር ብሬሻ ሞራ ብዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በኃላፊነት ሠርተዋል። እርሳቸው የአውሮፓ ፓርላማ በባንክ አፈታት ጉዳዮች ላይ አማካሪ ነበሩ፣ የአውሮፓ ባንክ ባለስልጣን የባንክ ባለድርሻ አካላት ቡድን አባል (ኢቢኤ) እንደ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ አባል ነበሩ።
በተጨማሪም፣ ለስምንት ዓመታት ያህል፣ በመጀመሪያ በምክትል ፕሬዚደንትነት ከዚያም የአውሮፓ ኮሜርሻል ባንክ (ECB) አስተዳደራዊ የግምገማ ቦርድ (AboR) ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፣ ይህም የECB የባንክ ቁጥጥር ውሳኔዎችን ሕጋዊነት ይገመግማል።