የቻይና መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ለካቶሊክ ጳጳስ ይፋዊ እውቅና መስጠቱን ቅድስት መንበር በደስታ ተቀበለች
የቻይና መንግሥት ብጹዕ አቡነ ሜልኪዮር ሺ ሆንግዘንን የቲያንጂን ጳጳስ እንደሆኑ መቀበሉ ቅድስት መንበርን እንዳስደሰታት የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ማክሰኞ ነሐሴ 21/2016 ዓ. ም. ብጹዕ አቡነ ሜልኪዮር ሺ ሆንግዘን ሲቪል ጉዳዮች ለማስፈጸም የቲያንጂን ጳጳስ ሆነው በይፋ እውቅና ማግኘታቸው ቅድስት መንበር ያስደሰታት መሆኑን ገልጻለች።
ብጹዕ አቡነ ሜልኪዮር ሺ ሆንግዘን በቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ የቲያንጂን ማዘጋጃ ቤት ዕውቅና ማግኘታቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም፥ ይህ እርምጃ በቅድስት መንበር እና በቻይና መንግሥት መካከል ላለፉት ዓመታት የተካሄደው ውይይት አወንታዊ ውጤት ነው ብሏል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1929 የተወለዱት ብጹዕ አቡነ ሺ ሆንግዘን በሐምሌ 4/1954 የክኅነት ማዕረግ የተቀበሉ ሲሆን፥ በኋላም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ 15/1982 ዓ. ም. የቲያንጂን አካባቢ ሐዋርያዊ ተተኪ ጳጳስ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።
ብጹዕ አቡነ ሺ ሆንግዘን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ የነበሩ አቡነ ስቴፋኖ ሊ ጎንን ተክተው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
የቲያንጂን ሀገረ ስብከት ወደ 56,000 የሚጠጉ ምእመናን ያሉት፣ በ21 ቁምስናዎች ተከፋፍለው በ62 ካኅናት በኩል አገልግሎት እንደሚያገኝ እና ጥሩ ቁጥር ያላቸው ገዳማውያት እህቶች ያሉበት መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
28 August 2024, 16:18