ውይይት ለሃይማኖታዊ መቻቻል እና ለማኅበራዊ ሚዲያ የቁጣ ቅስቀሳ መፍትሄ መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አቶ አንድሬያ ቶርኒርሊ የሐዋርያዊ መልዕክቱ ስልሳኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በሰጡት አስተያየት፥ ውይይት በተፈጥሮ የማይታበይ፣ የማይመር እና የማያስከፉ እንደሆነ ገልጸው፥ በያዘው እውነት፣ በበጎ ሥራው እና በሚያቀርበው ምሳሌ የበለይነት እንዳለው፥ ትእዛዝ ማስተላለፊያ ወይም ግዴታ ማስቀመጫ መንገድ እንዳልሆነም አስረድተዋል።
በውይይት ሰላም እንደሚገኝ እና አመፅ እንደሚወገድ፣ ውይይት ታጋሽ እና ለጋስም እንደ ሆነ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ ከስልሳ ዓመት በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 6/1964 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት የመጀመሪያ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ላይ መግለጻቸውን አቶ አንድሬያ አስታውሰው፥ “እነዚህ ጥቂት ቃላት የቅዱስነታቸውን መልዕክት ልዩ ጠቀሜታ ለመገንዘብ በቂ ናቸው” ብለዋል።
ጣሊያን ውስጥ ብሬሻ ክፍለ ሀገር የተወለዱት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ የኢየሱስን ተልዕኮ “የድነት ውይይት ነው” ብለው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮዎቹን እንዲቀበል ማንንም እንዳላስገደደ እና ይህም ከባድ የፍቅር ጥያቄ እንደ ነበር፥ ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው ሰዎች ትልቅ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም መልስ ለመስጠት ወይም ላለመስጠት፣ ጥያቄውን ለመቀበል ወይም ላለመቀበል ሙሉ ነፃነት እንደሰጣቸው እና የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት ውይይትን በሚመርጥ ሰው ዘንድ የአክብሮት፣ የማስተዋል እና የመልካምነት ሃሳብን እንደሚያመነጭ ተናግረው፥ ውግዘትን፣ የሚያሳዝኑ ቃላትን እና ከንቱ ንግግሮችን እንደማያካትት ተናግረዋል።
“በዚህ ዓይነት መንገድ በሰዎች ላይ የሚፈርዱ፣ የንቀት ቋንቋዎችን በሚጠቀሙ፣ ጠላትነት ለማንገሥ የሚፈልጉ በሚመስሉ እና በዲጂታል ሚዲያ ላይ ጭውውቶችን በሚያቀርቡ ሰዎች መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ልብ ማለት ይቻላል” ብለዋል።
ለቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ውይይት በወንጌል ምስክርነት አማካይነት ፈጣን ለውጥ ለማምጣት ዓላማ እንደሌለው፥ መለወጥ ሁልጊዜ የእግዚአብሔር የጸጋ ሥራ እንጂ የሚስዮናውያን ጥበብ እንዳልሆነ፥ ይልቁኑ መለወጥ የሰውን የአዕምሮ ሁኔታ እና ሌሎችን ለማዳን ከሚደረገው ጥረት ሊለይ እንደማይችል አስቀድሞ ያሳያል።
አንድ ሰው ብቻውን ሊድን እንደማይችል ሁሉ እንዲሁም ራስን ከብክለት ለመከላከል እና ከዓለም ለመራቅ ግድግዳዎችን መገንባት መፍትሄ እንደማይሆን አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ገልጸው፥ ውይይት የእውነት እና የበጎ አድራጎት፣ የመግባባት እና የፍቅር ጥምረት ነው” በማለት የገለጹት አቶ አንድሬያ፥ ወንጌልን ለመስበክ ዓለምን እና አጀንዳዎቹን ማስማማት አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑት ሰዎች የማንነት ጥያቄ እንዳልሆነ አስረድተዋል። የራስን ማንነት ለይቶ ማወቅ ሌሎችን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከቱ የሚያደርግ አለመሆኑን የገለጡት አቶ አንድሬያ “ቤተ ክርስቲያን ካለችበት እና ከምትደክምበት ዓለም ጋር ውይይት ማድረግ አለባት” ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያን መናገር የምትፈልገው ነገር አላት፣ የምታስተላልፈው መልዕክት አላት፣ የምታቀርበው የግንኙነት መንገድ አላት” ያሉት አቶ አንድሬያ፥ “ዓለምን ከመቀየራችን በፊት ከዓለም ጋር መገናኘት እና መወያየት አለብን” ብለው፥ ዓለምም በበኩሉ ላይ ላዩን ብቻ መዳን እንደማይቻል የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው በኩል መግለጻቸውን አስታውሰዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የመጀመሪያ ሐዋርያዊ መልዕክት ከመጀመሪያዎቹ ቃላት ጀምሮ ስለምንኖርበት ዘመን ጠቃሚ የሆኑ ግንዛቤዎችን እንደሚያስጨብጥ አቶ አንድሬያ ተናግረው፥ ቤተ ክርስቲያን የመሥራችዋ የኢየሱስ ክርስቶስ ንብረት እንጂ የእኛ ንብረት እንዳልሆነች፥ በእጃችን እንዳልተገነባች እና የብልሃታችን ፍሬ እንዳልሆነች አስረድተዋል። ውጤታማነቷም በገንዘብ አቅም፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ስምምነት በተደረገባቸው ቅስቀሳዎች፣ ደረጃዎች ወይም የመሰብሰቢያ ቦታዎችን በመሙላት ችሎታ ላይ የሚመካ እንዳልሆነ ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያን በሕይወት የምትኖረው ትልልቅ ክስተቶችን፣ የሚዲያ ዕውቅናን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ስልቶችን መሥራት ስለምትችል እንዳልሆነ አቶ አንድሬያ ገልጸዋል።
ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ የምትኖረው በሕዝቦች መካከል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት በዕለት ስለምትመሰክር፣ ኃጢአተኞችን ይቅር በማለት የመዳን እና የተስፋ አድማስ የሚሰጥ የእርስ በርስ ግንኙነት መንገድ ስለምትከተል እና እያንዳንዱ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት የሚችልበትን ዕድል ለመስጠት በዓለም መካከል እንደምትገኝ አስረድተዋል።